ሙሉነህ ቸሩ እባላለሁ የ28 ዓመት ወጣት ነኝ፡፡ ትውልዴ የሶዶ ደጋማ ክፍል የሆነችው አማውቴ፣ ንረጌ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ናት፡፡ በትምህርት ዝግጅት የመጀመሪያ ዲግሪዬን በሲቪል ምህንድስና ከጅማ ዩንቨርሲቲ በ 2008 ዓ.ም ተቀብያለሁ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲተ ቴክኖሎጂ ኢንስትትዩት 5 ኪሎ ካማፓስ በ ‘‘ሮድ ኤንድ ትራንስፖርት’’ ትምህርት ዘርፍ እየተከታታልኩ ሲሆን በስራ ደረጃ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በመሀንዲስነት እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡
ክፍል አንድ
በሶዶ ክደስታኔ ቤተ -ጉራጌ ከሚገኙ በርካታ ባህላዊ ክንውኖች መካካል ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓት አንዱ ነው፡፡ ይሕ የእርቅ ስነ ስርዓት በዘመናት ለውጥ በተለያዩ በጎም ይሁኑ መጥፎ ተፅዕኖዎች ምክንያት የመጥፋት አዝማሚያ ከታየባቸውና እራሳቸውን ተንገታግተው ካቆሙ የማህበረሰቡ ሀብታት ውስጥ ይመደባል፡፡
በጊዜ ሂደት ደግሞ እራሱን ከዘመኑ ጋር አዘምኖ፣ ከዘመናዊው ህግ ጋር እኩል ለማቆም እየጣረ ይገኛል፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድ ችገሮች ሲፈጠሩ ባህሉ በሚፈቅደው መሰረት ችግሩን መፍታት የተለመደ ተግባር ሆኖ ቆይቷል፡፡
ከነዚህ ችግሮች ሁሉ የነፍስ ማጥፋትን በተመለከተ የሚደረገው ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓት ለሀሉም የበላይና ሁሉንም በአንድነት የሚገልፅ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡
ምክንያቱም ፈጣሪ በራሱ አምሳል የፈጠረውን ግንባታ ከማፍረስ በላይ ወንጀልም፣ ሀጢያትም አይገኝምና ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ፅሑፍ ሁሉንም የዕርቅ ስነ ጫፎችን ያካትታል ያልኩትን በሶዶ ክስታኔ ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓት ያለበቂና ሰፊ ጥናት በእኔ እይታ ትክክል ነው ብዬ ያመንኩባቸውንና ከእኔም የእድገት ሂደት ውስጥ ያገኘኋቸውን እንዲሁም ከተወሰኑ ምንጮች ያሰባሰብኳቸውን ሁነቶች ለማካተት ሞክሬያለሁ፡፡
የግድያ አፈፃፀም ዓይነቶች
ግድያ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ በቀላልም ይሁን በከባድ ግጭት ምክንያት ሊፈጠር የሚችል ሁነት ነው፡፡ የግድያው አፈፃፀም ግን ለዕርቅም ይሁን በዕርቅ ስነ ስርዓት ውስጥ ለሚከናወኑት ማናቸውም ተግባራት ቁልፍ መመዘኛዎች ይሆናል፡፡ በዋነኛነት ከሚታዩት የግድያ አፈፃፀም ዓይነቶች ውስጥ የግፍ አገዳደል፣ በስህተት የሚፈፀም ግድያና እራስን በመከላከል የሚያጋጥም ግድያ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሆነ ተብሎ በጭካኔና ጠብቆ፣ አቅዶበት፣ ጊዜና አጋጣሚን አመቻችቶ የገደለ እንደሆነ የግፍ አገዳዳል ይሆናል፡፡
በታቃራኒው በስህተት የሚፈፀም ግድያ ሳይታሰብበት፣ ጋዳዩም ይሁን ሟች ምንም ባልገመቱበት ሁኔታ የሚከሰት ነው፡፡ ይህኛው አጋጣሚ ብዙውን ጊዜ በቤተሰብ፣ በጓደኛሞችና በመሳሰሉት መካካል የሚያጋጥም ነው፡፡
በዚህ ፅሑፍ ውስጥ ለማብራራት የምሞክረው የግፍ አገዳዳል በተፈፀመ ወቅት የሚከናወነውን የእርቅ ስነ ስርዓት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ሌሎቹ የግድያ አጋጣሚዎች በግፍ የእረቅ ስነ – ስርዓት ውስጥ መካካት የሚችሉ ናቸው፡፡
የገዳይና ሟች መስተጋብር
ባህላዊ የዕርቅ ስነ ስርዓት ወስጥ የሟችና የገዳይ ቅርበት ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ በተለይ ግድያው ከተፈፀመ በኋላ ለሚያደርጋቸው ማናቸውም ተግባራት ከባድ ጥንቃቄ ማድረግ ግድ ይለዋል፡፡ ይህ ተግባር ለገዳይ ቤተሰቦችም ከባድ ስጋት ይጥልባቸዋል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ገዳይ የመኖሪያ ቦታውን ሸሽቶ ስለሚለቅ ነው፡፡ ይህ ተግባር ለሟች ቤተሰቦች የገዳይ ቤተሰብና ገዳይ በተግባሩ መፀፀታቸውና ለዕርቅ ፍላጎት እንዳላቸው የሚገልፅ ነው፡፡ በተቃራኒው ግን ይህንን ተግባር ቦታ የማይሰጡት ከሆነ ቀጣይ ለሚያደርጉት የእርቅ ጉዞ ወስብስብና አስቸጋሪ የደርግባቸዋል፡፡
ከዚያም አልፎ ለበቀል ሊያነሳሳቸው ይችላል፡፡ የሟችና የገዳይ የቅርበት ሁኔታ ለዕርቁ የአንበሳውን ድርሻ ይወጣል፡፡ ከማሳያዎቹ አንዱ ገዳይና ሟች ከግድያው አስቀድሞ በነበረው ኑሯቸው ውሃ ከአንድ ወንዝ ቀድተው ይጠጡ ከነበረ የግዴታ የገዳይ ቤተሰብ የውሃ ምንጫቸውን መቀየር ይገባቸዋል፡፡ ይህም የሚሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡
አንደኛው የውሃ ምንጫውን በተወላቸው ጊዜ ‘‘እባካችሁን ይቅር በሉን፤ ይኸው ተፀፅተን መደበኛ ኑሯችንን ትተን ተቸግረንና ተንገላተን እየኖርን ነው ’’፣ የሚለውን ለማስተጋባት ሲሆን በሌላ በኩል በቀጣይ የሚልኩት ሽማግሌው የሚያቅበውና ማስረጃ የሚሆነው ስንቅ ያስቀምጡለት ዘንድ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በቀሪው ቤተ ዘመድ መካካል የቂም በቀል ደም መፋሳስ እንዳይቀጥል ለማድረግ ነው፡፡
ምክንያቱም የሟች ቤተሰብ በሚገኙበት ቦታ ሁሉ የገዳይ ቤተሰብ መራቅ ይገባቸዋል፡፡ አቅራቢያው ያገኘው እንደሆነ ልቡ ለበቀል .እጁም ለስለት ይፈጥናል ተብሎ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ለገዳይ ቅርበት ያላቸው ቤሰቦች በሙሉ ለሟች ቅርበት ካላቸው የማህበረሰቡ አካላት በፍፁም ፍርሀትና አክብሮት መራቅ ይገባቸዋል፡፡
የሽማግሌዎች አመራረጥ
በክስታኔ ቤተ ጉራጌ፣ ሽማግሌዎች ‘‘ ጉርዝ ’’´፣ የዕርቁ ሂደት ደግሞ ‘‘ግርዝና ’’´ ተብሎ ይጠራል፡፡ ማህበረሰቡ ለነዚህ ወገኖች ከፍ ያለ አክብሮት አለው፡፡ በምንም አጋጣሚ እንዲከፉበት አያደርግም፡፡ ሽማግሌዎች ስማቸው እንደሚጠቁመው ፣እድሜያቸው ጠና ያለና ምራቃቸውን የዋጡ መሆን አለባቸው ተብሎ ይታመናል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ እንዳለ ሆኖ በትምህርት ዝግጅታቸው የላቁ ፣ በብስለታቸውም የታመኑ ከሆኑ ሽምግልና መቀመጥ ይችላሉ፡፡ ይህም የሚሆነው አንድም በቦታው ለሚካሄደው የእርቅ ተግባር በጥሩ የዕውቀት ጥበቡ በጎ ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ ይታመናልና ነው፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ የአባቶቹን ባህላዊ ስነ ስርዓት ጠብቆ ለሚቀጥለው ተቀባይ ትውልድ ሳይበረዝ ያደርሳል ተብሎ ስለሚታመንበት ነው፡፡
የሀገር ሽማግለዎቹ ከየትኛውም አካባቢ የተመረጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዋናው ቁም ነገር የሚመረጡት ሽማግሌዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው፤ በመልካም ስራቸው ከፊት የሚቀድሙ፣ ሰው የማይበድሉ፤ ድንበር የማይገፉ፤ ሴራን የሚያከብሩ፤ በሽምግልናቸው የታፈሩ እንዲሁም በትውልድ ቅብብል ስማቸውን ከመቃብር በላይ ሊያስነሳላቸው የሚችል ፍትህ ያለው ሽምግልና መስጠጥ የሚችሉ መሆናቸውን መረጋገጥ ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ የገዳይ ቤተሰቦች በተመረጡት ሽማግሌዎች ሙሉ በሙሉ ካማኑባቸው ወደ ቀጣዩ ተግባር መሸጋጋር ነው፡፡
More Stories
“ትናንት ከሌሎች የቀሰምኩት ሙያ ዛሬ መተዳደሪያዬ ሆኗል” – ወጣት መለሰ ሾጤ
የልማት ዕድሎችና ተግዳሮቶች
ለአረጋዊያን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለፀ