የእርባታ ሥራ ባለቤቱ ካልተሳተፈበት ውጤት አይኖረውም – አቶ አሰፋ አሥማረ

በአብርሐም ማጋ

ባለታሪካችን ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በከብቶች እርባታ ተሰማርተው ልምድ የቀሰሙ ናቸው፡፡ የዛሬ 24 ዓመት ገደማ በአንድ ላም እርባታ የጀመሩት በባለቤታቸው እገዛና ጥረት ነበር፡፡ በአንዲት ላም የጀመሩት እርባታ አሥር ከብቶች እስከሚሆኑ ድረስ ሠራተኞች አልነበራቸውም፡፡ የሠራተኞች እገዛ ያገኙትም ከብቶቻቸው ከ1ዐ በላይ ሲሆኑ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ከ14 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የስራ ዕድል የፈጠሩ ቢሆንም የእሳቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ፉርሽካ መበጥበጡ፣ ላሞችን ማጠቡ፣ የከብቶች ምግብ ማቅረቡ አልተለያቸውም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቻ ወተት በማለቡ ተግባር ላይ አይሳተፉም፡፡

በዚሁም በከብቶቻቸው እርባታ ላይ የሚያደርጉት ጠንካራ ተሳትፎ ውጤታማ እንዳደረጋቸው በደስታ ይናገራሉ፡፡ አቶ አሰፋ በቀድሞው አጠራር በጐጃም ክፍለ ሀገር፣ በይልማና ዴንሳ ወረዳ በኦዳት ቀበሌ በ1948 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ዛሬ ላይ የ68 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ የልጅነት ህይወታቸው እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ነበር፡፡ ገና በልጅነታቸው በተለምዶ ቄስ ትምህርት ቤት በሚባለው ሐና ቤተክርስቲያን ገብተው ማንበብና መጻፍ ብሎም ዳዊት እስከመድገም ለመድረስ በቁ፡፡ ከዚያም በ1959 ዓ.ም በመንግስት ት/ቤት ገብተው ዘመናዊ ትምህርት የመማር እድል ገጠማቸው፡፡ በትምህርት ቤቱ ከ2ኛ ክፍል እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ያለውን በ4 ዓመት ውስጥ አጠናቀቁ፡፡ ቀደም ሲል በቄስ ት/ቤት ሲማሩ የጨበጡት እውቀት ረድቶአቸው ትምህርታቸውን የጀመሩት ከሁለተኛ ክፍል ነበር፡፡ በትምህርታቸው ጐበዝ ተማሪ በመሆናቸውም በየዓመቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ክፍሎችን ተዛውረዋል፡፡

በ1962 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው በጥሩ ውጤት ወደ 7ኛ ክፍል ተዛወሩ፡፡ ትምህርት ቤቱ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ስላልነበረው ቀጣዩን ክፍሎች ለመማር ባህር ዳር ከተማ መሄዱ የግድ ሆነባቸው፡፡ በመሆኑም በባህርዳር አፄ ሰርፀ ድንግል መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከ1963 ዓ.ም እስከ 1964 ዓ.ም 7ኛ እና 8ኛ ክፍል አጠናቀዋል። 9ኛ እና 1ዐኛ ክፍልንም በዚያው ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ ነገር ግን በ1966 ዓ.ም ላይ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሆነው የሁለተኛ ሴሚስተር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሳለ በአጋጣሚ ት/ቤቱ ተዘጋ፡፡ አጋጣሚውም መሬት ለአራሹ የሚል የተማሪዎች እንቅስቃሴ እንደነበርም አጫውተውኛል፡፡

ሆኖም በ1967 ዓ.ም 1ኛ ሴሚስተር ለተፈተኑ ተማሪዎች የነፃ ዝውውር ሲፈቀድ እሳቸውም ወደ 11ኛ ክፍል ተዛወሩ፡፡ ተዛውረውም በ1967 ዓ.ም ላይ እድገት በህብረት የእድገትና የሥራ ዘመቻን የደርግ መንግስት ሲያውጅ እሳቸውም በጐጃም ክፍለ ሀገር በገበዛ ማርያም ዘመቻ ጣቢያ ሥር ተመደቡ። ሆኖም በፀጥታ ምክንያት የዘመቻ ጣቢያው ሲታጠፍ እሳቸው የ15 ቀን ስልጠና ተሰጥቶአቸው የዘመቻ አስተማሪ በመሆን በወለጋ ክፍለ ሀገር በሆሮጉድሩ አውራጃ በራሶ በሚባል ት/ቤት ዘማች መምህር ሆነው ለአንድ ዓመት አስተምረዋል፡፡

በዚህ በመደበኛ ትምህርት ሲያስተምሩ በወር 90 ብር ደመወዝ እየተከፈላቸው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ በ1968 ዓ.ም የአንድ ዓመት ዘመቻ ሲጠናቀቅ ወደ ትውልድ ቀያቸው ይመለሳሉ፡ ፡ እንደተመለሱም ከ1969 ዓ.ም እስከ 1970 ዓ.ም ድረስ የፖለቲካ አቋማቸውን አጠናክረው የኢህአፓ አባል ሆነው ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቆዩ፡፡ በሴል ደረጃ በመንቀሳቀስ የድርጅቱን ልሳን ማንበብ፣ ማስተማር እና በርካታ አባላትን አሳምኖ ማፍራት ዋና ተግባራቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህን እንቅስቃሴ እያደረጉ ቆይተው በ1971 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ ተይዘው እስከ 1973 ዓ.ም ታህሳስ ወር ድረስ በእስር ቤት ቆይተዋል፡፡ ከእስር ቤት እንደተፈቱ ከታህሳስ ወር ጀምሮ ያቋረጡትን የ11ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡

በ1974 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው 3 ነጥብ በማምጣት በወቅቱ አለማያ እርሻ ኮሌጅ ገብተው በ1978 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በእንስሳት ሳይንስ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቁ፡፡ ከተመረቁ በኋላም በደቡብ ቀጠና በቀድሞ ጋሞ ጐፋ ክፍለ ሀገር ገለብ፣ ሐመር አናባኮ አውራጃ በጂንካ ከተማ የቆዳና ሌጦ ባለሙያ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ ከጂንካ ከተማ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር፣ ጀምጀም አውራጃ ክብረ መንግስት ከተማ ተዛውረው የቆዳና የሌጦ ጥራት ክትትል ባለሙያ ሆነው ተመደቡ፡፡

ዋና ተግባራቸውም ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚሄደውን ቆዳና ሌጦ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ አሽገው መላክ ነበር፡፡ እስከ 1981 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በክብረ መንግስት ከቆዩ በኋላ በ1982 ዓ.ም ወደ ያቤሎ አውራጃ ተዛውረው እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ የቦረና ደልጋ ከብቶች ዝርያ ማሻሻያ የእርባታ ማዕከል ሐላፊ ሆነው ለ6 ዓመታት ያህል ሠርተዋል፡፡ ከዚያም ወደ ቀድሞው ደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ተዛውረው ከ1988 ዓ.ም እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ወረዳዎችና የዞኑ የቆዳና የሌጦ ባለሙያ ሆነው ሠርተዋል፡፡

ከ1997 ዓ.ም ከህዳር ወር ጀምሮ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስም በደቡብ ክልል የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ ባለሙያ ሆነው ሠርተዋል። ለጡረታ ሁለት ዓመት ሲቀራቸው በራሳቸው ፈቃድ የመንግስት ሥራ ትተው በግል ሥራ ከተሠማሩ በኋላ በ2010 ዓ.ም ላይ ነበር የጡረታ ዋስትናቸውን ያስከበሩት፡፡ በግል ሥራ የተሰማሩትም በከብቶች እርባታ ነበር፡፡ በእርግጥ ሥራውን የጀመሩት በ1992 ዓ.ም ነበር፡፡ መነሻ ካፒታላቸውን ያገኙት በቀድሞው አጠራር ሲዳማ አስተዳደር አካባቢ ልማት ተብሎ በተቋቋመው የሠራተኞች የገንዘብ ቁጠባና ብድር አገልግሎት ማህበር አባል ሆነው ባገኙት 4 ሺህ 500 ብር /አራት ሺህ አምስት መቶ / ብድር ነበር፡፡

በተበደሩት ገንዘብም አንዲት የውጭ ዝርያ ያላትን ላም ገዝተው በመኖሪያ ቤታቸው እርባታውን አሀዱ ብለው ጀመሩ፡፡ በትምህርት ያገኙትን ሙያ ወደ ተግባር መለወጡ ለእሳቸው ቀላል በመሆኑ ለላሚቷ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረጉ የዘወትር ሥራቸው ሆነ፡፡ እርባታው በቂና ተገቢ እንክብባቤ ስለነበረው ቀስ በቀስ እያደገ ሲመጣ ነበር ወደ ሥራው በማድላት የመንግስት ሥራን ለቀው ወደ ግል ሥራቸው የገቡት፡፡ የሥራው ሂደቱም ቀስ በቀስ እቤት ከሚወለዱት በተጨማሪ አዳዲስ ጊደሮችን በየዓመቱ እየገዙ በመጨመር በ2008 ዓ.ም የላሞቹ ቁጥር አሥር ደረሰ፡፡

አሥር ከብቶችን ይዘው በመኖሪያ ግቢያቸው የሚያካሂዱት እርባታ ምቹ ቢሆንም ሰፊ የእርባታ ቦታ መፈለጉ የግድ ሆነባቸው፡፡ በዚሁም በዳቶ ቀበሌ 1 ሺህ 600 /አንድ ሺህ ስድስት መቶ/ ካሬ መሬት ወስደው የማስፋት ሥራ ጀመሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ35 በላይ ከብቶችን ያረባሉ። በቀን የወተት ምርቱ መጠን ከ180 እስከ 200 ሊትር ይደርሳል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የከብቶች መኖ ዋጋ በእጅጉ በመጨመሩ ምክንያት የአንድ ሊትር የወተት ዋጋ 60 ብር የነበረው 70 ብር መግባቱንም ከአንደበታቸው ለመረዳት ችለናል፡፡ የከብቶች ዋጋ ምን ያህል እንደሚሆን ተጠይቀው 1 እርጉዝ ላም እስከ 120 ሺህ ብር፣ ትልልቆቹ ደግሞ ከ2 መቶ ሺህ ብር በላይ እንደሚያወጡ ገልፀዋል፡፡ የአንዲት ላም የወተት ምርት በቀን ምን ያህል እንደሆነ ተጠይቀው እንደሁኔታው ምርቱ እንደሚለያይና ጊደሮች ከሆኑ በቀን እስከ 1ዐ ሊትር፣ ትልልቆች ግን በቀን 2ዐ ሊትር ድረስ እንደሆነ፣ እንዲሁም በአማካይ 14 ሊትር ወተት ከአንዲት ላም እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ስለእርባታው አጠቃላይ ሁኔታ ተጠይቀው ሥራው ከባድና አድካሚ እንደሆነ ይናገራሉ፡ – መመገቡ፣ ማለቡ፣ ማጠቡ፣ ጥጆችን መንከባከቡ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል ይላሉ፡፡ በዚሁም እሳቸው በሥራው ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡

ወደ ሥራ ቦታ እንደደረሱ ልብሳቸውንና ጫማቸውን አውልቀው በቦቲ ጫማና በቱታ ሆነው አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርጋሉ፡፡ በቅድሚያ የከብቶቻቸውን ጤንነት ያጣራሉ፡፡ ከዚያም እንደአስፈላጊነቱ ምግብና ውሃ ያቀርቡላቸዋል፡ አንዳንድ ልምድ የሌላቸው ሠራተኞች ሲኖሩ ሥራውን ያስተምራሉ። በአጠቃላይ ቀን ከሌሊት ውሎአቸው ከከብቶቻቸው ጋር ነው፡፡ በዚሁም በከብቶቻቸው እንክብካቤ ዙሪያ እሳቸው የማይሳተፉበት ሥራ አለመኖሩን ገልፀው “በከብቶች እርባታ ሥራ ባለቤቱ ካልተሳተፈበት ውጤት አይኖረውም” በማለት አጠቃላይ የሥራውን ሂደትና ውጤት አብራርተዋል፡፡ ይህ የእርባታ ድርጅታቸው “ዓይናለም የወተት እርባታ ማዕከል” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በስያሜው ላይ የተጠቀሰው ሥም የባለቤታቸው እንደሆነም ለማወቅ ተችሎአል፡፡

ድርጅቱ የወተት ምርቱን ለቸርቻሪዎች በማከፋፈልና በግል መሸጫ ቦታ አዘጋጅተው ይሸጣሉ፡፡ ይህ መሸጫ ቦታም የሚገኘው በሐዋሣ ቲቲሲ ሰፈር ከመምቦ ጀርባ የሐዮላ ት/ ቤት አዳሪ ተማሪዎች ማደሪያ ግቢ ፊት ለፊት ሲሆን ተገቢ አቅርቦትም አላቸው፡፡ አሬራ፣ አይብ፣ ቅቤ፣ ትኩስ ወተትና እርጐ በተገቢው ሁኔታ እንደሚያቀርቡም አብራርተዋል። እርጐ ለመጠጣት የፈለገ ሰው ለአንድ ሊትር 70 ብር ብቻ ወጭ ያደርጋል። በዋጋው ተመጣጣኝነትና በአቅርቦቱ ጥራት መነሻ በርካታ ደንበኞችም እንዳሉአቸው ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ አቶ አሰፋ ጤናማ የእርባታ ማዕከል የቀን ገቢው ከ80 እስከ 85 ከመቶ የሚደርሰው ወጪው ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አገላለፃቸው የቀን ትርፉ ከ15 እስከ 20 ከመቶ ብቻ ነው በማለት ሐሳባቸውን ያጠናክሩታል፡፡ ዓይናለም የከብቶች እርባታ ማዕከል ለ14 ሰዎች የሥራ እድል ሲፈጥር አሥር ቋሚና አራት ጊዜያዊ ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ በሥራ ሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮች ስለመኖራቸውም አቶ አሰፋ ተጠይቀዋል፡፡

የሰጡን ምላሽም የከብቶች መኖ ማልሚያ ቦታ አለመኖሩ ትልቁ ችግራቸው ነው፡፡ እነዚህ የውጭ ዝርያ ያላቸው ላሞች በሳምንት ሁለቴና ሶስቴ አረንጓዴ መኖ መመገብ ካልቻሉ ውጤታማነታቸው በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የመኖ ማልሚያ መሬት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ሌላኛው ደግሞ ከደብዘረይት የሚመጣው የተመጣጠነ የወተት ከብቶች መኖ እና የመድሃኒት ዋጋ በየቀኑ መጨመር ከባድ ችግር ሆኖባቸዋል፡፡ ለወደፊት የማስፋፊያ ሥራ የመሥራት ፍላጐት አላቸው፡፡

የወተት ማቆያ ቴክኖሎጂ በመግዛት ወተትን ከከተማዋ ውጭ ላሉት አካባቢዎች በማዳረስ የመሸጥ ዓላማ አላቸው። ሆኖም መንግስት ከጐናቸው ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውና አንዳንድ ሁኔታዎችን የቦታ የብድር አገልግሎት እንዲያመቻችላቸውም ጠይቀዋል፡፡