“የምርምር ሥራዎች የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው” – ዶክተር ፀጋዬ ማቴዎስ

“የምርምር ሥራዎች የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው” – ዶክተር ፀጋዬ ማቴዎስ

የዛሬው የንጋት እንግዳችን ዶክትር ፀጋዬ ማቴዎስ ይባላሉ፡፡ የሻሎም ቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ከባለሙያነት እስከ ኃላፊነት ቦታዎች ከ16 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ በኮሌጁ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ፣የምርምር ስራዎች እና የህብረተሰቡን ችግር ፈቺ አገልግሎት በሚሉ ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በገነት ደጉ

ንጋት፡- በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ዶክተር ፀጋዬ ፡- እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ትውልድ እና እድገትዎን ቢያስተዋውቁን?

ዶክተር ፀጋዬ፡- ተወልጄ ያደኩት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በምትገኘው ወንዶ ገነት ከተማ ነው፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በወንዶ ገነት ወሻ አትክልት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተልኩት፡፡

እዚያው ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ከተፈተንኩ በኋላ ጥሩ የማለፊያ ውጤት በማምጣት በወቅቱ በአካባቢው ላይ የ2ኛ እና የመሰናዶ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ሀዋሳ መጥቼ ትምህርቴን ለመከታተል ችያለሁ፡፡

ቤተሰቦቼም ለትምህርት ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ እና ጥሩ ቦታ እንድንደርስ ፍላጐት ስለነበራቸው እኔን፣ ወንድምና እህቶቼን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሀዋሳ ላይ ቤት ገዝተው ነው ያስተማሩን፡፡

ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል አዲስ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትያለሁ፡፡

ንጋት፡- የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና ውጤትዎ እንዴት ነበር?

ዶክተር ፀጋዬ፡- የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና(ማትሪክ) ሲወስድ በለስ ሳትቀናኝ ቀረሁና የተሻለ ውጤት ማምጣት አልቻልኩም፡፡

በትምህርቴ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ፡ ፡ የተፈጠረውን ነገር እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ ማወቅ ግን አልቻልንም፡፡

ቤተሰብ እንደገና እናስተምረው ሲሉ እራሴ አጥንቼ እፈተናለሁ በሚል ቤተሰቦቼ ጋር ወደ ወንዶ ገነት ከተማ በመሄድ ትኩረት ሰጥቼ ማጥናት ጀመርኩ፡፡

በወቅቱ ወንዶ ገነት ደን ኮሌጅ ደቡብ ዩኒቨርሲቲ በሚባልበት ወቅት የግዥ እና ንብረት አስተዳደር ማስታወቂያ ወጥቶ ስለነበር ጎን ለጎን እየሰራሁ ለምን አላጠናም በሚል ከ52 ተማሪዎች ጋር ተወዳድሬ 1ኛ በመውጣት ዕድሉን አገኘሁ፡፡

እዛውም በሚከፈለኝ ደመወዝ ብዙ መቆየትን አልፈለኩም፡፡ ከሶስት ዓመት ተኩል በኋላ ደቡብ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሲቀየር ወደ ሀዋሳ በመምጣት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ1996 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ቋሚ ሰራተኛ በመሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ ስራዬን ጀመርኩ፡፡

በስራ ጠንቃቃ ስለነበርኩ በአስቸኳይ ወደ ፋይናንስ እንድመጣ ተደርጌ የሂሳብ ሰነድ ያዥ በመሆን ቆየሁ፡፡ በኋላም የኦዲት ክፍል ተወካይ በመሆን ስሰራ ቆይቼ በቢፒአር ከፍተኛ ኦዲተር በመሆን አዲስ መደብ ላይ ስራዬን ቀጠልኩ፡፡

ንጋት፡- የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና ወይም ትምህርትዎ እንዴት ሆነ?

ዶክተር ፀጋዬ፡- የ12ኛ ክፍል ፈተና ወስጄ ባመጣሁት ውጤት እዚያው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪ እንዲሁም በቢዝነስ ማኔጅመንት ሁለተኛ ድግሪዬን ደግሞ በማርኬትንግ ማኔጅመንት ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቼ ተምሬያለሁ፡፡

በወቅቱ በዩኒቨርሲቲ አካባቢ ያሉ ሰዎች በህንድ ሀገር የውጪ የትምህርት ዕድል በቀላሉ እንደሚያገኙ መረጃ ስለነበረኝ ተፃፅፌ በህንድ ሀገር የትምህርት ዕድል አገኘሁ፡፡ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የድጋፍ ደብዳቤ ለመፃፍ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በግሌ ሞከርኩ እና ተሳክቶልኝ ወደ ህንድ ሀገር ለፒኤችዲ ሄድኩ፡፡

በኋላም ግማሽ ክፍያ ከራስ ተብሎ ሲጠየቅ በህንድ ሀገር በሚገኘው ሁጅራ በእስፖንሰር ሽፕ ፓሮል ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓትም ወደ 54 ሺ የሚሆኑ ተማሪዎችን ያያዘ ግዙፍ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

ትምህርቴን መከታተል ስጀምር በትምህርት ላይ ያለኝን ዝንባሌ እና ችሎታ በማየት በዩኒቨርሲቲው ነፃ የትምህርት እድል ተሰጠኝ፡፡

ለሶስት ዓመት ተኩል ትምህርቴን ስከታተል ቆይቼ በጥሩ ውጤት ተመርቄ ወደ ሀገር ቤት ተመለስኩኝ፡፡

ሶስተኛ ድግሪን (PHD) በማርኬትንግ ማኔጅመንት የጨረስኩ ሲሆን በወቅቱ ሪሰርች በሆቴል ኢንዱስትሪ፣ በባንኮች እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ነበር የሰራሁት። ሪሰርቼ በዓለም ጆርናሎች ላይ ተመራጭ በመሆን ዌብ ኦፍ ሳይንስ ላይ ታትሞልኝ በመውጣት ትምህርቴን ልጨርስ በቅቻለሁ፡፡

ንጋት፡- ትምህርትዎን ጨርሰው ሲመለሱ በመምህርነት ሙያ ለመቀጠል ያልፈለጉት በምን ምክንያት ነበር?

ዶክተር ፀጋዬ፡- በወቅቱ መምህርነት ትልቅ ሙያ ቢሆንም በመምህርነት ግን ልቀጥል አልፈለኩም፡፡ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ጥሩ ተከፋይ እንደማያደርግ ስለተረዳሁ የግል ትምህርት ቤት ከቤተሰቦቼ ጋር በመተጋገዝ ኮሌጅ ለምን አንከፍትም በሚል ነበር ማስተማር ያልፈለኩት፡፡

በወቅቱ የገንዘብ አቅም አልነበረኝም፤ ነገር ግን ሞራሉ ነበረኝ፡፡ ቤተሰቦቼን በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግን አላልፍም፡፡ በእጃቸው ያለውን ገንዘብ በሙሉ በመሥጠት ነበር ኮሌጅ እንዲከፈት የረዱኝ፡፡

ንጋት፡-የኮሌጁ ተልዕኮ እና ራዕይ ምንድ ነው?

ዶክተር ፀጋዬ፡- በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠሩ 20 ኮሌጆች መካከል ለመግባት ትልቅ ራዕይ ሰንቀን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ አሁን ተከራይተን ከምንሰራበት ህንፃ በተጨማሪ ትልቅ ጊቢ ኖሮን ጥራት ያለው ትምህርት ማስፋት ነው ራዕያችን፡፡ ከዚህም ባለፈ ኮሌጁን ዩኒቨርሲቲ አድርገን ትልቅ ግቢ ኖሮን የመማር ማስተማር፣ ምርምር እና የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች አካተን ለመስራት ይህንን ራዕይ ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ንጋት፡- ኮሌጁ ከትምህርት ጥራት አንፃር እየሰራ ያለው ስራዎችን እንዴት ይገለፃል?

ዶክተር ፀጋዬ፡- የትምህርት ጥራትን ጠብቆ ተማሪዎችን በተገቢው ሁኔታ ከማስመረቅ አንፃር ጥሩ ተሞክሮ አለ ብለን ነው የምናስበው፡፡

ተማሪዎችን ስንመዘግብ የአግባብነት ኤጀንሲ መመሪያዎችን መሰረት አድርገን፣ ውጤታቸውን በአግባቡ በማየት ነው የምንቀበለው፡፡ የሁለተኛ ድግሪ ተማሪዎችን በፈተና አወዳድረን ነው የምንቀበለው፡፡

ለቀን ተማሪዎች ከሰኞ እስከ አርብ ጥዋትና ከሰዓት፣ ለማታ ተማሪዎች ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ማታ ማታ እያስተማርን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎችን ለማብቃት የተለያዩ ትምህርት ተኮር የሆኑ የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት ሰርትፍኬት እንሰጣችኋለን፡፡

ከዚህም ባለፈ በዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ አካዳሚክ እና ኢንተርናሽናል ኮንፈረንስ በማድረግ እንታወቃለን፡፡

በአካዳሚክ ኮንፈረንስ የተገኙ በየዓመቱ ስምንት ጆርናሎችን ወይም ለውድድር ቀርበው ያሸነፉ ስምንት ሪሰርቾችን ለተመራማሪዎች ወይም ለተገልጋዮች በኦን ላይን በዌብ ሳይታችን ላይ ለቀናል፡፡ ማንም ሰው እንዲጠቀምበት አሳትመናል፡፡

ንጋት፡- ኮሌጁ የሚሰጣቸው የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እንዴት ይገለፃል?

ዶክተር ፀጋዬ፡- በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች ብዙ ተሞክሮ ያላቸው የግል ኮሌጆች አሉ፡፡ ከእነዚያ መሀል ነን፡፡ እኛ በቀበሌ በኩል ያሉ በሀዋሳ ሜሪ ጆይ አረጋዊያን መርጃ ማዕከልን፣የጎዳና ተዳዳሪዎችን ማገዝ በበዓላት በመመገብ እንዲሁም በሲዳማ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ በመሳተፍ እስከ ይርጋለም ከተማ ድረስ በመሄድ ሁለት ዓመት አሳክተናል፡፡

የወደቁ ትምህርት ቤቶች እና ሽንት ቤት የሌላቸውን በመጠገን /በአዲስ አበባ ቀበሌ አንድነት ትምህርት ቤት በአካል በመገኘት/ የበኩላችንን አድርገናል፡፡

ንጋት፡- ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች ከመስራት አንፃር ምን እየተሰራ ነው?

ዶክተር ፀጋዬ፡- ወደፊት ብዙ አቅደናል፡፡ አንድ ሪሰርች የሰራነው በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ ክፍለ ከተማዎች በውስጣቸው ያሉ ጀማሪ ቢዝነስ ሰራተኞችን ለቅመው እንዲሰጡን አድርገን በእነርሱ ላይ አንድ የምርምር ስራ ሰርተናል፡፡

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ስራ ጀምረው ያቆማሉ፡፡ እነዚህን ነገሮች ተከታትለን በክፍለ ከተማው ካጠናን በኋላ ውጤቱን ለክፍለ ከተማው በጽሑፍ አቅርበን እነሱም ሰባ የሚሆኑ ሰልጣኞችን ሰጥተውን አሰልጥነን ወደ ቢዝነሳቸው እንዲመለሱ አድርገናል፡፡

ይህም ስራ ጅምር እንደመሆኑ በቀጣይም በርካታ የምርምር ስራዎች የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው፡፡

ንጋት፡- ከአቻ ተቋማት ጋር ያለው የልምድ ልውውጥ እና ትስስር ምን ይመስላል?

ዶክተር ፀጋዬ፡- ከአቻ ተቋማት በተለይም ሀዋሳ ውስጥ ካሉት ጋር በጎ ቅርርብ ነው ያለን፡፡ በሚያስፈልገንም ይሁን በሚጎድለን ነገር እርስ በርስ እንተጋገዛለን፡፡ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ልውውጥ፣ የአካዳሚክ ኮንፈረንስና የሪሰርች ጉባኤዎች ሲኖሩ እንጋብዛቸዋለን፡፡ በዚህም መልኩ ከአቻ ተቋማት ጋር በቅርበት እንሰራለን፡፡

ንጋት፡- ኮሌጁ ቴክኖሎጂን ወይም አሰራርን ከማዘመን አንርፃር ምን እየሰራ ነው?

ዶክተር ፀጋዬ፡- ኮሌጁን በቴክኖሎጂ ከማዘመን ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎች ሁለት የኮምፒዩተር ላቦች በኔት ወርክ እንዲተሳሰሩ አድርገናል፡፡ ማንኛውንም የኦን ላይን ፈተና በብቃት የመስራት አቅም ያላቸውን ኮምፒተሮችን አስተሳስረን እየተገለገልን ነው።

ሌላው ተማሪዎች ኦን ላን ፈተና ከወረቀት መወደድ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በኦን ላይን ሁሉም ተማሪዎቻችንን እያስለመድን ነው፡፡

የሲኦሲ ምዘናዎችን በኦን ላይን እያካሄድን ነው ምንገኘው፡፡ የምዘና ፈቃድ አግኝተን እያስመዘንን እንገኛለን፡፡ ኮሌጃችን ላይ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሲሲቲቪ ካሜራ ገጥመን በቴክኖሊጂ እንዲታገዝ አድርገናል፡፡

ንጋት፡- በኮሌጁ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምን ደረጃ ላይ ነው?

ዶክተር ፀጋዬ፡- በሲዳማ ክልልም ሆነ በቀበሌያት ጥሪ ሲደረግልን ድጋፋችንን እናደርጋለን፡፡

በአረንጓዴ አሻራ እና በኤግዝቢሽኖች ላይ በብዛት ተሳትፈናል፡፡ ከኮሌጁ ውጪ ወጥተን የሰራነው ስራዎች ብዙ ባይኖሩም እንኳን በኮሌጁ ውስጥ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለሲዳማ ፣ ለቀድሞ ደቡብ ክልል እንዲሁም ለመከላከያ ማሰልጠኛ የኮማንዶ ዕዝ እንዲሁም ለመንግስት ተቋማት የትምህርት ክፍያ ነፃ ከማድረግ ጀምሮ በመቀነስ ጭምር ከፍተኛ ስራ ሰርተናል፡፡ በዚህም ማህበረሰቡን በማገልገል የራሳችንን አስተዋጽኦ አድርገናል ብዬ ነው ማስበው፡፡

ንጋት፡- ኮሌጁን ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ ከማድረግ አንፃር ምን እየተሰራ ነው?

ዶክተር ፀጋዬ፡- ወደፊት ሰፊ ቦታ ገዝተን ኮሌጁን ትልቅ የምርምር ማዕከል እና የመማር ማስተማር ተቋም ለማድረግ እየሰራን ነው፡፡

በኮሌጃችን እንደ ትልቅ ተግዳሮት የሚጠቀሰው የሰራነውን ሁሉ ለቤት ኪራይ ነው የምንከፍለው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የመንግስት አካል ቦታ በመስጠት ከከተማ ውስጥም ይሁን ውጪ ማገዝ ቢችል መልካም ነው፡፡

መንግስት ቦታ ማመቻቸት ቢችል በትምህርት ዘርፍ ላይ የበኩላችንን ሚና ለመወጣት የጀመርነው ጉዞ በቀላሉ እናሳካለን፡፡

ንጋት፡- በቀጣይ በኮሌጁ ሊሰሩ የታቀዱ እቅዶች ምንድናቸው?

ዶክተር ፀጋዬ፡- ዓመታዊ እና እስትራቴጅክ ፕላን አለን የ10 ዓመቱ ማለት ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት የሚመጣውን ለውጥ በሚያሳይ መልኩ ያዘጋጀናቸው ዓመታዊ፣ የአምስት ዓመት እና አስር ዓመት እስትራቴጂክ ፕላን አለን፡፡

እስትራቴጅክ ፕላኑ በ12 ፕሮግራሞች እየተመራ ያለውን ኮሌጅ ወደ 50 ፕሮግራም ወይም ዲፓርትመንት የማሳደግ ውጥን አለው፡፡ በቀጣይ ሙሉ ዩኒቨርሲቲ እውቅና አግኝቶ እስከሚሰራበት ድረስ የወደፊት ራዕይ ይዘን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡

ንጋት፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?

ዶክተር ፀጋዬ፡- ለትምህርቱ ማህበረሰብ የማስተላልፈው መልዕክት ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም አስፈላጊ በመሆኑ ለዚህ ቅድሚያ በሚሰጡ መሰል ኮሌጆች ሰው እራሱን፣ ልጆቹንና ቤተሰቡን ቢያስተምር መደገፍና መርዳት ቢችሉ መልካም ነው፡፡ ቋጨን፡፡

ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡

ዶክተር፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡