በመሐሪ አድነው
የአካል ጉዳተኞች በአብዛኛው የሀገራችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በመስጠት ተሣትፎ ማድረግ ቢገባቸውም በተሟላ ሁኔታ ተፈፃሚ ሲሆን አይስተዋልም፡፡ የአካል ጉዳተኞች ድምፅና አተያይ በተገቢው ሁኔታ መንፀባረቁ ሁሉንም ያማከለ ውሳኔ ሰጪነት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ባለቤትነት ያላቸው መሆኑን ስለሚያሳይ የአካል ጉዳተኞች ተሣትፎ ቸል የሚባል ጉዳይ መሆን እንደሌለበት አካል ጉዳተኞች ራሳቸው በተደጋጋሚ ያሳስባሉ፡፡
በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚኖራቸው አስተዋጽኦም ቀላል የሚባል አይደለም። ለዚህም በርካታ የአካል ጉዳተኞች በሀገራችን የተለያዩ ዘርፎች ላይ ወደ ፊት በመውጣት ውጤታማ ሲሆኑ ተስተውሏል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ወጣት ማህቶት በለጠ ይገኝበታል፡፡ ወጣት ማህቶት በለጠ በአማራ ክልል ደቡብ ጐንደር ደራ ወረዳ ነው የተወለደው፡፡ የአራት አመት ህፃን እያለ ከባድ የአካል ጉዳት በውል ባልታወቀ ምክንያት ደርሶበታል፡፡ በደራ አካባቢ የቤተክህነት ትምህርቱን በመከታተል በርከት ያሉ ጊዜያትን አሳልፏል።
በትምህርት አቀባበል መልካም ስለነበረ መምህራኖቹ ዘመናዊውን ትምህርት እንዲማር ያበረታቱት ነበር፡፡ ሆኖም ግን መንፈሳዊውን ትምህርት ገፍቶበት ከጐጃም ደብረ ማዊ ተባሪት ሃይል ቅድስት ማሪያም ገዳምና ከአዴት መድሃኒ ዓለም ገዳም የቅኔ ትምህርት ተምሯል፡፡ ወደ ዘመናዊ ትምህርት የገባበት ምክንያት ከወረዳው የቤተክህነት ተማሪዎች የሠንበት ትምህርት ተማሪዎችን ማስተማር አለባቸው የሚል ሃሳብ ስለመጣለት ነበር፡፡ በዚህም ለስብከት አገልግሎት ተመልምሎ ማስተማር ጀመረ፡፡ ሠንበት ትምህርት የሚማሩት ደግሞ የዘመናዋ ትምህርት ተማሪዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም ዘመናዊውን ትምህርት ጐን ለጐን እንዲማር ብዙዎች ግፊት ያደርጉበት እንደነበር የሚናገረው ማህቶት፣ በዚህ ምክንያት ዘመናዊውን ትምህርት መማር ጀመረ፡፡ በተለምዶ የቆሎ ተማሪ /የአብነት ተማሪ/ የሚባለው በእንተ ማርያም ብሎ ከየመንደሩ ምግብ አሰባስቦ ነበር የሚማረው። ማህቶት ግን ምግብ ፍለጋ በየመንደሩ ሲዞር የሚያጋጥመውን በውሾች መሳደድ እንዳይገጥመው ሌሎች የቆሎ ተማሪዎች ካደረጉለት ድጋፍ በስተቀር በምንም አይነት የተረጂነት ፍላጐት እንዳልነበረው ይናገራል፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ ቤተክርስቲያን አካባቢ ለፀሎት ሲሄድም ሠዎች ሳንቲም ይጥሉለት ነበር፡፡ በይሉኝታ የተቀበለውን ሳንቲም ግን ተጠቅሞበት አያውቅም፡፡ ለቤተክርስቲያን ይሰጥ ነበር፡፡ “አሁን ላይ ግን ሠዎች ገንዘብ ሲጥሉልኝ አመስግኜና በአንዳንድ ጉዳይ ላይ ግንዛቤ አስይዤ ነው የምሄደው” ይላል ወጣት ማህቶት፡፡ ማህቶት አዕምሮው ምጡቅ ስለሆነ ደካማ ቤተጉባኤ ያለበት ተመድቦ ጐጆ ተሰጥቶት ተማሪዎችን እንዲያግዝ ተደርጓል። የተሰጠችው ጐጆም ለማህበር ቅርብ የሆነችና መንገዱም ለአካል ጉዳተኛ አስቸጋሪ ያልሆነበት ተመርጦ ነው፡፡
በተጨማሪነትም ረዳት ተመድቦለታል፡፡ በባህሪውም ተረጂነትን ስለሚጠላ ቤተ[1]ምርፋቅ ወይም በተለምዶ ዘኬ ቤት እንኳን መግባት አይፈልግም፡፡ ዝክርም ሆነ ክርስትና ሲኖር ለዚያ ልጅ ተብሎ እስከ ቤቱ ድረስ ነው እንደ አባወራ ካህን የሚላክለት፡፡ ማህቶት የቅኔ ማህተም ነው እንጂ የክህነት ስልጣን ስለሌለው አንተ በለኝ (የዚህን ጽሁፍ አዘጋጅ) ስላለኝ ነው አንቱታውን የተውኩት፡፡ በዘመናዊውም ትምህርት በማኔጅመንት ዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ አሁን ላይ በአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖም እያገለገለ ይገኛል።
መኖሪያውንም በባህር ዳር አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኑሮውን የሚመራው በንግድ ሥራ ነው፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ በመቸርቸርና በማከፋፈል ከባህር ዳር እስከ ቤንሻንጉል ክልል አሶሳ ድረስ ተቀንሳቅሶ ይሠራል፡፡ ጐን ለጐንም በወጣቶች አደረጃጀት ውስጥ ስለሚሳተፍ ትጋቱንና መንፈሰ ጠንካራነቱን የተረዳው የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የመስሪያ ሼድ ሰጥቶት ነው የንግድ ሥራውን እያቀላጠፈ የሚገኘው፡፡ ለንግድ ሥራ መነሻ ገንዘብ ያገኘውም ከማንም እርዳታ ጠይቆ አይደለም፡፡ በቤተ ክህነት ውስጥ ባገለገለበት ወቅት የተለያዩ ቅዱሳት መፅሐፍትን በመደጐስ /በመጠረዝ/ የሚያገኘውን ገንዘብ አጠራቅሞ ነው፡፡
የንግድ ሥራ በባህሪው ተሯሩጦ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ይሄ ደግሞ ለአካል ጉዳተኞች ፈታኝ ነው፡፡ ማህቶት ግን ሥራ የጀመረባቸው የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ላይ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በፅናት በማለፍ ጥንካሬውን ማስመስከር ችሏል፡፡ አሁን ላይ አምራች አርሶ አደሮች ሳይቀሩ ጥረትና ታማኘነቱን በመረዳታቸው በስልክ ግንኙነት እያደረገ ከማሳ ጭምር እየገዛ በማከፋፈል ላይ ይገኛል፡፡ ማህቶት የደረሰበት የአካል ጉዳት ከባድ በመሆኑ በእግሩ መራመድ ስለማይችል በእጁ ነው የሚሄደው፡፡ ሆኖም ግን ምን አይነት ድጋፍ ከሠው ስለማይፈልግ አሁን የተቀመጠበት ወንበር ላይ የወጣው ካለሠው እርዳታ ስለመሆኑ የዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ ምስክር ነው፡፡ ከአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችም ምርቶችን በቀጥታ መረከብ የሚችልበት ደረጃ መድረሱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ “ከአካል ጉዳተኝነቱ በላይ ፈተና የሆነብኝ የማህበረሠባችን ከንፈር የመምጠጥና ለጠየቀው ትቶ ላልጠየቀው ገንዘብ ለመጣል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው፡፡
በየሄድኩበት አካባቢ የዚህ አይነት አጋጣሚዎች ይገጥሙኛል፡፡ እኔ ግን ሠርቼ የምበላ ሠው እንደሆንኩ አስረድቼ ነው የምሄደው፡፡” ሲልም ይናገራል፡፡ “በአሁኑ ወቅት አማራ ክልል ላይ ግጭቶች በመኖራቸው አልፎ አልፎ በሚከሰቱ አለመረጋጋቶች በእኛ የአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው የስነ ልቦና ጫና በቀላሉ የሚገመት አይደለም” በማለት ሠላም እንዲወርድ ነው ወጣት ማህቶት ጥሪ ያቀረበው፡፡
More Stories
“ጥበብ ነገሮችን በተለየ መንገድ ማየት መቻል ነው” – ተወዛዋዥ ተስፋ ጽዮን ንጉሴ
ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!
“መሸነፍ አልፈልግም” – ወ/ሮ ጀሚላ መሀመድ