“ምክክሩ ፍሬያማ እንዲሆን ሁላችንም የራሳችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅብናል” – ዶክተር ራሄል ባፌ

የሳምንቱ እንግዳችን ዶክተር ራሄል ባፌ ይባላሉ፡፡ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ እና የኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ እንግዳችን በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ከ30 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ በጥቂቱ እና እንዲሁም የህይወት ልምዳቸውን የተመለከቱ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በገነት ደጉ

ንጋት፡- በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ዶክተር ራሄል፡- እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ትውልድ እና እድገትዎን ቢያስተዋውቁን?

ዶክተር ራሄል፡- ተወልጄ ያደኩት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ዋካ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን እዛው ዋካ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ተከታትያለሁ። በወቅቱ ዋካ ላይ ከ8ኛ ክፍል በላይ ባለመኖሩ ወደ ጅማ በመሄድ ሚሽን ትምህርት ቤት ነው ትምህርቴን የጨረስኩት፡፡ የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ስራዬን አሀዱ ብዬ የጀመርኩትም አዲስ አበባ ሲሆን በመንግስት መስሪያ ቤት በጣም ጥቂት ጊዜያትን ሰርቻለሁ፡፡ አብዛኛው የስራ ሕይወቴ በግብረሰናይ ድርጅቶች ውስጥ ነው ያለፈው፡፡ ይህ ልምዴ በሀገር አቀፍ ደረጃ የግብረሰናይ ድርጅቶች መስራች እና ስራ አስኪያጅ ሆኜ የማገለግልበት ዕድልን ሰጥቶኛል፡፡ ከዚህም ባለፈ በዳውሮ ዞን “ሴፍ ማዘር ኤንድ ቻይልድ” በሚባል ግብረሰናይ ድርጅት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ ባሉ ትምህርት ቤቶች እና መዋለ ህፃናት ብዙ ስራዎችን መሥራት ችያለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ቤተሰቦቼ አዲስ አበባ ስለነበሩ ድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡

ንጋት፡- ከ12ኛ ክፍል በኋላ ቀጥታ ወደ ሥራ ነው የገቡት? የከፍተኛ ደረጃ ትምህርትዎንስ እንዴት ነበር የቀጠሉት?

ዶክተር ራሄል፡- የመጀመሪያ ድግሪዬን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመድቤ ማጥናት የምፈልገውን የፋርማሲ ትምህርት የመከታተል ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ ትምህርቴን ግን ቤተሰብ አካባቢ በተፈጠረ ችግር ምክንያት አቋርጬ ወደ ስራ ነበር የገባሁት፡፡ በወቅቱም ትምህርት አቋርጠሸ ከወጣሽ 12 ሲደምር 1 ወይም 2 እየተባለ ይያዝ ነበር፡፡ እኔ ግን በወቅቱ 12 ሲደመር 3 ተይዞልኝ ወጥቼ ነው ሥራ የጀመርኩት፡፡ የሥራ ጅማሮዬም መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ በመሥራት ነው የጀመረው። ከዚህ በኋላ ነው ቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በመግባት ትምህርቴን በማናጅመንት የትምህርት ክፍል ተምሬ የመጀመሪያ ድግሪዬን የያዝኩት፡፡ ሁለተኛ ድግሪዬን ደግሞ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን የጨረስኩ ሲሆን ሦስተኛ ዲግሪ /ፒ.ኤ.ች.ዲ/ ደግሞ ካሊፎርኒያ ቪዥን ተብሎ በሚጠራ ዩኒቨርሲቲ በሊደርሽፕ ሰርቻለሁ፡፡

ንጋት፡- የልጅነት ህልሜ ፋርማሲስት መሆን ነበር ብለውኛል÷ ወደዚያ እንዳይመለሱ ያደረገዎት ምን ነበር?

ዶክተር፡ ራሄል፡- ትምህርቴን አቋርጬ ወደ ስራ ስገባ በአስተዳደር ዘርፍ ነበር የተቀጠርኩት። ስለዚህ ማደግ የምችለው በዚያን አካባቢ ያለ የትምህርት ዘርፍ ስማር ነው በሚል ነው። በአጠቃላይ ከስራዬ ጋር እንዲሄድ በማሰብ ነበር የትምህርት ዘርፌን የቀየርኩት፡፡ ያም ቢሆን መድረስ ከምፈልገው ደረጃ ግን አላገደኝም፡፡ ጥሩ ዕድል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ንጋት፡- አሁን ላይ በምን ሥራ ላይ ነዎት?

ዶክተር ራሄል፡- በኔዘርላንድ መንግስት በሚደገፍ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ውስጥ ነው የምሰራው፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አባል በመሆን እጩ ሆኜ በምርጫ ለመወዳደር ሞክሬ ነበር፡፡ በዚህም በሚዲያ ላይ ብቅ የምልበት ተደጋጋሚ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር፡፡ በወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲ አባል እና እጩ ሆኖ መታየት በእኛ ሃገር ከባድ ስለነበር ሥራዬ ላይ ችግር ፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህም ከምሰራበት ማናጅመንት የቀረበልኝ ከፖለቲካ ፓርቲው ወይም ከስራው አንዱን እንድመርጥ ነበር የተጠየኩት፡፡ እኔ ግን ሁለቱም መብቶቼ ናቸው በሚል ተከራክሬ ሁለቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ እንደምችልም ነገርኳቸው፡፡ የእኛን አቅም ለማጎልበት (ኢምፓወር) ለማድረግ ከመጣችሁ እንደ እናንተ ሀገር ወደ ዴሞክራሲው ትምጣ እንጂ እንዴት አንዱን ምረጪ ብላችሁ ትቃወማላችሁ በማለት ተከራከርኩ፡፡ በወቅቱ እኔ የነበርኩበት ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ነበርኩ፡፡ ፓርቲው በወቅቱ ጠንካራ ስለነበር የምሰራበት መስሪያ ቤት ስጋት የገባው ይመስላል፡፡

ይሁንና ባደረኩት ክርክር የመስሪያ ቤቱ ቦርድ ሁለቱንም መቀጠል ትችላለች መብቷ ነው በማለት ምላሽ ቢሰጠኝም እኔ ግን መቀጠል እንደማልፈልግ አሳውቄ ሥራውን ለቀኩ፡፡ ይህ ጊዜ ለእኔ በጣም ፈታኝ ጊዜያት በህይወቴ ያሳለፍኩት ነበር፡፡ በዚህም ለሀገሬ አንድ ነገር ማበርከት አለብኝ ብዬ ነው ወደ ፖለቲካው መስመር የመጣሁት፡፡

ንጋት፡- እንዴት ነበር ሁለቱንም ስራዎች አስተሳስረው ማስኬድ የቻሉት?

ዶክተር ራሄል፡- ፈጣሪም ረድቶኝ ለሀገሬ መስራት አለብኝ የምለውን ቁጭት በማሰብ ነበር በሁለቱም ውጤታማ ለመሆን ስጥር የነበረው፡፡ በወቅቱ ምንም ዓይነት የቢሮ ስራም ሆነ ፖለቲካዊ ተልዕኮዬን ሳልበድል ነበር የሰራሁት፡፡ ወቅቱ የኮቪድ ወረርሽኝ የተከሰተበት ጊዜ ሰለነበር አንድ ሳምንት ቤት ቀጣዩን ደግሞ ቢሮ በመግባት ነው ስሰራ የነበረው፡፡ ሁለቱም ላይ ውጤታማ ነበርኩ ማለት እችላለሁ፡፡ በዚህም ብዙ ሰዎች ይገረሙ ነበር፡፡

ንጋት፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን እንዴት ነው መምራት የጀመሩት?

ዶክተር ራሄል፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ በመሆን በዶክተር አብይ ዘመን ስመረጥ የመጀመሪያ ሴት ሆኜ ቀርቤ ነው የተመረጥኩት፡፡ በሀገራችን ውስጥ ካሉ 53 ፓርቲዎች መካከል እኔ ብቻ ነበርኩ ሴት ሰብሳቢ ሆኜ የቀረብኩት፡፡ የመጀመሪያ ሴት ሆኜ መጥቼ የጋራ ምክር ቤቱን ስራ መበድልን አልመረጥኩም ነበርና ከእኔ የሚጠበቀውን ለመሥራት እሞክር ነበር። ይህን ማድረግ ካልቻልኩ ወደፊት ሴቶችን አያመጡም የሚል እልህ ስለነበረብኝ ነው ሥራዬን በቁርጠኝነት ስሰራ የቆየሁት፡፡

በጣም በጠባብ እድል ስመረጥ 52ቱ ወንዶች ስለነበሩ ከእነርሱ ጋር ውጤታማ ሆኖ ስራ ለመቀጠል ከቤተሰቦቼ ጋር በመነጋገር ጭምር ነበር የግል ስራዬን ለመልቀቅ የወሰንኩት፡፡

ንጋት፡- ምክር ቤቱን በመምራት ምን ያህል ጊዜ ቆዩ?

ዶክተር ራሄል፡- ለሁለት ዓመታት ያህል በታማኝነትና በጥንካሬ አገልግያለሁ፡፡ ለሁለተኛ ዙርም ተመርጫለሁ፡፡ በወቅቱም ጥሩ ስራዎችን በመስራት ውጤታማ ነበርኩ፡፡ ለሌሎች ተከታዮቼም ጥሩ ነገር ትቼ ነበር ያለፍኩት፡፡ በዚህም እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ለዚህም ነው ሴቶች በጣም ጠባብ የሆነ ዕድል ስለምናገኝ መወሰን ያስፈልጋል የምለው፡፡ የቤተሰብ ኃላፊ እና የአራት ልጆች እናት ከመሆኔ ባለፈ የማስተዳድራቸው ወላጆች ነበሩኝ። የትኛው ያመዝናል የሚለውን በመለየት ከእኔ በኋላ ለሚመጡ ሴቶች ጭምር በማሰብ ነው ስሰራ የነበረው፡፡ በዚህም ብዙ ተከታይ ማፍራት ያስቻለ ሥራ ሰርቻለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ሌሎች ሃገራት ውጤታማ ለመሆን ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ደግሞም ዋጋ ሳይከፈል የትም መድረስ አይቻልም፡፡

ንጋት፡- በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ውስጥ ያለዎት ኃላፊነት ምንድን ነው? እንቅስቃሴውንስ እንዴት ያዩታል?

ዶክተር ራሄል፡- በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ እና የኮሚቴ አባል በመሆን ነው እየተንቀሳቀስኩ ያለሁት፡፡ በሴቶችም ይሁን በፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካይነቴ እንዲሁም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚጠበቅብኝን በማድረግ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማበርከት እየጣርኩ ነው፡፡ የሁላችንም የሃሳብ ጠብታ ተጠራቅሞ ውጤት እንዲያመጣ እና ሀገራችን ውጤታማ የምትሆንበትን ምቹ ዕድል ለመፍጠር የራሴን የዜግነት አስተዋጽኦ እያበረከትኩ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት መንግስት ብቻውን የሚሰራው ስራ የለም፡፡ ውጤት ማምጣት የምንችለው ሁላችንም የራሳችንን ድርሻ ማድረግ እና ማበርከት ስንችል ብቻ ነው፡፡ ሀገራችን ከእኛ ብዙ ነገር ትጠብቃለች፡፡ የምንመካከረው ሁላችንም እንጂ የተወሰነ አካል ብቻ ባለመሆኑ የተጀመረው ምክክር ፍሬ አፍርቶ ውጤት እንዲመጣ ሁላችንም የራሳችንን ድርሻ ማበርከት ይጠበቅብናል፡፡

ንጋት፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰብሳቢ እንደመሆንዎ ያሉ ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ? ሴት በመሆንዎስ የገጠመዎት ችግር አለ?

ዶክተር ራሄል፡- ቀደም ሲል ሊነሱ የሚችሉ ችግሮች አይጠፉም፡፡ ነገር ግን ከእኔ በኋላ ብዙ ሴቶች ተገቢው ቦታ ላይ የሚመጡበት ዕድል በመፈጠሩ መሰል ችግሮች በብዛት አይታዩም፡፡ እንደ እኔ መጀመሪያ ላይ እራስን ማለማመዱ ከባድ ነበር፡፡ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ነው የገባሁት፡፡ ገብቼ ብዙም ሳልቆይ ነው ወደ አመራርነት የመጣሁት፡፡ በጣም ጥሩ አመራሮች ነበሩ፡፡ የደገፉኝ እና ብዙ ነገር ያስተማሩኝ እነሱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ እኔን የሚመስል ሴት ስላልነበር ይከፋኝ ነበር፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሂደቱን ስረዳ ነገሮች ቀለውኛል፡፡ ፖለቲካ ውስጥ መቆየት በራሱ የሚያስከፍለው ዋጋ ይኖራል፡፡ በእርግጥ ለህዝብሽና ለሀገር ጉዳይ የቆምሽ ከሆነ ምንም ዓይነት ጥቅም ሳይጠበቅ ነው መሰራት ያለበት፡፡ የሆነውም እንደዛ ነው፡፡ የመታሰር፣ የመገለል ሁኔታዎችን በመጋፈጥ ጭምር ነው የምትጓዥው፡፡ በወቅቱ ትልልቅ የሚባሉ ሰዎች ሳይቀሩ የሚከፍሉትን ዋጋ ሳይ ነበር በእጅጉ የበረታሁት፡፡ እኔን ለማገዝና እንዳልቸገር ዋጋ ከፍለው እኔ ጋር ይመጡ ነበር፡፡ እኔ እነርሱ ጋር አልሄድም፤ በዚህም አጋጣሚ ከልብ አመሰግናለሁ። በሥራው የተወሰኑ ዓመታትን ካሳለፍኩ በኋላ ግን እኔ ብቻ ሴት መሆኔን እስከረሳ ድረስ አይታወቀኝም ነበር፡፡ የጋራ ምክር ቤቱም ውስጥ ስመጣ ያን ጊዜ የነበረው ልምድ ስለነበረኝ ምንም አልተቸገርኩም፡፡ በዚህም ብዙ ነገር አይቻለሁ ተምሬበታለሁም፡፡ በተለይም የነበርኩበት ፓርቲ በጣም ነበር የቀረፁኝ፡፡

በጋራ ምክር ቤቱ ውስጥ ባለኝ ቆይታም ሴቶችን ወደ ፊት ለማምጣት ዕድሉ በጣም ጠባብ ስለነበረ ተነጋግረን የሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና የወጣቶች አደረጃጀት እንዲኖር በማድረግ የራሴን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፡፡ ይህንንም እንደ ትልቅ እድል ነው የማየው፡፡

ንጋት፡- ምን ያህል ጊዜያት ነው በስራ ላይ የቆዩት?

ዶክተር ራሄል፡- በጣም ብዙ ዓመታትን ነው በስራ ላይ የቆየሁት፡፡ ከ30 ዓመታት በላይ ቆይቻለሁ፡፡ ለሀገሬም ይሁን ለሴት እህቶቼ የራሴን ጥቂት አሻራ አኑሬያለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህን ስል ግን የሚቀሩ ብዙ ሥራዎች እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ እንደ ሃገር የፖለቲካ አካሄዳችን መሻሻል ያለበት ይመስለኛል፡፡ ችግሮችን ቁጭ ብሎ በመወያየት መፍታት የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር መሥራት ከሚመለከታቸው አካላት ይጠበቃል፡፡

ንጋት፡- ካሳለፏቸው የሥራና የሕይወት ልምድዎ በመነሳት ለሴት እህቶች ምን ይመክራሉ?

ዶክተር ራሄል፡- እኔ ካሳለፍኩት የህይወት ጎዳና አንፃር ለሴቶች የምመክረው የሚሰጡንን እና የሚመቻቹልንን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ነገር ለመሥራት መንቀሳቀስ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን ይህን ስል የተሰጠንን ኃላፊነት ለማስጠበቅ መስራት እንዳለብን መረሳት የለበትም፡፡ እንደ ዶክተር አብይ ፈቃደኛ የሆኑ መሪዎች የመኖሩን ያህል፤ ነገ የሚመጣው ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡ እኔ ዕድሉን ሰጥቼሽ ነው እንጂ ችለሽ አይደለም እዚህ የደረስሽው ሊል ይችላልና ለቀጣይነቱ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ ለቦታው ብቁ ሆነን ለመዝለቅ መሥራት ከሴቶች ይጠበቃል፡፡ ሁሉንም ነገር አሟልተሽ እንኳን ብትመጪ የመጣሽበት መንገድን በመካድ እንደ ውለታ ሊቆጥሩት የሚሞክሩ አይጠፉም። ስለዚህ ሴቶች እራስን መሆን ሊያሳጣ የሚችል ፈተና ጭምር ሊገጥም ስለሚችል ብቁ ሆነን መገኘት ብንችል መልካም ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም በነፃ የሚሰጥ ነፃነትና መብት የለም፡፡ በእኛ ሀገር ይቅርና በዓለም ዓቀፍ ደረጃም የለም፡፡ ወደፊት ልጆቻችን በዚያ መንገድ እንዳያልፉ ከወዲሁ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር መስራት ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ አይደለም ለሌላ ሴቶች ለራስ መቆም አንችልም፡፡ የትምህርት ዝግጅታችንን እና ልምዳችንን በመጠቀም በምንችለው ቦታ በመሆን ጥሩ ሥራ ለመስራት እራሳችንን ማብቃት አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ከቤታችን ጀምሮ እያሸነፍን መምጣት አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡

ስራዬን ስለቅ ልጆቼ እና ባለቤቴን አሳምኜ ነው፡፡ ይህም መጀመሪያ ቤታችንን ካሸነፍን በያለንበት ማሸነፍን እንችላለን፡፡ በዚህም ሴቶች ልጆቼም ሆኑ እህቶቼ ሁል ጊዜ በዚህ መንገድ እንዲሄዱ መልዕክቴን ማስተላለፍ እወዳለሁ ደግሞም እመክራለሁ፡፡

ንጋት፡- የቤተሰብ ሁኔታዎን ቢነግሩን? ምንአልባት እርስዎ የመጡትን መንገድ ተከትለው ይሆን?

ዶክተር ራሄል፡- ባለትዳር እና የሶስት ሴት እና አንድ ወንድ ልጅ እናት ነኝ፡፡ ልጆቼ ፈጣሪ ይመስገን ሁሉም ጥሩ ቦታ ደርሰዋል፡፡ እንደ እኔ ግን ወደ ፖለቲካው አልመጡም፡፡ በሚሰሩበት ቦታ ሁሉ ጠንካራ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው፡፡ ከእኔም የተሻለ ቦታ በመድረሳቸው ደስተኛ ነኝ፡፡ ከራሳቸው አልፈው ህዝብ እና እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በዚህም በጣም እኮራለሁ፡፡ በሀገርም ይሁን ከሀገር ውጪ ሄደው እየሰሩ ህዝባቸውን የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ልጆቼን እንደ አንድ ጥሩ እናት አርዓያ ሆኜ ጠንክሮ መማርም ሆነ መስራት ጨምሮ ሁሉንም ነገር መስራት እንደሚቻል እያሳየሁ ነው ያሳደኳቸው፡፡ እናትነት ከማንኛውም ነገር ሊያግድ እንደማይችልም ጠንቅቄ አሳይቻቸዋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ንጋት፡- የምክክር ኮሚሽኑ ውጤት አምጥቶ ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ምን ይመክራሉ?

ዶክተር ራሄል፡- ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሀገር ጉዳይ የጋራ አቋም በመያዝ ለስኬቱ መሥራት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ሀገራችን በጀመረችው ምክክር ፍሬ አፍርታ ውጤት ማምጣት እንዲቻል ሁላችንም የሀሳብ መዋጮ በማድረግ አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን፡፡ በዚህ የምክክር መድረክ ሃገር የሁሉንም ልጆቿ ሃሳብና ሠላማዊ እንቅስቃሴ ትፈልጋለች እና ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት መረባረብ አለበት የሚል መልዕክት አለኝ፡፡

ንጋት፡- አመሰግናለሁ፡፡ ስለነበረን ቆይታ በድጋሚ

ዶክተር ራሄል፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡