“እንደ ስደት አስከፊ ነገር የለም” – ወጣት ቤዛ ሌሞ

በአስፋው አማረ

በዓለማችን በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች የስደት ሕይወት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ በተለይም አህጉራችን አፍሪካ ሁለት ዓይነት ስደትን ታስተናግዳለች፡፡ አንደኛው በጦርነት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ የተሻለ የሥራ ዕድሎችን ፍለጋ በማስብ የሚደረግ ስደት፡፡ በዛሬው የእቱ መለኛ ጥንቅራችን እራሷንና ቤተሰቦቿን ለመቀየር የተሻለ ሥራ ፍለጋ ስደትን እንደ አማራጭ አድርጋ የሕይወትን ሌላ መልክ ስላየች እንስት ተሞክሮ በአጭሩ በማንሳት ሌሎች ከእርሷ እንዲማሩ ላጋራችሁ ወድጃለሁ፡፡

ወጣት ቤዛ ሌሞ ትባላለች፡፡ የተወለደችው በወላይታ ዞን አረካ ከተማ ነው፡፡ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን በአዲማንቾ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡ ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ደግሞ በአዲማንቾ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቃለች፡፡ ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ እራሷን ለመለወጥ የተለያዩ ሥራዎችን ሰርታለች፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር የመቀየር ውጥንን አስባ ወደ ስደት የገባችው፡፡

ወደ አረብ ሀገር የተሰደደችበትን አጋጣሚ ስታወጋን፦

“አረካ ከተማ ላይ ወደ አረብ ሀገር ሄደው ሥራ ሰርተው እራሳቸውን የቀየሩ ልጆች መኖራቸውን እሰማ ነበር፡፡ እኔም ወደ አረብ ሀገር በመሄድ እራሴንና ቤተሰቦቼን ለመለወጥ ማሰብ ጀመርኩ። ከዚያም ለጉዞ የሚያስፈልገኝ ፓስፖርት ሀዋሳ በመሄድ አወጣሁኝ፡፡ ፓስፖርቴን ከያዝኩ በኋላ የጉዞ ብር ያስፈልገኝ ነበር፡፡ ለጉዞ የሚያስፈልገኝን ብር በቀላሉ ማግኝት ግን አልቻልኩም፡፡ በዚህም ምክንያት ለትራንስፖርት የሚሆን ብር ውጭ ሀገር ሄጄ ሥራ ሰርቼ ብድሩን የምመልስለት ሰው ፈለኩኝ፡፡ ከዚያም 19 ሺህ ብር ተበድሬ ለመጓዝ ተነሳሁ ትላለች፡፡

“ከዛም ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በመሆን ጉዞ ጀመርን፡፡ የጉዟችን ጅማሮ የሆነው ከአረካ በመነሳት መጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ ነው የሄድነው፡፡ በመቀጠል ከአዲስ አበባ በመነሳት ከሁለት ቀናት ጉዞ በኋላ ጎንደር ገባን፡፡ ጎንደር ሁለት ቀን ያህል ካሳለፍን በኋላ ለጉዞ ተዘጋጁ ተባልን፡፡

“በለሊት ከጎንደር ተነሳንና ወደ መተማ መጓዝ ጀመርን፡፡ ከረጅም ጉዞ በኋላ መተማ ከተማ ገባን፡፡ መተማ ከተማ ላይ አንድ ቀን ካደርን በኋላ ወደ ገላባት አነስተኛ ከተማ ተጉዘን ገባን። የህገ ወጥ ስደት ስቃይ አስከፊነት የሚጀምረው ከዚህ በኋላ ነበር” ስትል የስቃይ ምዕራፍ ሀ ብሎ የሚጀምርበትን ቦታ ታስታውሳለች፡፡

ገለባት ከተማ ከገቡ በኋላ የስደት መራራ ጽዋ መጎንጨት እንደጀመሩ የምትናገረው ወጣት ቤዛ በከተማው የነበረው ከፍተኛ ሙቀት፣ የምግብ አለመስማማት፣ ውሃ ጥማት እና የማደሪያ ቦታ አለመመቸት ላይ ሌሎች በርካታ ችሮች መጋፈጣቸውን ታነሳለች፡፡ በዚህ ሁኔታ ሶስት ቀን ለማሳለፍ መገደዳቸውንም ትናገራለች፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነው ከገላባት በመነሳት ጎዟቸውን ወደ ሱዳን ያደረጉት፡፡ በመንገድ ላይ በርከት ያሉ ፍተሻዎችን በማለፍ ወደ ሱዳን መግባት ቢችሉም በጉዞ ወቅት የገጠማቸው ችግር ተነግሮ እንደማያልቅ ታወሳለች፡፡ ይህ ጉዞ የሚደረገው ደላሎች በዘረጉት መስመር መሆኑ ደግሞ ለእንግልቶቹ ምክንያት እንደሆነም አጫውታኛለች፡፡

ሱዳን ከገቡ በኋላ ለስድስት ቀን ያህል በድብቅ ቆይተዋል፡፡ እነሱ ሲገቡ የሱዳን ሙቀት ከፍተኛ መሆኑ ከነበረው የምግብ አቅርቦት እጥረት ጋር ተደማምሮ በርሃብና ሙቀት የተፈተነ ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ ምክንያቱም ደግሞ እሷና ጓደኛዋ ህገ ወጥ ስደተኞች ስለነበሩ እንደፈለጉ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው ነበር፡፡

“መቼም አንዴ ከሃገር ስለወጣን እንጂ በቀላሉ መመለስ ቢቻል ሃገሬ ማሪኝ ብዬ እመለስ ነበር” ስትልም ሁኔታው ከሚታሰባው በላይ ከባድ እንደነበር ታስረዳለች፡፡

ከሱዳን ወደ ቤሩት የሄዳቹበት አጋጣሚ እንዴት ነበር? ብዬ ላነሳሁላት ጥያቄ ምላሽ ስትሰጥ፦

“በሱዳን ከስድስት ቀናት ቆይታ በኋላ የቤሩት ቪዛ መጣልን፡፡ ከዚያም ወደ ቤሩት በረራ አደረግን፡፡ የስደት ችግሩ ሁሌም ይከተልሀል፡፡ እዚህ ምድር ላይ እንደ ህገ-ወጥ ስደት አስከፊ ነገር የለም፡፡ ቤሩት ከደረስኩኝ በኋላ እኔን ካስመጣችኝ ቀጣሪዬ ጋር መስራት ጀመርኩ፡፡ ይሁን እንጂ ያለሷ ፍቃድ የትም መንቀሳቀስ አለመቻሌ ሌላ ፈተና ሆኖብኝ ነበር፡፡

“ሥራ የምታሰራኝ ሴትዮ(ማዳም) እኔ ሌላ ቦታ ሄጄ እንድሰራ አትፈልግም፡፡ በዚህም ምክያት በእኔና በአሰሪዬ መካከል አለመግባባቶች ተፈጠሩ። እኔ ደግሞ ወደ ቤሩት የገባሁት በሱዳን በኩል ስለነበረ ‘ወደ ሀገርሽ መሄድ ከፈለግሽ የሱዳኖችን ስልክ ቁጥር ስጭኝ እደውልላቸውና ይወስዱሻል ስትል አስፈራራችኝ፡፡ እኔ የፈለኩት ሌላ ቤት ተቀጥሬ መስራት ስለነበር ስልክ ቁጥሩን መስጠት አልፈለኩም፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ የስቃይ ጊዜያቶችን ለማሳለፍ ተገደድኩ፡፡ በተለይም አንድ ዓመት ከአራት ወር ያለ ምንም ስልክ ግንኙነት ቤተሰቦቼን ስላገኝ በማሳለፍ በሕይወቴ ከባድ የሆነውን ወቅት ተጋፈጥኩ፡፡ ይህንን ሁሉ በትግስት ያሳለፍኩት እራሴንና ቤተሰቦቼን ለውጣለሁ በሚል ተስፋ ነበር፡፡

“በመጨረሻም የኢትዮጵያዊያኖችን ቢሮ ስልክ ቁጥር አገኝሁና ስልክ በመደውል አድራሻቸውን ተቀብዬ ወደ ቢሯቸው ሄድኩ። ወደ ሌላ ቤት እንዲቀይሩኝም ጠየኳቸው። እነሱም እንደማይቻል አስረዱኝ፡፡ አንዳንዴም መደብደብና ስድብ ሁሉ እንደሚያጋጥም በማስረዳት እንድመለስ አደረጉኝ፡፡

“ያለሁበትን ሁኔታ በአስተርጓሚ ጭምር በተደጋጋሚ ባስረዳም ከአሰሪዬ ጋር ተነጋገሩና ምንም በማላውቅበት ሁኔታ በድንገት በ2009 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መለሱኝ” ስትል ወደ ሀገሯ የተመለሰችበትን ሁኔታ አጫውታኛለች፡፡

ነገር ግን አሁንም የእኔንም ሆነ የቤተሰቦቼን ኑሮ መቀየር የምችለው አረብ ሃገር በመሥራት ነው የሚል እሳቤ ውስጤ ስለያዘ ለዳግም ስደት እራሴን አዘጋጀሁ፡፡ በዚህም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ቤሩት ለማምራት ተዘጋጀሁ፡፡ ነገር ግን ወደዛ ስታመራ ሁኔታዎች ከዚህ ቀደም እንደነበረው በችግር የተሞላ አለመሆኑን ትናገራለች፡፡

ለዚህም ምክንያቱ ህጋዊ ሂደትን የተከተለ ጉዞ መምረጧ መሆኑን ታስረዳለች፡፡ እዛም ቢሆን የነበረው ሁኔታ እና ሥራ ቀላል እንዳልነበረ ትናገራለች፡፡ ቢሆንም ግን “መብቴ ተከብሮ የምሰራበት ሁኔታ በመፈጠሩ እራሴንና ቤተሰቦቼን የምለውጥበ ጥሪት በመያዝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመመለስ አቅዳ መሄዷን ታስረዳለች፡፡

“አንዳንዴ አሰሪዎች (ማዳሞች) ደሞዛችንንም የሚከለክሉበት ሁኔታ አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምንዛሬው ዝቅተኛ የሚሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል። እነዚህ ሲደማመሩ ያሰብነውን ሀሳብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት እንቸገራለን፡፡ ከዚህም የተነሳ ሳላስበው አምስትና ስድስት ዓመት ለመቆየት ተገደድኩ፡፡

ይሁን እንጂ ደላሎች የሚነዙት የተሳሳተ መረጃ ብዙዎችን ከመንገድ ማስቀረቱን በማንሳት ከእኔ ተማሩ ስትል ተሞክሮዋን ታጋራለች፡፡ “አሁን ላይ ደላሎች ዱባይ ሄዳችሁ ሥራ ትሰራላችሁ እያሉ ያታልላሉ፡፡ ነገር ግን የሚልኳቸው ቤሩት ነው። ቤሩት ያለችበት ሁኔታ ደግሞ ጥሩ ባለመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ስትል ትመክራለች፡፡

በመሆኑም አንድ ሥራ ለመሥራት ወደ አረብ ሃገር መሄድ የሚፈልግ ሰው መጓዝ ካለበት መንግስት የሚያመቻቸውን ህጋዊ መንገድ ተከትሎ መሆን አለበት ስትልም በአፅንኦት ታነሳለች፡፡ በተለይም ወደ አረብ ሀገር የሚደረግ ስደት ብዙ ፈተናዎች ያሉበት በመሆኑ አስፈላጊውን የስነ- ልቦና ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ከተሞክሮዋ በመነሳት ትመክራለች፡፡

አሁን ላይ በህገ ወጥ መንገድ ከመሰደድ ይልቅ ሃገር ላይ ሰርቶ መለወጥ የሚያስችል ሁኔታ በመኖሩ ያለውን ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም መንቀሳቀስ ከወጣቶች ይጠበቃል ትላለች፡፡

“አንድ ሰው በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ወጥቶ ሲሄድ ከእንግልቱ ሁሉ የሚከፋው እጁ ላይ ያለው ገንዘብ ከተዘረፈ መንገድ ላይ የሚቀርበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህም ነገሩን ከድጡ ወደማጡ በማድረግ የበረሃ ሲሳይ እንድትሆን ያደርጋል፡፡ ችግሩ በዚህ ብቻ አያበቃም የምትለው ወጣት ቤዛ ከቤተሰቦቻቸው የሚያስልኩበትም ሁኔታ አለ፡፡

ከዚህም የሚከፋው ደግሞ በህገ-ወጥ ጉዞ ወቅት እስከ ህይወት መስዋትነት የሚያስከፍል ሁኔታ ስለሚያስከትል በህገ ወጥ መንገድ ስደት የሚያስቡ ወገኖች ካሉ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል ስትል ትመክራለች፡፡