ቀብድ እና ቅድመ-ክፍያ

በደረሰ አስፋው

ቃብድ የሚለው ቃል በተለምዶ ቀብድ ብለን የምንጠራው ነው፡፡ ሕጉ ቃብድ ስለሚለው እኛም ቃብድ ብለነዋል፡፡ ከብላክስ ሎው ዲክሽነሪ መረዳት እንደሚቻለው የቀብድ ክፍያ ማለት ውል መደረጉን ለማረጋገጥ ገዥ ለሻጭ የሚሰጠው ገንዘብ ወይም ዋጋ ያለው ዕቃ ማለት ነው ብሎ ይተረጉመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቃብድ(ቀብድ) ከጥንት ጀምሮ ህብረተሰቡ ሲጠቀምበት የነበረ ነው፡፡

በሀገራችንም የፍትሀ ብሔር ህግ ቁጥር 1883 የቀብድ ትርጉም አንድ ወገን ለአንዱ ወገን ቀብድ መስጠቱ በማያከራክር ሁኔታ ውል መደረጉን ያረጋግጣል በማለት ይገልፃል፡፡ የቀብድ ክፍያ ማለት ተዋዋይ ወገኖች በውሉ ለመገደድ ወይም ውሉን እስከ መጨረሻው ተከታትሎ ለመጨረስ ያለውን ፍላጎት ለማሳየት ሲል በመያዣነት ለሌላኛው ወገን የሚሰጠው ክፍያ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ክፍያ የሚፈጸምበት ዓላማም ተደራዳሪው ወገን ውሉን አስመልክቶ ከልቡ መሆኑን ወይም በውሉ ለመገደድ ያለውን ፍላጎት የሚገልጽበት ስልት ነው፡፡ እንዲህ አይነት የክፍያ ስርዓቶች ከድሮ ጀምሮ ያሉ ስለመሆናቸው የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በእኛም ሀገር ቢሆን በባህል ህብረተሰቡ ሲገለገልበት የነበረ ስለመሆኑ ይታወቃል፡፡ የፍትሐ ነገስት ህግም ይህንኑ አስመልክቶ የሚደነግጋቸው አንቀጾች ነበሩት። በፍትሀ ብሔር ህግ ቁጥር 1884 ስር እንደተደነገገው ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር ቀብድ ተቀባይ ውሉ ከተፈፀመ በኋላ የቀብዱን ገንዘብ መመለስ ወይም ውሉ ሲፈፀም ከጠቅላላው ክፍያ መቀነስ ያለበት መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ ይህም ለተዋዋይ ወገኖች ምርጫ የተወ ቢሆንም ሌላ ስምምነት ካላደረጉ ውሉ ሲፈፀም የቀብድ ክፍያ እንደ ቅደመ ክፍያ ይቆጠራል ወይም ቀብድ ተቀባይ ለቀብድ ሰጪ ይመልሳል፡፡ ቀብድ ሰጨና ተቀባይ ውሉን ለመተው ቢፈልጉ በቀብድ ክፍያው ላይ የሚኖረው ውጤት የተለያየ መሆኑንም ከፍትሀ ብሄር ህጉ ድንጋጌ መገንዘብ እንችላለን፡፡ የአሁኑ የፍትሃ ብሄር ህግም ከአንቀጽ 1883 እስከ 1885 ድረስ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ይደነግጋል፡፡

አንቀጽ 1883 የአንዱ ወገን ለአንዱ ወገን ቃብድ መስጠት ውል መደረጉን ያረጋግጣል ይላል፡፡ ይሁን እንጂ፤ እንዲህ አይነት ውል በጽሁፍ ሊደረጉ የሚገባቸውን ውሎች በጽሁፍ ሳይደረጉ ቀርተው ቃብድ በመሰጠቱ ብቻ ውል መደረጉን ያረጋግጣል ማለት አይደለም፡፡ በፍትሃ ብሄር ህግ ቁጥር 1885 መሰረት ደግሞ ሌላ ስምምነት ከሌለ በቀር ቃብድ የሰጠውን ወገን፤ የሰጠውን ቃብድ በመልቀቅ ውለታውን በራሱ ፈቃድ ለማፍረስ የሚችል ሲሆን እንዲሁም ሌላ ስምምነት ከሌለ በቀር ቃብድ የተቀበለው ወገን የተቀበለውን ቃብድ አጠፌታ በመክፈል ውለታውን ለማፍረስ ይችላል ይላል፡፡ ይህም በሚታይበት ጊዜ ቃብድ ሰጪ ቃብድ ባይሰጥ ኖሮ ያገኝ የነበረውን መብት ማለትም በፍርድ ቤት ውሉ እንዲፈጸም የማስገደድ መብትን ገንዘቡ እስከተመለሰ ድረስ ሊጠቀሙበት የማይችል በመሆኑ የውልን አስገዳጅ ሁኔታ ይቀንሰዋል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ቀብድ ተቀባይ የተቀበለውን ቀብድ አጠፌታ በመክፈል ውሉን መተው ወይም ማፍረስ ይችላል፡፡ ከዚህም ቀብድ ሰጪና ቀብድ ተቀባይ ውሉን ሲያፈርሱ የሚከፈለው የቀብድ ክፍያ መጠን አንድ አይነት አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ቀብድ ተቀባይ የቀብዱን እጥፍ እንዲከፈል ህጉ አስገዳጅ ያደረገው ውሉ ባለመፈፀሙ ምክንያት በሌላኛው ወገን (በቀብድ ሰጪ) ላይ ሊደረስ የሚችለውን ጉዳት እንደማካካሻ እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡ በተዋዋይ ወገኖች ውል የመፈፀም ሂደት ውስጥ ሌላው የሚነሳው ጉዳይ የቀብድ እና የቅድመ ክፍያ ልዩነት ሲሆን አንድ ክፍያ ቀብድ ከሆነ ከፋይ ውሉ ቀሪ ቢሆን የሚያስመልሰው የቀብዱን እጥፍ ይሆናል፡፡ አንድ ክፍያ ቅድመ ክፍያ ከሆነ ግን ከፋይ አካል ገንዘቡን የሚያስመልሰው በፍ/ቤት ክስ በመመስረት፣ ውሉ ባለመፈፀሙ የደረሰበትን ኪሳራ በማስረዳት እና ያወጣውን ወጪ በመጠየቅ ነው፡፡

እዚህ ጋ መረዳት እንደምንችለው ቀብድ በሚሆንበት ወቅት ጉዳት መኖሩን ሳያመለክት ቀብድ ሰጪ ውሉን ካፈረሰው ሰው ላይ የተከፈለውን ገንዘብ እጥፍ መቀበል እንደሚችልና ቅድመ ክፍያ ከሆነ ግን ከፋይ የሚቀበለው የተከፈለውን ገንዘብ ያክል ብቻ ሆኖ ተጨማሪ ክፍያዎችን ለመቀበል ጉዳት መኖሩን ማመልከት እንዳለበት ነው፡፡ ይሁንና አብዛኛው ማህበረሰብ የሚረዳው መጀመሪያ የሚከፈለው ቅድመ ክፍያ ቀብድ እንደሆነ እና ውሉን ለመፈፀም ተዋዋይ ወገኖች ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት እንደሆነ ነው፡፡ ፍትህ ሚኒስቴር በንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ ሰነድ እንዳመለከተው ከሆነ ቀብድ የተቀበለ ሰው ውሉን ለመፈፀሙ ቀብድ ካልተቀበለ ሰው ይልቅ የሚተጋ/ ውሉን ለመፈፀም የሚታትር/ ሲሆን ቀብድ የከፈለ ሰውም ውሉን ላለማፍረስ እንደማሰሪያ የሚይዘው ይሆናል፡፡

ውሉን ለማፍረስ ሲወስን ገንዘቡን ለመተው አምኖበታል ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ቀብድ ተቀባይ የተቀበለውን ቀብድ እንዲመልስ አይገደድም፡፡ በቅድመ ክፍያ ወቅት ግን ይህ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ለዚሁ ውል ያወጣቸው ወጪዎች ከሌሉ በቀር የተቀበለውን ቅድመ ክፍያ እንዲመልስ ይገደዳል ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛውን ጊዜ ቀብድ ሰጪ ውል ሲያፈርስ ገንዘቡን ማስመለስ ሲፈልግ የሰጠሁት ቅድመ ክፍያ እንጂ ቀብድ አይደለም የሚሉት፡፡

የሁለቱን የክፍያ አይነቶች ጥቅም በምንመለከትበት ወቅት ቀብድ የፍርድ ቤት እንግልትና ወጪ የሚቀንስ እና በአብዛኛው በእርግጠኝነት የሚገኝ ስለመሆኑ እንረዳለን፡፡ የቅድመ ክፍያ ገንዘብ የሚከፈለው በውሉ ለመገደድ ያለን ፍላጐት ለመግለፅ ሳይሆን ወደ ፊት የሚመጣውን የእዳ መጠን ለመቀነስ ታስቦ የሚከፈል ክፍያ ነው፡፡ ቃብድ ግን በውሉ ለመታሰር እና ውል ስለመኖሩም ለማስረዳት በማሰብ የሚደረግ የውል አይነት ነው፡፡