የተተኪዎች ተስፋ

በአንዱዓለም ሰለሞን

ከ 20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮንሽፕ፣ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ውድድር ነው፡፡ ውድድሩ እ.ኤ.አ በ1986 ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የዓለም የወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮንሽፕ በሚል ስያሜ ሲሆን፣ በ2015 የአሁኑን ስያሜውን አግኝቷል፡፡ የመጀመሪያው ውድድር በግሪኳ አቴንስ ከተማ፣ በአቴንስ ኦሎምፒክ ስታዲየም ነበር የተደረገው፡፡ በወቅቱ የቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን በሜዳሊያ ሰንጠረዡ አናት ላይ በመቀመጥ ውድድሩን ፈጽማለች፡፡ በእስከ አሁኑ የውድድሩ ታሪክ፣ በርካታ ወጣት አትሌቶች በአሸናፊነት የውድድሩ ድምቀት መሆን ችለዋል፡፡ በላቀ ደረጃ ውጤታማ የሆኑ አትሌቶችን ስንመለከት ደግሞ፣ ከሴቶች አኔሻ ማክላውግሊን ዊልቢ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ናት፡፡ አትሌቷ ከ 2000 እስከ 2004 በተደረጉ ውድድሮች አንድ የወርቅ እና አራት የብር ሙዳሊያዎችን በማግኘት በዚህ ረገድ ስሟ በቀዳሚነት ይነሳል።

ከወንዶች ደግሞ፣ ቻርለስ ኔልሞስ፣ ዳቪድሰን ኢዝንዋ እና ዴክስተር ሊ የተባሉ አትሌቶች እያንዳንዳቸው አራት አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት በውድድሩ የታሪክ ድርሳን ስማቸው በደማቁ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ገጽ 24 ውድድሩ የዕድሜ ገደብ የተደረገበት ከመሆኑ አንጻር ይህን መሰሉን ውጤት ለማስመዝገብ ለአትሌቶች ከባድ ነው፤ የራሳቸውን ያለፈ ያሸናፊነት ውጤት ማስጠበቅ መቻልም እንዲሁ፡፡ ከዚህ አንጻር፣ በውድድሩ ታሪክ እስከ አሁን 22 አትሌቶች ብቻ (8 ወንዶች እና 14 ሴቶች) ይህን ለማሳካት (ያለፈ የአሸናፊነት ክብራቸውን ማስጠበቅ) ችለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር፣ አስራ አምስት አትሌቶች በግላቸው ብሎም በቡድን ባደረጓቸው ውድድሮችበአንድ የውድድር መድረክ ሁለት ድሎችን ማስመዝገብ (ሁለት ሜዳሊያዎችን ማግኘት) ችለዋል፡፡

በቅርቡ በፔሩ፣ ሊማ የተካሄደው ውድድር በዓይነቱ ልዩ የሚያደርገው ነገር ነበር፡፡ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአትሌቶች ለግልም ሆነ ለቡድን ልምምድ ለማድረግ የሚያስችል፣ ለመዝናናት ብሎም ለአብሮነት ምቹ የሆነ የአትሌቶች መንደር ተዘጋጅቶላቸዋል። ይህን የአትሌቶች መንደርም 1ሺህ 500 ሰዎች እንደጎበኙት ተዘግቧል፡፡ ይህን አስመልክቶ፣ የዓለም አትሌቲክስ ዋና ሀላፊ የሆኑት ስቴፋኔ ኤግል፡ “ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ለወጣት አትሌቶች ጥሩ እድል የፈጠረ መሻሻል አሳይቷል” በማለት ተናግረዋል፡፡ አስተያየታቸውን ሲቀጥሉም፡ “አትሌቶች በዚህ መልኩ በአንድ ላይ መሆናቸው ታዳጊ ኮከቦችን ለመደገፍና ለማብቃት ይረዳል፡፡ ይህ ፕሮግራም በዚህ መልኩ የተነደፈውም ለውድድሩ ተሳታፊዎች ለዝግጅት የሚረዷቸውን አስፈላጊ መረጃዎች ለማድረስ እና ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ አካላት ሙያዊ ምክረ ሀሳቦችን ለመስጠት ያመች ዘንድ ነው” ብለዋል፡፡ በዘንድሮው የሊማ ውድድር፣ 20 ሀገራት የወርቅ ሜዳሊያ ለማግኘት ችለዋል። ታይላንድ ደግሞ በውድድሩ ታሪክ የመጀመሪያዋ የሆነውን ሜዳሊያ ማሳካት ችላለች፤ ፕሪፖል ቦንሰን በተባለው የ100 ሜትር ሯጯ አማካይነት። አትሌቱ ከዚህ ድሉ ባሻገር በ 4በ100 ሜትር የዱላ ቅብብል ውድድር ሀገሩ የነሀስ ሜዳሊያ አሸናፊ እንድትሆን ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በውድድሩ 8 የወርቅ፣ 4 የብር እና 4 የነሀስ፣ በድምሩ 16 ሜዳሊያዎችን ያገኘችው አሜሪካ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ አናት ላይ ስሟ ተከትቦ ይገኛል፡፡ 6 የወርቅ፣ 2 ብር እና 2 ነሀስ፣ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ሃገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። አራት አትሌቶች የውድድሩን ክብረ ወሰን ያሻሻሉ ሲሆን ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው፤ በሴቶች 5ሺህ ሜትር 14:39.71 በመግባት ያሸነፈችው መዲና ኢሳ እና በሴቶች የ3ሺህ ሜትር መሰናክል 9:12.71 በመግባት ቀዳሚ በመሆን ያጠናቀቀችው ሲምቦ አለማየሁ፡፡

ሌሎቹ ሁለት ክብረ ወሰኖች፣ 39:24.85 በመግባት የ10 ሺህ ሜትር የእርምጃ ውድድሩን ባሸነፈው፣ ቱኒዚያዊው ራየን ቼሪኒ እና 8ሺህ 425 ነጥቦችን በማስመዝገብ የዴካትሎን ውድድር አሸናፊ በሆነው የቼክ ሪፐብሊኩ፣ ቶማስ ጃርቪኔ የተሻሻሉ ናቸው፡፡ ከ1 ሺህ 700 በላይ አትሌቶች በተሳተፉበት በዘንድሮ ውድድር፣ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው፤ እነዚህ አትሌቶች በቀጣይ በኦሎምፒክና ዓለም ሻምፒዮና ሀገራቸውን የሚያስጠሩ ይሆናሉና፡፡ ክብረ ወሰን ካሻሻሉት ከሁለቱ ሴት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ባሻገር፣ አብዲሳ ፈይሳ እና ሳሮን በርሔ በወንዶችና በሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር ውድድር በማሸነፍ ለሀገራችን ወርቅ አምጥተዋል፡፡ ጀነራል ብርሀኑ፣ በ800 ሜትር ወንዶች እና አለሽኝ ባወቀ፣ በሴቶች 3ሺህ ሜትር ውድድር ለኢትዮጵያ ወርቅ ያስገኙ ሌሎች አትሌቶች ናቸው፡፡ አትሌት አብዲሳ ፈይሳ እና አትሌት መቅደስ አለምሸት፣ በወንዶችና በሴቶች የ5ሺህ ሜትር ውድድር የሁለተኛ ደረጃን በማግኘት የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆነዋል፡፡ በ 3ሺህ ሜትር ወንዶችና ሴቶች ውድድር ደግሞ ሀይሉ አያሌው እና ማርታ አለማየሁ ሁለት የነሀስ ሜዳሊያዎችን ለሀገራችን አስገኝተዋል።

በእርግጥ በአጠቃላይ ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ውድድር፣ የሀገራችን ውጤት በበጎ የሚታይ ነው፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ሁለት ውድድሮችን ብንመለከት እንኳ የምናገኘው ውጤት ለዚህ አብነት የሚሆን ነው፡፡ በ2021 በኬንያ ናይሮቢ በተደረገው ውድድር፣ አዘጋጇ ኬንያ በ16 ሜዳሊያዎች፣ ማለትም 8 ወርቅ፣ 1 ብር እና 7 ነሀስ በማግኘት በቀዳሚነት ፈጽማ ነበር፡፡ አውሮፓዊቷ ፊንላንድና አፍሪካዊቷ ናይጄሪያ የሁለተኛ እና 3ኛ ደረጃን ባገኙበት በዚህ ውድድር፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ የ4ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች፤ 3 የወርቅ፣ 7 የብር እና 2 የነሀስ፣ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ በኮሎምቢያ፣ ካሊ በተካሄደው ውድድር ደግሞ፣ ደረጃዋን በማሻሻል 3ኛ ሆና ያጠናቀቀችው ሀገራችን፣ 6 የወርቅ፣ 5 የብር እና 1 የነሀስ፣ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች፡፡ አሜሪካ እና ጃማይካ ተከታትለው የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ በተቀመጡበት በዚህ ውድድር፣ ኬንያ ከኢትዮጵያ በመቀጠል የ4ኛ ደረጃን ይዛ ፈጽማለች፤ 3 የወርቅ፣ 3 የብር እና 4 የነሀስ፣ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት፡፡ የካሊው ውድድር አፍሪካ የተሻለ ውጤት ያስመዘገበችነት በመሆንም ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ፣ 2 የወርቅ፣ 1 የብር እና 2 የነሀስ፣ በድምሩ 5 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከኬንያ በመቀጠል የ5ኛ ደረጃን ይዛ መፈጸሟ እንደ አብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በእስከ አሁኑ የውድድሩ ታሪክ፣ አጠቃላይ የሀገራት ውጤትን ስንመለከትም ኢትዮጵያ፣ 263 እና 212 ሜዳሊያዎችን ካገኙት አሜሪካ እና ኬንያ በመቀጠል፣ የ3ኛ ደረጃን ይዛ ትገኛለች፤ በ46 የወርቅ፣ በ51 የብር እና በ32 የነሀስ፣ በድምሩ 129 ሜዳሊያዎችን በማግኘት፡፡