በደረሰ አስፋው
ገና በልጅነታቸው ከጓሮ ሎሚ፣ ዘይቱን፣ ብርቱካንና ሌሎች ፍሪፍሬዎችን ወደ ገበያ አውጥተው በመሸጥ ነበር የንግድ ስራውን ሀ ብለው የጀመሩት፡፡ በዚህም ንግድ በትጋት እንጂ በዕድል የሚገኝ ውጤት አለመሆኑን ስለመገንዘባቸው ነው በነበረን ቆይታ የገለጹልን፡፡ የትናንቱ የልጅነት ዘመን የቤት ውስጥ ንግዳቸው ልምድ አጎናጽፏቸዋል፡፡ ለዛሬው ስኬታቸውም መሰረት እንደሆናቸው ይገልጻሉ። የንግድ ስራም በዘልማድ ሳይሆን ሳይንሳዊ መንገድንም መከተል እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ በንግዱ ዓለም ስኬትን ለመጎናጸፍ ትጋት፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እና የተገኙ ልምዶችንም ወደ ተሻለ ምእራፍ መቀየር አስፈላጊዎች ናቸው ይላሉ። በአሁን ወቅት በቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም በልዩ ልዩ ዲዛይንና ቀለማት ያሸበረቁ አበቦችን በቤት ውስጥ ያዘጋጃሉ፡፡ ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ጥሬ ዕቃውን ከአዲስ አበባ ያመጣሉ፡፡ በሀዋሳና አካባቢው በሚከፈቱ ባዛሮች /ኢግዚቢሽኖች/ ላይ በመሳተፍ ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ የገበያውን ዕድል ለመጠቀም ይተጋሉ፡፡ እኒህ የዛሬው የእቱ መለኛ አምድ ባለታሪካችን፡-
ወ/ሮ መስከረም ተበጀ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ነጌሌ ቦረና ነው፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት ኑሯቸውም በዚሁ ነጌሌ ቦረና ነበር፡፡ ትምህርታቸውንም እስከ 12ኛ ክፍል ነጌሌ ቦረና ነው የተማሩት፡፡ በአጼ ካሌብ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በነጌሌ ቦረና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፡፡ አሁን ግን መኖሪያቸው ሀዋሳ ከተማ አካባቢ ፒያሳ ነው፡፡ በሀዋሳ ከተማ መኖር ከጀመሩም ከ10 ዓመታት በላይ እንደሆናቸው ነው የገለጹት፡፡ ወ/ሮ መስከረም ከ12ኛ ክፍል በኋላ ግን ትምህርቱን አልቀጠሉም፡፡ “ህይወት በትምህርት ብቻ አይደለም” እንዳሉትም በልጅነት ዕድሜያቸው ወደ ውስጣቸው ዘልቆ የገባው የንግድ ፍቅር ሚዛኑን ደፋና ወደዚያው ገቡ፡፡ ቤተሰባቸው በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸው በጎ ተጽእኖ መኖሩ የማይካድ ነው፡፡ በአነስተኛ ንግድ በመጀመር ነገ የተሻለ ደረጃ እንደሚደረስም እምነቱ ነበራቸው፡፡ ለዚህም በቤት ውስጥ የጀመሩት የፍራፍሬ ንግድ ጅማሬያቸው ልምድ ቀስመውበታል፡፡
ወደ ሀዋሳ በመምጣት መኖር እንደጀመሩ የንግድ መስመር ያደረጉት በቦረና መስመር ተንቀሳቃሽ ንግዱን ነበር፡፡ ከቦረና አካባቢ ጤፍ፣ ስንዴና ሌሎች እህሎችን እንዲሁም የቤት እቃዎችንና አልባሳትን በማምጣት ሀዋሳ ላይ ለሚረከቧቸው ጎረቤቶቻቸውና ደንበኞች ያቀርባሉ፡፡ ወ/ሮ መስከረም የንግዱን ጥበብ የተካኑበት ይመስላል፡፡ ወደ ቦረና ሲሄዱም እንዲሁ ባዶ እጃቸውን አይሄዱም፡፡ ከሀዋሳና አካባቢው አቮካዶና ሌሎች የፍራፍሬና አትክልት ምርቶችን በመውሰድ ይሸጡ ነበር፡፡ አብዛኛው የልጅነት እድሜያቸውን ያሳለፉት በንግድ እንደሆነ የሚገልጹት ወ/ሮ መስከረም ዘይቱና፣ ሎሚ፣ ብርቱካንና ሌሎች ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን በጋሪ እየገፉ በጅምላና በችርቻሮ በመሸጥ ያካባቱት ልምድ ለዛሬው ንግድ እንደጠቀማቸውና ንግድ ሰዎችን የሚያተጋ የስራ ዘርፍ እንደሆነም የተገነዘቡበት ነው፡፡ የቦረናውን ንግድ አቋርጠው ንግዳቸውን በቋሚነት ያደረጉት ሀዋሳ ላይ ነው፡፡ ይህም አሁን ላሉበት የስራ ዘርፍ መሰረት የጣሉበት ነው፡፡
ሴት ልጃቸው የ12ኛ ክፍልን አጠናቃ ወደ ዩኒቨርስቲ መግባት አልቻለችም፡፡ ለዚህ መላው በቤት ውስጥ አለ በማለት የዲዛይን ሙያ እንድትማር አደረጓት፡፡ በሰለጠነችበት የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ስራ እንድትሰለጥን አደረጓት፡፡ በሰለጠነችበት ሙያም ጥሬ እቃውን ከአዲስ አበባና ሀዋሳ በመግዛት የሴቶች የእጅ ቦርሳና የተማሪዎች ቦርሳን በቤት ውስጥ በማምረት ስራ ጀመሩ፡፡ በዚህም የስራ ፈጠራ ሀሳባቸው ለልጃቸው የስራ ዕድል ከመፍጠር በዘለለ እሳቸውንም ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ነው የተናገሩት፡፡ በልጃቸው በጥበብ የተዘጋጁ ቦርሳዎችንም እየተዘዋወሩ መሸጥ የብዙዎችን ቀልብ ሳቡ፡፡ በርካታ ደንበኞችንም አፈሩበት፡፡
ከሀዋሳ ባለፈ እስከ ወላይታ፣ ሻሸመኔና ቦረና ድረስ በመውሰድ ይሸጣሉ፡፡ ዛሬ ላይ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ለሴቶች በሰጠው ዕድል ምስራቅ ጮራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አካባቢ የመስሪያ ቦታ ተሰጥቷቸዋል። “ውብናት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ” የተቋማቸው ስያሜ ነው፡፡ ምንም እንኳ ማህበረሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶች የመግዛት አመለካከቱ ዝቅ ያለ ቢሆንም ገበያውን ሰብረው ለመግባት በእግር እየተንቀሳቀሱ ጭምር ምርቶቻቸውን ያስተዋውቃሉ፣ ይሸጣሉ፡፡ ምርቶቻቸውንም በጅምላ ለነጋዴዎች እንደሚያስረክቡ ነው የተናገሩት፡፡ ከቦርሳው በተጨማሪ በቤት ውስጥ የተዘጋጁ ጌጠኛ አበቦችን እያመረቱ በወላይታ ሶዶና አካባቢው፣ ሻሸመኔና አካባቢው ለተቀባይ ደንበኞቻቸው ያስረክባሉ፡፡
ለዚህም ጥሬ እቃውን ከአዲስ አበባ በማምጣት እዚሁ ደግሞ የሰውን አይን በሚስብ መልኩ በተለያዩ ዲዛይኖችና ቀለማት በቤት ውስጥ በእጅ ያዘጋጃሉ። ለዚህም በሙያው የሰለጠነ ሰው በስልጠና እንደሚያግዛቸው ነው የተናገሩት፡፡ በዚህም ቢሆን በስራው የተሰማሩ በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ እንደሆኑበት ነው የተናገሩት፡፡ ወ/ሮ መስከረም ወደ ንግዱ ሲገቡ ትልቅ የሚባል ካፒታልን ይዘው አይደለም፡፡ የቦረናውን ንግድ ሲጀምሩ ከ500 እስከ 600 ብር በመያዝ ብዙ መነገድ እንደሚቻል ያስታወሱ ሲሆን ስንዴና ጤፍ ኪሎው በ10 ብር እና ከዚያ በታች ይገዙ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይህም በአነስተኛ መነሻ ካፒታል ወደ ንግዱ መግባት ይቻል እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ልጆቻቸውንም አስተምረው ለቁም ነግር ያደረሱት በዚሁ ንግድ ነው፡፡ ከቀለብ እስከ ልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ከዚሁ ከንግድ ከሚያገኙት ገቢ ነበር የሚጠቀሙት፡፡ አንድ ልጃቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በምህንድስና (ኢንጅነሪንግ) ተመርቋል፡፡ ሴት ልጃቸውም በዲዛይነር ተመርቃ በሙያዋ እየደገፈቻቸው ነው፡፡ ሌላው ወንድ ልጃቸውም ወደ ውጭ ሀገር ለስራ ሄዷል፡፡ 2 ልጆቻቸውንም በግል ትምህርት ቤት ከፍለው ያስተምራሉ፡፡ በከፈቱት የስራ መስክ ለአንድ ባለሙያም የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ በህይወታቸው ውጤታማ የሆኑት ነግደው ባገኙት ውጤት በመሆኑ ደስተኛ እንደሆኑም ነው የተናገሩት፡፡ በርካታ ሴቶች በሀገር ውስጥ ሰርቶ መክበር እያለ መሰደድን አማራጭ ያደረጉትን ወ/ሮ መስከረም ይቃወማሉ፡፡ ገንዘብ ካለ በሀገር ውስጥም ሰርቶ መለወጥ ይቻላል በማለት፡፡ መሰደድን አስበውት አያውቁም፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ከመሰደድ ይልቅ በሀገር ሰርተው መለወጥ እንደሚቻል በሀሳብ ይደግፏቸው ነበር። ይህ አስተሳሰብ በልጆቻቸውም እንደሚንጸባረቅ ነው የገለጹት፡፡ ወንድ ልጃቸው በኢንጅነሪንግ የተመረቀ ቢሆንም በሀገር ውስጥ ሰርቶ ለመለወጥ እንጂ ወደ ውጭ ተመኝቶ እንደማያውቅ በመግለጽ፡፡ የአቻ ጓደኛም ተጽእኖ አላሸነፈውም። እሱም ቢሆን በንግድ ስራ ላይ በመሰማራት ውጤታማ መሆን እንደቻለ ነው የገለጹልን፡፡
“ስኬት ማለት ትጋት ነው፡፡ አቅምህንና ጉልበትህን ብሎም ጊዜህን በአግባቡ መጠቀም ከቻልክ ውጤታማ መሆን ይቻላል” የሚሉት ወ/ሮ መስከረም አንድ ሰው በሚሰራበት ስራ ስኬታማ ለመሆን የተወሳሰበ ነገር እንደሌለው ነው ከልምዳቸው በመነሳት የተናገሩት፡፡ ከስኬታማ ሰዎች ልምድ መቅሰምም ሌላው ለውጤት እንዳበቃቸው የገልጹት ጉዳይ ነው። “ስኬት ወደ ሰማይ አንጋጠህ የምታመጣው ሳይሆን ሰርተህ በጥረትህ የምታመጣው ነው” የሚሉት ወ/ሮ መስከረም “ፈጣሪም ሰርተህ በላብህ ብላ እንጂ ቁጭ ብለህ ብላ አይልምና የፈጣሪም ትእዛዝ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል ይላሉ፡፡” ወ/ሮ መስከረም ወደ ፊት ትልቅ ቦታ የመድረስ ህልም አላቸው፡፡ አሁን የጀመሩት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርትን የማዘመን እቅድ አላቸው። በገበያው ላይ ተወዳዳሪ በመሆን ገበያውን ዘልቆ የመግባት ራዕይን ሰንቀው እንደሚንቀሳቀሱ ነው የሚገልጹት፡፡ ተቋማቸውን በዘመናዊ ማሽን በማደራጀት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ስራ አጦችም የስራ እድል የመፍጠር ሀሳብም የዕቅዳቸው አካል አድርገው እየሰሩ ነው፡፡
“የኔማደግ ለሀገርም ለኔም ጥቅም ነው” የሚሉት ወ/ሮ መስከረም ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው በቅርቡም እቅዳቸውን እውን እንደሚያደርጉት ነው የተናገሩት፡፡ ለዚህም ማነቆ የሆነባቸው የማምረቻ ቦታ ጥበትን በመቅረፍ የሚመለከተው አካል ትብብሩን እንዳይነፍጋቸውና ለስኬታቸው እውን መሆን እንዲያግዛቸው ነው የጠየቁት፡፡ በሚያመርቷቸው ምርቶች በጥራት የሚሰሩ እንደሀነ ይገልጻሉ፡፡ ከዋጋ አኳያም ተጠቃሚውን የማይጎዳ መሆኑን የሚገልጹት ወ/ሮ መስከረም ማህበረሰቡም የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።
በሀገራችን ሴትነት ባህላዊ ተጽእኖዎች ያሉበት እንደሆነ ቢረዱም እሳቸው ግን ከቤተሰባቸው ጀምሮ በተጽእኖ አላዳጉም፡፡ ዛሬም በባለቤታቸው አልተንጸባረቀም፡፡ ይህ ደግሞ ለውጤት እንዳበቃቸው ነው የሚገልጹት፡፡
“ጋሪ እየገፋው ንግዱን ስጀምር ባህላዊ ተጽእኖው አላንበረከከኝም፡፡ ንግዱንና ትምህርቱ ጎን ለጎን ነበር የማከናውነው፡፡ በነበርኩበት አካባቢ ለሌሎች ሴቶች አርአያ ነበርኩ፡፡ ዛሬም ቢሆን እቤት ውስጥ እጄን አጣጥፌ ተቀምጬ ከባል እጅ 5 እና 10 ብር አምጣ እያልኩ ህይወትን መግፋት አልፈልግም፡፡ አድርጌውም አላውቅም፡፡ “ሴት ልጅ ቤት ውስጥ መቀመጥ ጊዜው የሚፈቅደው አይደለም፡፡ ጊዜው ተለውጧል፡፡ መንግስት ለሴቶች ሰርተው እንዲለወጡና ከጓዳ እንዲወጡ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይህን ዕድል መጠቀም ደግሞ ከሴቷ ይጠበቃል፡፡ ሴት የወንድ እጅን መጠበቋ ተገቢ አይደለም፡፡
የወ/ሮ መስከረም በጥቂት ብር መነሻ ካፒታል የጀመረው ንግዳቸውም ዛሬ ላይ ወደ 100 ሺህ ብር ለመድረስ እየተንደረደረ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡ ማህበረሰቡ ሰልባጅ ምርቶችን ከመጠቀም ይልቅ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ቢጠቀም በዋጋም በጥራትም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ታምርት በሚለው እድል ለመጠቀም በተለያዩ ወቅቶች በባዛር ምርቶቻችንን ብናቀርብም የሚገዛው ግን ይህን ያህል አይደለም፡፡ ይህን አስተሳሰብ መለወጥ ይገባል፡፡ መንግስትም ህገ- ወጥ ንግዱ ላይ ጠበቅ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ለተማሪዎች፣ ለሴቶች እና ለጉዞ የሚሆኑ ምርቶችን ከንጹህ ቆዳ እናመርታለን። ለምርቶቻቸውም ዋስትና እንደሚሰጡ በመግለፅ ዜጐች በሃገራቸው ምርት እንዲኮሩና እንዲያግዟቸው ጠይቀዋል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው