የወንጀል ክሱ አንደምታ

በደረጀ ጥላሁን

በሀማስ የሚመሩ ታጣቂ ቡድኖች እ.ኤ.አ ጥቅምት 7/2023 ነበር በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር የእስራኤልን ዜጎች እና የጦር ሰፈሮች በማጥቃት ጦርነቱን የጀመሩት። በዚህ ጥቃት ሲቪሎችን ጨምሮ ብዙ እስራኤላውያን እና የውጭ ሀገር ዜጎች ተገድለዋል።

እስራኤል በአንፀሩ ወረራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጋዛ ውስጥ ከ 40 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 52 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ህጻናት ናቸው። ከዚህም ባለፈ የእስራኤል ጥብቅ እገዳ መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲቋረጡ አድርጓል፡፡ በመሠረተ ልማት ላይ የሚሰነዘረው ጥቃትም የጤና አጠባበቅ ላይ ችግር ከመፍጠሩም ሌላ ረሃብ ማስከተሉን የአልጀዚራ ዘገባ ያመላክታል፡፡

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ለእስራኤል ሰፊ ወታደራዊ እርዳታ ሰጥታለች በሚል በምትወነጀልበት በዚህ ወቅት፤ የሃገሪቱ የፍትህ ዲፓርትመንት እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7/2023 ሃማስ በእስራኤል ላይ በከፈተው የሮኬት ጥቃት ቢያንስ 43 የአሜሪካ ዜጎች እንደሞቱ ገልፆ የፌደራል አቃቤ ህግ በሀማስ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የወንጀል ክስ መስርቷል፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው በአሜሪካ የክስ መዝገብ ስማቸው ከተጠቀሰው ስድስት የሃማስ ባለስልጣናት ውስጥ ሶስቱ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል በቴህራን የተገደለው የቀድሞ የሃማስ የፖለቲካ ሃላፊ ኢስማኢል ሃኒዬ አንዱ ሲሆን፤ እስራኤል በጋዛ ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት የተገደሉት መሐመድ ዴፍ እና ማርዋን ኢሳ ይገኙበታል፡፡

በሌላ በኩል በጋዛ ውስጥ እንደሚገኙ የሚታመነው የሃማስ አዲሱ መሪ ያህያ ሲንዋር እንዲሁም መቀመጫውን በዶሃ ያደረገው እና የቡድኑን የዲያስፖራ ጽህፈት ቤት የሚመራው ካሊድ መሻል እና በሊባኖስ የሚገኘው የሀማስ ከፍተኛ ባለስልጣን አሊ ባራካ በህይወት ያሉ ተከሳሾች ናቸው።

የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሜሪክ “እነዚህ ተከሳሾች÷ የጦር መሳሪያ የታጠቁ፣ የፖለቲካ እና የገንዘብ ድጋፍ ከኢራን መንግስት ለሃማስ በማቅረብ የእስራኤልን መንግስት ለማጥፋት እና ሰላማዊ ሰዎችን ለመግደል ጥረት አድርገዋል ብለዋል።

በአሜሪካ ታዋቂው የቤይሩት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ራሚ ክሁሪ ለአልጀዚራ እንደተናገሩት አሜሪካ የሃማስ መሪዎችን መክሰሷ በመካሄድ ላይ ባለው የተኩስ አቁም ንግግር ውስጥ የአስታራቂነት ሚናዋን እንደሚጎዳ ጠቁመዋል።

“ዩናይትድ ስቴትስ÷ እስራኤል በጋዛ ላይ በምታደርገው እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ስትደግፍ ቆይታለች፡፡ እናም እንደ ሃማስ እና ሂዝቦላህ ያሉትን ቡድኖች በአሸባሪነት በመፈረጅ ስትቃወማቸው ቆይቷል” ሲሉ ክሁሪ ከአሜሪካ ቦስተን ከተማ ለአልጀዚራ ተናግረዋል።

የፍልስጤም ቡድንን ለመክሰስ የተወሰደው እርምጃ አሜሪካ ለድርጊቷ ሃማስን ተጠያቂ ለማድረግ ያሰበች ሲሆን፤ ይህም እስራኤልን ተጠያቂ የማድረግ ተመሳሳይ ፍላጎት እንደሌላት የሚያሳይ ነው ሲሉ ነው ክሁሪ የተናገሩት።

“ስለዚህም በአብዛኛዉ አለም እይታ አሜሪካ ታማኝ አይደለችም፤ ነገር ግን በእስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባባሪ ናት” ሲሉም ተደምጠዋል።

በኒውዮርክ ከተማ ፌደራል ፍርድ ቤት የቀረበው የወንጀል ክሱ÷ ለውጭ ሀገር አሸባሪ ድርጅት የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ በማሴር፣ የአሜሪካ ዜጎችን ለመግደል እንዲሁም ሽብርተኝነትን ለመደገፍ በማሴር እና የመሳሰሉ ክሶችን ያጠቃልላል። በተጨማሪም የኢራን እና የሊባኖስ ሂዝቦላህ የገንዘብ ድጋፍ፣ ሮኬቶችን ጨምሮ የጦር መሳሪያዎች እና ወታደራዊ አቅርቦቶችን ለሀማስ ጥቃቶች ማስፈጸሚያ መዋሉን የሚያትት መሆኑን ኤፒ ኒውስ ዘግቧል፡፡

“የቀረቡት ክሶች ሁሉንም የሃማስ ተግባራትን ኢላማ ያደረጉ ሲሆን እነዚህ ድርጊቶች የመጨረሻ አይሆኑም” ሲል ዋና አቃቤ ህግ ሜሪክ ጋርላንድ ተናግሯል። “ያህያ ሲንዋር እና ሌሎች የሃማስ ከፍተኛ አመራሮች ይህን አሸባሪ ድርጅት ለአስርት አመታት የፈጀውን የጅምላ ጥቃት እና የሽብር ዘመቻ በማቀነባበር እና የጥቅምት 7 ጥቃትን ጨምሮ ነው ክስ የተመሰረተባቸው።”

የወንጀል ቅሬታው እልቂቱን በሃማስ ታሪክ ውስጥ “በጣም ኃይለኛ፣ መጠነ ሰፊ የሽብር ጥቃት” ሲል ገልፆታል። “ከባድ መኪና፣ ሞተር ሳይክሎች፣ ቡልዶዘር፣ ፈጣን ጀልባዎች” ይዘው ነበር ወደ ደቡብ እስራኤል የገቡት የሚለው ክሱ÷ የሃማስ ሰዎች አስገድዶ የመድፈር ተግባር እንዲሁም መትረየስን የመሳሰሉ የጦር መሳሪያ በቅርብ ርቀት በመተኮስ በአሰቃቂ የጥቃት ዘመቻ እንዴት እንደተሳተፉ በዝርዝር ያስቀምጣል።

ክሱ የተካሄደው ኋይት ሀውስ ከግብፅ እና ከኳታር አቻዎቿ ጋር አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ፕሮፖዛል በማዘጋጀት ለአስራ አንድ ወራት የዘለቀውን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።

ጦርነቱ ከፍተኛ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውጤቶችን እያስከተለ ቀጥሏል። በዋነኛነት የፍልስጤም ደጋፊ የሆኑ ትላልቅ የተቃውሞ ሰልፎች በመላው አለም ተካሂደዋል፣ የተኩስ አቁም ጥሪም እየተደረገ ነው። ከዚህ ሌላ ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች የሚለውን ክስ እየገመገመ ይገኛል። ይሁን እንጂ ዩናይትድ ስቴትስ ለእስራኤል ሰፊ ወታደራዊ እርዳታ ሰጥታለች በሚል በርካታ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የተኩስ አቁም ውሳኔዎችን ቢያቀርቡም ውድቅ አድርጋለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተቃውሞ ቡድኖቹ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፖችን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸው፣ እንዲሁም የየመን ሁቲዎች ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የንግድ መርከቦችን ማጥቃታቸው፤ እንዲሁም በአሜሪካ የሚመራ ወታደራዊ ምላሽ መኖሩ እና በሊባኖስ ሂዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል እየተካሄደ ያለው የተኩስ ልውውጥ ተዳምሮ ሌላ ጦርነት ሊፈነዳ ይችላል የሚሉ አስተያየቶች እንዲደመጡ እያደረገ ነው።