“የሰላም ጉዳይ ሀገራዊ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል” – ዲያቆን አንተነህ ጌትነት

የሳምንቱ እንግዳችን ዲያቆን አንተነህ ጌትነት ይባላሉ፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በአርክቴክቸርና አርባን ፕላኒግ የመጀመሪያ ድግሪ እንዲሁም በሀውሲንግ ኤንድ ሴንስተነብል ዴቨሎፕመንት ሁለተኛ ድግሪ አላቸው፡፡ በመንፈሳዊ ትምህርት ደግሞ በስነ መለኮት በሁለት የትምህርት መስኮች ለሁለተኛ ድግሪ እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ በመንፈሳዊ ሥራ ለ23 አመታት አገልግለዋል፡፡ አሁን ላይ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሲዳማ ሀገረ ስብከት ወንጌል ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ ይገኛል፡፡ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የአዲስ ዓመት ምንነት እንዲሁም በሰላምና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ

በደረጀ ጥላሁን

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

ዲያቆን አንተነህ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦ እንደ ሀይማኖት አስተምህሮ አዲስ አመት እንዴት ይገለፃል?

ዲያቆን አንተነህ፦ አመት ዘመን መቁጠሪያ ነው፡፡ ዘመን መቁጠሪያ ያስፈለገበት ምክንያትም የሚያልቅ ስለሆነ ነው፡፡ የተጀመረ ነገር ያልቃል። ስለዚህ ይህ አለም ስለተጀመረ ያልቃል፡፡ ሰው ይወለዳል፤ ሲወለድ መኖር ይጀመራል ሲሞት ደግሞ ያልቃል፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ የሰው ልጅ ሞት እንዳለበት እንዲያውቅና እንዲረዳ ከማህጸን በሚወጣበት ጊዜ የመኖሪያ ስፍራው አለም መሆኑን እንዲያውቅ ዘመን አስፈልጎታል፡፡

ይህ ዓለም ሰውን የሚያመጣበት ሥነ ስርዓት ደግሞ ራሱን ችሎ የዘመን ሥነ ሥርዓት አለው፡፡ እያንዳንዱ ዘመን ወቅቶች አሉት፡፡ እነዚህ ወቅቶች የሰው ልጅ በአካል በስጋ ደረጃ የሚመገብባቸው እና ሌሎች ሥነ ሥርአዓቶችም በዚሁ ዘመን ተካተውለታል፡፡ በቤተክርስቲያን ደረጃ ዘመን ኡደት ያለው ነው፡፡ ዘመን ከዚህ አለም ጋራ ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው ከክርስቶስ ጋር ያለ ግንኙነት ነው፡፡ ትልቅ ትርጉም የሚኖረው ከክርስቶስ ጋር ስለሆነ ዘመንም ከዚህ አንፃር ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት ይቆጠራል፡፡ በእለት ተእለት ኑሮ ጋር የሚቆጠርበት ሥነ ሥርዓትና ትምህርትም አለው፡፡

በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ያቡኸር ትምህርት ይባላል፡፡ አዲስ ዘመን ሲመጣ ያቡኸር ዘመን አቆጣጠሩ መስከረም አንድ ላይ ይመጣል፡፡ በአመቱ ያሉ አጽዋማት መቼ እንደሆኑና ሌሎች ዘመኑን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የሚጠቁም ይሆናል፡፡

አዲስ አመት በቤተክርስቲያን ደረጃ በሁለት ተከፍሎ ይታያል፡፡ ከክርስቶስ በኋላ ያሉ አመታት ሁሉ አዲስ አመት ናቸው፡፡ ከግለሰብ አንፃር እያንዳንዱ አመትም አዲስ አመት ይባላል። አዲስ ዓመት የምንጠብቀውና ሁሉም ተስፋ የሚያደርገው ሰላም ያለበትን ህይወት ነው። አዲስ አመት ሲከበርም አዲስ የሆነ የሰላም ብስራት ይዞልን እንዲመጣ በማሰብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለአዲስ አመት እንደ መሸጋገሪያ የምናደርጋት ጳጉሜን ነው፡፡ በዘመን ቁጥርና ስፍር ትርፍ ሆኗ የተገኘች ነች፡፡ ዘመን ስንቆጥር በፀሀይ ስለምንቆጥር በሰላሳ ቀን ነው የሚሰላው። ሌሎች የአለም ሀገራት በጨረቃ የሚቆጥሩ ሲሆን ወራቱ 28፣ 29፣ 30 እና 31 እያለ የተለያየ ቁጥር ይኖረዋል፡፡ በኛ ሀገር ብቻ ያለችው ጳጉሜ በአመት ካለው 365 1/4ኛ ቀናት ለሰላሳ ተካፍሎ የቀረው ጳጉሜን ይወልዳል፡፡ ትርፍ ነችና እንደ መሸጋገሪያ ተደርጋ ትቆጠራለች፡፡ ንጋት፦ ሀይማኖት ሰላምን ከመስበክ አኳያ ያላት አስተምህሮ ምን ይመስላል? ዲያቆን አንተነህ፦ ሰላምና ቤተክርስትያን መለያየት አይችሉም፡፡

በውስጣችን ያለ ሰላም ትልቅ እንዲሆንና ለሌላውም ማካፈል እንድንችል በቤተክርስቲያን ውስጥ በቅዳሴ እንዲሁም በስብከት ላይ ሁሌም ሰላም ይሰበካል። በግለሰባዊ ችግሮች ምክንያት ሰላምን የመቀበልና የማስተናገድ ችግር ካልሆነ በቀር ቤተክርስትያን ሰላም ላይ ያላት አቋም ትልቅ ነው። የምትመራውም በሰላም ነው፡፡ በሀገር ደረጃ አብዛኛው አማኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሚፈጠረው የሰላም ችግር በተለይ የሚሰጠውን የሰላም ትምህርት ሰዎች ባለማወቅና ባለመቀበል ብዙ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። በየቤተእምነቱ ምን ያህል ሰው እምነቱን ያውቃል? ለመማርስ ምን ያህሉ ይተጋል? የሚለውን መለየት አለብን፡፡ ከዚህ አኳያ ቤተ እምነቶች የሰላም ስጋት ሆነው አያውቁም፡፡

ንጋት፦ አብዛኛው አማኝ በሆነበት ሁኔታ ሰላም እየተሰበከ ሰላም የሚጠፋው ለምንድነው?

ዲያቆን አንተነህ፦ ስጋዊነት ሲያይል ሰላም ሊጠፋ ይችላል፡፡ በዚህም ወደ እርስ በእርስ ያለመግባባት እና ግጭት ይከተናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መንፈሳዊነትና የትምህርት ማነስ ይስተዋላል፡፡ በየትኛውም የሀይማኖት ተቋም የተሻለ እውቀት ያለው ጥቂት ነው፡፡ እንደ ሀይማኖት መንፈሳዊ እውቀት የሚኖረው ሰው ብዙ ላይሆን ይችላል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ሰውን ከሀይማኖቱ ይልቅ ወደ ሌላ ስሜት ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል፡፡ ይህም እንደ ሀገር ሰላም ሊያሳጣ ይችላል፡፡

ንጋት፦ ለሰላም መስፈን ከእምነት ተቋማት ምን ይጠበቃል? ዲያቆን አንተነህ፦ ትልቁ ችግራችን መንፈሳዊ እውቀት ይመስለኛል፡፡

ለዚህም ሰው ወደ መንፈሳዊ ህይወት እንዲመጣ መስራት ያስፈልጋል። ሌላው ለሁሉም መሰረት ቤተሰብ ነውና ቤተሰብ ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ቤተሰብ ሰላም ከሆነ ለሌሎች ሰላም ይሰጣል፡፡ ሰላም ከሌለ ግን ለሌላውም ሰላምን ሊሰጥ አይችልም፡፡ ቤተሰብ ላይ ሰውን ነው የምናገኘው፡፡ ከቤተሰብ ስንወጣ ነው ሌላውን ተቋም የምናገኘው፡፡ ስለዚህ ቤተሰብ ሰላም ከሆነ የትኛውም ተቋም ሰላም ይሆናል፡፡ እንደ ቤተእምነት በዚህ ጉዳይ እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ሰላምን ለማምጣት እየተደረገ ያለው ጥረት ቀላል አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ አምላክ የሚሠጠን ሰላም አለም እንደሚሰጠን ሰላም አይደለም፡፡ የዚህ አለም ጠባዩ ሰጥቶ መቀበል ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የአምላክ ሰላም ግን መስጠት ላይ መሰረት ያደረገ ነው። ስለዚህ በቤተእምነት ያለ ሰላም አይፈርስም የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ መስጠት እንጂ መቀበል ስለማይጠበቅብን ሁልጊዜ ሰላም የመፍጠር እድል አለው፡፡ ብዙዎች የእምነት ተቋማት ሰላምን እንደሚሰብኩ ያታወቃል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በሰላም ላይ ተግተን መስራት አለብን፡፡

ንጋት፦ ለሰላም መስፈን የምእመናን ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?

ዲያቆን አንተነህ፦ ትልቁ ጉዳይ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ነው፡፡ ለምሳሌ በእምነት ተቋማት የሚከበሩ የአደባባይ በአላት አሉ፡፡ እነዚህን በዓላት ማክበር የምንችለው እንደ ሀገር ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ልናከብረው አንችልም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰላምን ከማንም በላይ እንሻለን፡፡ ከአደባባይ በዓላት በተጨማሪም ጉዞ የሚደረግባቸው ብዙ በዓላት አሉ፡፡

በከተማችን እንኳን በሐምሌ እና ታህሳስ ወር የሚከበሩ የመላኩ ገብርኤል በዓልን ለማክበር ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ምእመናን ይመጣሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ታዲያ ሀገር ሰላም ስትሆን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሰላምን አብዝቶ መሻት ካላባቸው ግምባር ቀደሟ ቤተክርስቲያን በመሆኗ ሁሉም የእምነቱ ተከታይ ሆነ ሌላውም የማህብረሰብ ክፍል ሰላም ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። እናም የሰላም ጉዳይ ሀገራዊ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ንጋት፦ በሰላም ጉዳይ ከሌሎች ተቋማት ጋር የተሰሩ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

ዲያቆን አንተነህ፡- ለሰላም ጉዳይ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በተለይ መንግስት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለዚህም ነው በሚንስቴር ደረጃ የተቋቋመ መስሪያ ቤት መኖሩ። ከዚህ ሌላ ሰላምን ለማምጣት ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የሀይማት ተቋማት ናቸው፡፡ ተቋማቱ ሰላምን ማምጣት እንዲችሉ በትኩረት መስራት አለባቸው። በዚህ ደረጃ መንግስትም መስራት የሚገባውን ከሰራ እንዲሁም የእምነት ተቋማቱም ለሰላም ችግር የሆኑ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ከሰሩ ችግሩ ይወገዳል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ የሀይማኖት ተቋማቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መንፈስ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ የሚመለከተው የመንግስት መስሪያ ቤት በቅርበት ከተቋማቱ ጋር ቢሰራ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ በትብብር የመስራቱ ጉዳይ በቂ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ብዙ መስራት ይፈልጋል፡፡

የሀይማት ተቋማት እርስ በእርስ ያላቸው ግንኙነት ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ከመዋቅር አልፈው መግባባት መቻል አለባቸው፡፡ ምድራዊ ስሌትን በመተው በመንፈሳዊነት መግባባት ቢቻል መልካም ነው፡፡ ሁሉም የሚያመልከው አምላክን ነውና ሰዋዊ እና ከልብ የሆነ መግባባት ያስፈልጋል። በየሀይማት ተቋሙ የሚከናውኑ ሥርዓቶች ሀገራዊ መገለጫዎች ናቸው። እንደ ሀገር አንድ የሚያደርገን ስለሆነ እኔን ይመለከተኛል በማለት በመከባበር እና በመተጋገዝ መስራት አለብን፡፡ ይህ ሲሆን የምንፈልገው ሰላም ይመጣል፡፡

ንጋት፦ የእምነት ተቋማት በልማት ሥራ ያላቸው ተሳትፎ እንዴት ይገለጻል?

ዲያቆን አንተነህ፦ እንደ ሀገር ሰላም እንዳይኖር ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ ድህነት ነው። በዚህ ጉዳይ የሀይማኖት ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል፡፡ አንድ እምነት ያለው ሰው ድሀ መባል የለበትም፡፡ አብዛኛው ሀይማኖተኛ በሆነ ሀገር ድሀ መሆን የሀይማኖት ተፅዕኖ አለበት ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ድህነት ላይ መንግስት የራሱ ድርሻ ቢኖረውም በሀይማኖት ተቋማት ደረጃ ግን ተከታዮቻቸው ከድህነት የሚወጡበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርብናል። ተቋማቱ ተከታዮቻቸውን መብላት መጠጣት ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ማምጣት ቢቻል ጥሩ ነው። ይህ ሲሆን ሰላምንም ማጣጣም ይቻላል፡፡

በቤተክርስትያን ደረጃ ያለውን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ገዳማት ሥራ እንዴት እንደሚሰራ በደንብ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ገዳማቱ ላይ ያለውን ልምድ ወደ ከተሞች ማምጣት ከቻልን ከድህነት መውጣት እንችላለን፡፡ የተወሰኑ ገዳማት ከህብረተሰቡ ጋር ግንኙነታቸው እየጨመረ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ ኦሞ ትልቅ የልማት ሥራ እየተሰራ ነው። በሲዳማ ክልልም የታቀደ ሥራ አለ፡፡ ሀዋሳ ገብርኤልም እንዲሁ በቀጣይ ለሚሰሩ ሥራዎች ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በየተቋማቱ ግቢዎች ውስጥ የጓሮ አትክልቶችን ማልማት እየተለመደ ነው፡፡ ይህን ልምድ ወደ ሌሎች ቤተክርስቲያናት እያሰፋን ሲሆን ከትንሽ ጊዜ በኋላ ውጤቱ የሚታይ ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ ሁሉም ቢሰራ ድህነትን ማጥፋት ይቻላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ እንደሚታወቀው በሀገራችን ሁሉም ነገር አለ። መሬቱ ለም እና አየሩ ተስማሚ በመሆናቸው ከድህነት ሊያወጡ የሚችሉ ሥራዎችን በመስራት ሰላማዊ ሀገር መገንባት እንችላለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ንጋት፦ አዲስ አመትን አስመልክቶ የሚያስተላልፉት መልእክት ዲያቆን አንተነህ፦ አዲስ አመት ሲመጣ ሁልጊዜ የተለመደው መልካም ምኞት እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሳችሁ የሚለው ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በአዲስ አመት ምን አዲስ ነገር አስበናል? ለመለወጥ ያሰብነው ምንድነው? ትላንት ከነበረው የተሻለ ምን ዝግጅት አድርገናል? የሚለውን መመለስ አለብን። ይህ ካልሆነ የቀናት መቀያየር ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የምንቀይረው ነገር ከሌለን አዲስ አመት ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተቻለ መጠን ድህነትን ለመቅረፍ የምንሰራበት÷ ሰላምን ለማምጣት በየእምነታችን የምንተጋበት ዘመን ያደርግልን! ዘመኑ የምንስማማበት፣ ለሀገር የምንተርፍበት፣ ለመስጠት እንዲኖረን የምንሰራበት እና የምንተጋበት ዘመን ያድርግልን! አሜን!!

ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

ዲያቆን አንተነህ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡