በመሐሪ አድነው
በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን የመሠረተ ልማት አውታር ግንባታ አለመኖርና የአገልግሎት አሠጣጥ ጉድለት በርካቶችን ለእንግልትና የጤና ችግር እየዳረጋቸው እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ይህም አካል ጉዳተኞች በማህበረሰቡ መካከል ተገቢውን እንክብካቤ እንዳያገኙና በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ እንዲያልፉ አድርጓቸዋል።
በሀገራችን ከ23 እስከ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጐች ከተለያየ ዓይነት የአካል ጉዳት ጋር እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ በርካታ ፈተናዎችን እንዲያልፉ ቢገደዱም የገጠማቸውን ችግር በትዕግስትና በብርታት አልፈው ለሌሎች አርዓያ መሆን የቻሉ አካል ጉዳተኞች ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡
ዶ/ር ወይንሸት ግርማ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ጐላ ሚካኤል በሚባል አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም እዚያው ነው የተማሩት፡፡
ዶ/ር ወይንሸት የ13 ዓመት ልጅ እያሉ በአካባቢው ተከስቶ በነበረ የማጅራት ገትር ወረርሽኝ በሽታ ተይዘው በነበረበት ጊዜ ነው መስማት የተሳና ቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ መስማት የተሳናቸው ሠዎች የጉዳታቸው መንስኤ ማጅራት ገትር የሚባለው በሽታ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
አብሮ ያልተፈጠረና ከጊዜ በኋላ የሚመጣ ጉዳትን አምኖ ለመቀበል ጊዜ ይወስዳል፡፡ ዶ/ር ወይንሸት በ1990ዎቹ አጋማሽ የ8ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ በደረሰባቸው ህመም መሰማት ተሳናቸው፡፡ እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ እየሰሙ ተምረው ከዚያ በኋላ መስማት ሲሳናቸው ይህን ተቀብሎ ለማስተናገድ ከብዷቸው ነበር፡፡
ነገር ግን መለወጥ የማይቻል ነገር መሆኑን ሲገነዘቡ አምነው ለመቀበል ራሳቸውን አሳመኑ፡፡ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሠዎች አብዛኛውን ጊዜ መስማት ብቻ ሳይሆን መናገርም ይሳናቸዋል፡፡ ዶ/ር ወይንሸት ግን እንደ እድል ሆኖ የመስማት እንጂ የመናገር ችግር ከትናንሽ መደነቃቀፍ ያለፈ አልደረሰባቸውም፡፡
በዚያ ምክንያት የምልከት ቋንቋ መማር ጀመሩ፡፡ በዚህ መልኩ እየተማሩ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገቡ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሥነ ልሳን ትምህርት በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቁ፡፡ ውጤታቸው ከፍተኛ ስለነበር ዩኒቨርሲቲው አስቀርቷቸው እዚያው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አሁንም በጥሩ ውጤት አጠናቀው በዩኒቨርሲቲው ማስተማራቸውን ቀጠሉ። የትዳር አጋራቸውንም ያገኙት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ የትዳር አጋራቸውም መስማት የተሳናቸው ናቸው፡፡
የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በኖርዌይ ኦስሎ ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው ነበር ያጠናቀቁት፡፡ ዶ/ር ወይንሸት አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት ታዲያ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አይደለም፡፡
ከጊዜ በኋላ ያጋጠማቸውን የአካል ጉዳት ተቀብለው ለመዝለቅ ከነበረው የስነ ልቦና ጫና በላይ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም ሃገር ውስጥ ባሉት ትምህርታቸውን ለመከታተል የነበረው ያልተመቻቸ ሁኔታ በቀላል የሚገለፅ ችግር አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምንም እንኳን ትልቅ ተቋም ቢሆንም መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች አስተርጓሚ አላዘጋጀም ነበር፡፡
አንዳንድ ተማሪዎች የራሳቸውን አስተርጓሚ ይዘው ለመግባት ጥረት ቢያደርጉም አስተርጓሚዎቹ በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ላይ የሚኖራቸው እውቀት ውሱን ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የአካል ጉዳተኞችን መብት ከማስከበር አንፃር የሚታይ ክፍተት ነው፡፡ ዶ/ር ወይንሸትም በህይወቴ ካጋጠሙኝ ፈተናዎች ከባዱ ነው የሚሉት ይህንኑ ነው፡፡
የማጅራት ገትር በሽታ በተወሰነ ደረጃ ህክምና በቶሎ ስላገኙ ንግግራቸው ላይ ብዙም ጉዳት አልደረሰም፡፡ በመሆኑም ሲያወሩ ለሚያያቸው ሠው ጆሮዋቸውም የሚሰማ ነው የሚመስለው፡፡ ከዚህ አንፃር አልሰማም ቢሉም የሚያምናቸው የለም፡፡
ይህ ደግሞ ከወደ ማህበረሰቡ በኩል ያለው ተግዳሮት ነው፡፡
ዶ/ር ወይንሸት ወደ ሥራው አለም ሲገቡ በርካታ ውጣ ውረዶችን ተሻግረው ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርነት ባሻገር ሥራ የጀመሩት በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ነበር፡፡ ማህበሩ በኢትዮጵያ ወደ 36 ቅርንጫፍ ማህበራት አሉት፡፡
ከዚያ በኋላ ደግሞ ከፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በነበረው ትልቅ ፕሮጀክት ላይ የብሔራዊ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በሴቶች አቅም ግንባታና በአካል ጉዳተኞች በተለይም መስማት የተሳናቸው በመረጃ ተደራሽነት እጥረት ምክንያት ለበሽታና ለአደጋ እንዳይጋለጡ በትኩረት የሚሠራ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ዶ/ር ወይንሸት መስማት ከተሳነው ባለቤታቸው እና ሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በከፈቱት ሆፕ ፎር ዴፍ አሶሴሽን (Hope for deaf association) በሚባል ማህበር ዳይሬክተር በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ማህበሩ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መብት ጥበቃ ላይ ነው።
ከዚህም ጐን ለጐን የአዲስ አበባ አጠቃላይ አካል ጉዳተኞች ማህበር ሠብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
“የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ በሃገራችን እምብዛም ተግባራዊ እየሆነ አይደለም፡፡ አካል ጉዳተኛ ምንም ያህል የትምህርት ዝግጅት ቢኖረውም በሙያው እንደ ልብ ሠርቶ የሚኖርበት የተመቻቸ ሁኔታ የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ አካል ጉዳተኞች ወደ ውጭ ሃገር የሚሄዱበትን አጋጣሚ ይፈልጋሉ፡፡ ባለቤቴም ኑሮውን በውጭ ሃገር ያደረገው በዚሁ ምክንያት ነው” ይላሉ፡፡
በሃገራችን አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ማህበረሰቡ አካል ጉዳተኛ ሲባል እንደማንኛውም ሠው ተምሮ እንደሚለወጥ፣ ሠርቶ መብላት እንደሚችል የተቀበለው አይመስልም፡፡ ይህንን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት በማህበራቸው በኩል በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ አንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሃገራችን የተለያዩ የአካል ጉዳተኛ መብቶች ስምምነት ፈርማለች፡፡ ሆኖም ግን ተግባራዊ እየሆነ ነው ለማለት አያስደፍርም። እንደዛም ሲባል የተጀማመሩ ጥረቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡
ጤና ጥበቃ፣ ትምህርት ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አካል ጉዳተኞች አብዛኛውን ጊዜ ወደ ልመና ሲገቡ ይታያሉ፡፡ በአንድ በኩል ሲታይ ግን ማህበረሰቡ ለእነርሱ ምን አቀረበ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከወላጅ ጀምሮ አካል ጉዳተኛ ልጁን ተምሮ መለወጥ ይችላል፣ ሠርቶ መኖር ይችላል ብሎ ማመን አለበት የሚሉት ዶ/ር ወይንሸት ወላጆች አካል ጉዳተኞችን ወደ ት/ቤት አያመጧቸውም፡፡ ስለዚህ ሳይማሩ እንደምንም ብለው ያድጋሉ፡፡ ካደጉስ በኋላ ሥራ የሚሰጣቸውስ ማን ነው? የዶ/ር ወይንሸት ጥያቄ ነው፡፡
በመሆኑም ለመኖር ሲሉ የሚለምኑበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሚታይ አካል ጉዳት ያለባቸው ሠዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሠዎች ምናልባትም ትልቅ ተቋምና ድርጅት የሚመሩ ሊሆኑና ጥሩ ኑሮ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ነገር ግን ቤተክርስቲያን በራፍ ለፀሎት ሲሄዱ ማህበረሰቡ ሣንቲም ለመስጠት ይሞክራል፡፡ ማህበረሰቡ አካል ጉዳተኞች ሠርተው መብላት አይችሉምና መርዳት አለብን የሚል አመለካከት እንዳለው ማሳያ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ለልመና ያበረታታል፡፡
ማህበራቸው አካል ጉዳተኞች ወደ ሥራ እንዲገቡ አጫጭር ሥልጠናዎችን እየሠጠ የሚገኝ ቢሆንም ይህ ነገር በዋና ዋና ከተሞች እንጂ ገጠር አካባቢ እየተዳረሰ ባለመሆኑ ቀጣይ ስራዎች እንዳሉም ይናገራሉ፡፡
ዶ/ር ወይንሸት እንዳሉት አሁን ላይ ትግል እየተደረገ የሚገኘው አካል ጉዳተኛው በሞግዚትነት ከሚተዳደርበት ሁኔታ ተላቆ እራሱ አካል ጉዳተኛው የሚመራው ተቋም በአዋጅም ይሁን በሚኒስቴር ደረጃ እንዲቋቋምና የአካል ጉዳተኛውን ጉዳይ የሚመለከት ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖር ነው፡፡
እንደዚያ ቢሆን የአካል ጉዳተኛው መብት በአግባቡ ይከበራል፡፡ “እኛም መብታችን አልተከበረም ይሄ ጐደለብን ብለን ሁልጊዜ ጣታችንን ወደ መንግስት አንጠቁምም፡፡ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ተቋሙ ሃላፊነት ይወስዳል፤ መንግስትም ከወቀሳ ይድናል” ባይ ናቸው ዶ/ር ወይንሸት፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው