በአብርሃም ማጋ
የዛሬው ባለታሪካችን በመምህርነት ረጅም ዓመታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ መምህርነት እጅግ የተከበረ ሙያ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ የዚህች ዓለም ምስጢር ማሳያ መነፅርም መምህር ስለመሆኑ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡
ተመራማሪዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ ሐኪሞች፣ መሃንዲሶች፣ አውሮፕላን አብራሪዎች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ ሌሎችም ለህብረተሰቡ ወሳኝ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች የመምህር ውጤት ካልሆኑ ሌላ ከየትም አይመጡም ይላሉ፡፡
“መምህር አስተማሪ ብቻ ሳይሆን የአለም ብርሃን ፈንጣቂ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የተከበረ ሙያ ይዤ ካልተደሰትኩ ሌላ ምን ሊያስደስተኝ ይችላል” ሲሉም ይደመጣሉ፡፡
ይህ ታላቅ ደስታ የተሰማቸው ደግሞ ዛሬ ሳይሆን፣ ገና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘው ሥራ ለመቀጠር ዕጣ አውጥተው ሥራቸውን ለመጀመር እንደተሰናዱ ነው፡፡
በሙያው ውስጥ ሆነው ለረጅም ዓመታት ቆይተው በጡረታ ከተገለሉ በኋላም ተመልሰው በመምህርነት ሙያ በዩኒቨርስቲ መቀጠራቸውም ለሙያው ያላቸውን ፍቅር እንደሚያሳይ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
ዶ/ር ፍራንሷ ዳላቸው በወላይታ ዞን በሶዶ ዙሪያ ወረዳ፣ በሰሬዋሙሪ ቀበሌ በ1954 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ በአሁኑ ወቅት 62ኛ ዓመታቸው ላይ ይገኛሉ፡፡ የልጅነት አስተዳደጋቸው እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ቢሆንም ለየት የሚያደርጋቸው ነገር የአባታቸው ቀድመው ትምህርት መማር ነበር፡፡ አባታቸው የካቶሊክ ሚስዮን እምነት ተከታይና ሰባኪም ነበሩ፡፡ የትምህርትን ጥቅም ጠንቅቀው መረዳታቸውም የልጃቸው የትምህርት መስመር እንዲሰምር ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዶ/ሩ ቀደም ብለው ከተወለዱ ሴት ልጆች በኋላ መወለዳቸውና ከቤት ውስጥ የመጀመሪያ ወንድ ልጅ መሆናቸው ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጣቸው አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሳይቸገሩ በእንክብካቤ እንዲያድጉ አስችሏቸዋል፡፡
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በልጅነታቸው መማር ጀመሩ፡፡ በወቅቱ ገብተው መማር የጀመሩት በአካባቢያቸው በተከፈተ ትምህርት ቤት ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ተዘግቷል። የሚያስታውሱት ነገር ቢኖር በትምህርት ቤቱ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ መማራቸውን ነው፡፡
በቀጣይነትም ትምህርት ቤቱ ከ4ኛ ክፍል በላይ ስለማያስተምር ቀጣዩን ክፍሎች ለመማር ራቅ ያለ ቦታ ተጉዘው መማር ግድ ሆነባቸው። ከዚያም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስር ሆኃቴ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመባል በተሰየመ ት/ቤት ገብተው ከ5ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል፡፡
ት/ቤቱ ከመኖሪያ ቤታቸው የሁለት ሰዓት መንገድ ርቀት ያለው በመሆኑ በቀን የ4 ሰዓት መንገድ እየተመላለሱ ነበር የተማሩት፡፡ ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ደግሞ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ዱባ ቅድስት ማሪያም ት/ቤት ተምረዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥር የተከፈተ ነበር፡፡
የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ 9ኛ ክፍል መዛወራቸውን ተከትሎም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በወላይታ ሶዶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል፡ በ1971 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ሲያጠናቅቁ በብሔራዊ ፈተናም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ጥሩ ውጤት በማምጣት ነበር፡፡
በዚህም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ በመግባት በማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ በስነልቦና ትምህርት ክፍል ለአራት ዓመት ተከታትለው በ1975 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀል፡፡
በወቅቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች በቀጥታ በመንግስት ሥራ መቀጠራቸውን ተከትሎ በትምህርት ሚኒስቴር የመምህርነት እጣ ደረሳቸው፡፡ መምህርነቱን በጣም ሲመኙት ነበርና ደስታውን አልቻሉትም ነበር፡፡
ከዚያም በድሮው አጠራር ጋሞጐፋ ክፍለ ሃገር፣ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ምክርና አገልግሎት /ጋይዳንስ እና ካውንስለር/ ሐላፊ ሆነው ተመደቡ፡፡ ከኃላፊነታቸው ባሻገርም የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርትንም በተጓዳኝ ያስተምሩ ነበር፡፡
በጂንካ ሁለት ዓመት ካስተማሩ በኋላ በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተመድበው በተመሳሳይ ዘርፍ ለሁለት ዓመት ሠርተዋል፡፡ በመቀጠልም ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው አየር ጤና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ ቤት በተመሳሳይ ዘርፍ አገልግለዋል፡፡
በወቅቱ ሥራቸውን እየሠሩ እያሉ በ1979 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ለመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ምክትል ርዕሰ መምህራንን አወዳድሮ በደረጃ እድገት ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድረው በማለፍ በሮቤ መምህራን ማሰልጠኛ በሐላፊነት አዲስ ሥራ ጀመሩ፡፡
በዚህ መሃል በ1981 ዓ.ም የአንድ ዓመት የሙያ ማሻሻያ ትምህርት አግኝተው በጀርመን ሃገር ሰልጥነው ወደ ሮቤ ተመለሱ፡፡ ከዚያም በሮቤ መምህራን ማሰልጠኛ በምክትል ርዕሰ መምህርነት ለአንድ ዓመት ከሠሩ በኋላ፣ በ1982 ዓ.ም ከሐምሌ 1 ጀምሮ ወደ ሐዋሣ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተዛውረው ለ8 ዓመታት ያህል በምክትል ርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል፡፡
በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግስት በኢህአዴግ ሲተካ የተቋሙ ዋና ርዕሰ መምህር የነበሩት ሐላፊ በፖለቲካ ምክንያት ሲታሰሩ ዶ/ር ፍራንሷ ተተክተው በተጠባባቂ ርዕሰ መምህርነት ከ1984 ዓ.ም እስከ 1986 ዓ.ም ድረስ ተቋሙን መርተዋል።
ከ1989 ዓ.ም እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ የሐዋሣ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ወደ ኮሌጅ ደረጃ ሲያድግ በተጠባባቂ ዲንነት አገልግለዋል፡፡ ከዚያም በ1991 ዓ.ም ወደ አርባ ምንጭ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተዛውረው በዋና ርዕሰ መምህርነት ተመድበው እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ ለአራት ዓመታት ያህል ተቋሙን መርተዋል፡፡
በመቀጠልም በ1994 ዓ.ም ከየካቲት ወር ጀምሮ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በወጣት ጥፋተኞች ተሐድሶ ማእከል በሐላፊነት ተመደቡ፡፡ ሆኖም ተቋሙ ሥራው እንዲጀመር ስላልፈለገ ወደ አቅም ግንባታ በመዛወር የሴክተር ቢሮዎች ቡድን አስተባባሪ በመሆን ለአንድ ዓመት አገልግለዋል፡፡
በ1997 ዓ.ም ደግሞ እንደገና ወደ አርባምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ተዛውረው የአካዳሚክ ምክትል ዲን በመሆን ለአራት ወራት ካገለገሉ በኋላ የመንግስት ሥራን አቋርጠው በግል ኮሌጅ ውስጥ በዲንነት ተቀጠሩ፡፡
ኮሌጁም ሐዋሣ ዩኒየን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ሲሆን ለሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በ1999 ዓ.ም ከየካቲት ወር ጀምሮ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሥራውን ሲጀምር በመምህርነት ተቀጥረው ወደዚያው አቀኑ፡፡
ዶ/ር ፍራንሷ ከፍተኛ ትምህርት የመማር ፍላጐት ስለነበራቸው በ1992 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድጋሚ ገብተው በትምህርት እቅድና ሥራ አመራር ትምህርት ለሁለት ዓመታት ተከታትለው በሁለተኛ ዲግሪ /በማስተርስ/ ተመርቀዋል፡፡
በተጨማሪም ከ2004 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም እንደገና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በትምህርት አስተዳደርና ፖሊሲ ትምህርት 3ኛ ዲግሪያቸውን /ፒኤችዲ/ በማጠናቀቅ የዶክትሪት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም ላይ እድሜአቸው 60 ዓመት ደርሶ በጡረታ ቢገለሉም በሶዶ ዩኒቨርስቲ በመምህርነትና በተመራማሪነት በረዳት ፕሮፌሰር ማእረግ ተቀጥረው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
ዶ/ሩ ለሥራ ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹ፣ ሥራ የህይወታቸው ዋስትና መሆኑን ገልፀው ከፍተኛ ፍቅር እንዳላቸውም አበክረው ይናገራሉ። በመሆኑም ለበርካታ ዓመታት በኃላፊነት በሠሩባቸው ጊዜያት መመሪያና ደንብን ተከትለው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ መመሪያ ሰጪ ብቻ ሳይሆኑ ሠርተው የሚያሳዩ የአባትነት ባህርይ የተላበሱ መሪ ናቸው ሲሉም በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡
ከታች ካሉት ጀምሮ ሠራተኞቻቸውን አስተባብረውና አስማምተው በመካከላቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን አስወግደው የሚመሩ ሃላፊም ናቸው፡፡ ሠራተኞችን ከመቅጣት ይልቅ በምክር መመለሱ ልዩ ችሎታቸውና መለያቸውም ነው፡፡
ከተማሪዎችም ጋር ያላቸው ግንኙነት በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ከላይ ያሉ አለቆቻቸው ጋርም ያጋጠማቸው ችግር ብዙም እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡
በተቋማቸው ውስጥ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ ብዙ ጥረቶችን ያደርጋሉ፡፡ መምህራን በተቋማቸው ውስጥ ጥናትና ምርምር እንዲያካሂዱ ያበረታታሉ፡፡ ማበረታታቸውም ጥሩ ተግባር ለሚፈጽሙት እውቅና መስጠት፣ ወርክ ሾፖችን በማዘጋጀት ልዩ ስልጠና መስጠት …ወዘተ እንደሆኑም አብራርተዋል፡፡
ማህበራዊ ህይወታቸውን በተመለከተ ዝምተኝነት ያጠቃቸዋል፡፡ ከሰዎች ጋር በፍጥነት የመተዋወቅ ባህርይ አይታይባቸውም፡፡ ቀስ ብለው ይግባባሉ፡፡ አንዴ ከተግባቡ ግን ዘላቂ ጓደኝነት ይፈጥራሉ፡፡ የወረተኝነት ባህርይም በፍጹም አይታይባቸውም፡፡
በተለያዩ ማህበራዊ ህይወት በእጅጉ ይሳተፋሉ፡፡ በተለይም ሰዎች ሲቸገሩ በፍጥነት ደራሽ ናቸው፡፡ ለሰዎች ክብር የሚሰጡት በእድሜ፣ በፆታ፣ በሐይማኖት፣ በቀለም፣ በዘር ሳይለዩ ነው፡፡
በሠሩባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ ከ15 በላይ ሰርተፊኬቶችን በማግኘት እውቅና ማግኘታቸውን ከአንደበታቸውና ከሰነዶቻቸው መረዳት ችለናል፡፡
ለአብነት ያህል በዚምባብዌ ትምህርታዊ ጉብኝት አድርገው፣ ዩ ኤስ ኤይድ (USAID) ፕሮጀክት በማስተባበር፣ ሐየር ዲፕሎማ ፕሮግራም በመማር፣ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በንግድ ሥራ ትምህርት የተሰጣቸው ዲፕሎማዎችና ሰርተፊኬቶች ካገኟቸው እውቅናዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ስለመምህርነት ሙያ ያላቸውን አስተያየት ተጠይቀው፡-
“መምህር ሁሌ ተማሪ ነው፡፡ ሁሌ ማንበብ አለበት፡፡ ንባብ ደግሞ የእውቀት ጐተራ ያደርጋል። እውቀት ደግሞ የዚህ ዓለም ሚስጢር መክፈቻ ቁልፍ ነው፡፡ በተጨማሪም መምህርነት የሰላማዊና የተረጋጋ ህይወት መፍጠሪያ ሐይል ነው፡፡ እንደገናም ወጣትነትም ነው” በማለት ያብራራሉ፡፡
በዚህ መነሻ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ እጣ ሲያወጡ የመምህርነት ሙያ ሲደረሳቸው በእጅጉ የተደሰቱት፡፡ አሁንም ጡረታ ከወጡ በኋላ ተመልሰው ወደ ሙያው ገብተው ማስተማር የመጀመራቸው ምስጢርም ለሙያው ካላቸው ፍቅር እንደሆነም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
ዶ/ር ፍራንሷ ወደ ትዳር ዓለም የገቡት በ1983 ዓ.ም ሲሆን 3 ልጆች አፍርተዋል፡፡ ሶስቱም ልጆቻቸው በጥሩ የትምህርት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው