“ለሙዚቃ የተለየ ፍቅር አለኝ” – ድምፃዊት ትብለጽ ተከስተ
በአንዱዓለም ሰለሞን
በዋነኛነት የሲዳማ ብሔረሰብን ባህልና እሴት ለማጎልበት በሚል የተቋቋመው የ “ወሊማ ባንድ” ከተመሠረተ እነሆ በዚህ ዓመት 30 ዓመታትን አስቆጠረ፡፡ ባንዱ በእነዚህ ዓመታት በርካታ የኪነ ጥበብ ተሰጥኦ ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት ችሏል፡፡ በሲዳማ ባህል አዳራሽ ቅጥር ጊቢ ተገኝቼ፣ በአሁኑ ሰዓት ከባንዱ ጋር እየሰሩ ከሚገኙ ከተወሰኑ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጌአለሁ፡፡
ለዛሬ በዚህ አምድ ከሙዚቃ ባንዱ ጋር ለ15 ዓመታት ከሰራችው ድምጻዊት ጋር በነበረኝ ቆይታ ያወጋችኝን እነሆ፡፡
ድምጻዊ ትብለጽ ተከስተ፣ ትውልድና ዕድገቷ በሲዳማ ክልል፣ አለታ ወንዶ ከተማ ነው። ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ለኪነ ጥበብ፣ በተለይም ደግሞ ለሙዚቃ የተለየ ፍቅር እንደነበራት አጫውታኛለች፡፡ ቤት ውስጥ በማንጎራጎር የጀመረው የሙዚቃ ፍቅሯ፣ በሂደት ወደ አደባባይ መውጣቱ አልቀረም፡፡ ይህ የሆነው ግን እንዲሁ በቀላሉ አልነበረም፤ ዛሬ የደረሰችበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን በትዕግስት አሳልፋለች፡፡
እንደ አብዛኛው ታዳጊ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰጥኦዋን በአደባባይ ይፋ ያወጣችው ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በመቀጠል በወቅቱ በከተማው ወደሚገኘው “ጮራ የፀረ ኤድስ ክበብ” አመራች፡፡ በእርግጥ በክበቡ ተሳትፎ እንድታደርግ ቤተሰቦቿ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው፣ በትምህርቷ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት ነበር፡፡ በወቅቱ ተሰጥኦዋን የተመለከቱት አንድ መምህሯ ጉዳዩን ለቤተሰቦቿ በማስረዳት አስፈቀዱላትና ያሰበችው ሆነ፡፡ በክበብ ቆይታዋ በውዝዋዜ፣ በትወና፣ በድምጻዊነት፣ ተሳትፎ ታደርግ ነበር፡፡ ስዕል መሳልም ትሞክር ነበር፡፡ ለሙዚቃ የተለየ ፍቅር ስለነበራት ግን ይበልጥ ወደ እሱ አዘነበለች፡፡
በሂደት በክበቡ ቆይታዋ ሥራዎቿን የተመለከቱት ቤተሰቦቿ ያበረታቷት ጀመር። እሷም ከትምህርቷ ጎን ለጎን የክበቡን ሥራዋን አጥብቃ ያዘች፡፡ ይህን ሁኔታዋን የታዘቡት ቤተሰቦቿም እምነት ጣሉባት፡፡
በዚህ የተነሳ በ2000 ዓ/ም የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሟን ስትሰራ ሙሉ ወጪዋን የሸፈኑላት ቤተሰቦቿ ነበሩ፡፡ ያም ሆኖ አልበሟ ያን ያህል አልተሸጠላትም፡፡ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ስታስታውስ እንዲህ በማለት አውግታኛለች፡-
“ሁኔታው ከባድ ነበር፡፡ አባቴ ሰላሳ ሺህ ብር አውጥቶ ነበር ወጪዬን የሸፈነልኝ፡፡ በጊዜው ይህ ብዙ የሚባል ብር ነው፡፡ የአልበሙ ሽያጭ ግን እንኳንስ ትርፍ ላገኝበት ይቅርና ወጪውን እንኳ አልመለሰም፡፡ አጋጣሚው ጥሩ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ቤተሰቦቼ መኖሪያ ቤታቸውን እስከ መሸጥ የደረሱበትና እኔም የተጎዳሁበት ነበር” ብላለች፡፡
በወቅቱ የሆነው ነገር ተስፋ አላስቆረጠሸም? ስል ጥያቄ ማንሳቴ አልቀረም፡፡ እሷም እንዲህ በማለት መለሰችልኝ፡-
“እርግጥ ነው፣ ሁኔታው በጣም የተፈተንኩበት ነበር፡፡ ግን ደግሞ ፈጽሞ ተስፋ አላስቆረጠኝም። እንደውም የተሻለ ነገር ለመስራት እንድነሳሳ ነው ያደረገኝ፡፡ የሲዳማ ቋንቋና ባህል ገና ብዙ ሊሰራበት እንደሚችል እምነት ነበረኝ፡፡ ከዚህ አንጻር ያኔም ሆነ አሁን ሥራዬን ስሰራ በዋንኛነት የማስበው የምሰራው ሥራ ዛሬ ላይ ብዙም ተቀባይነት ባይኖረውና ጥሩ ገቢ ባያስገኝልኝም የሆነ ጊዜ ላይ ይደመጣል በሚል እምነት ነው። በእርግጥ አሁን ላይ ከበፊቱ በተሻለ ሥራዬ እየተደመጠ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂውም አስተዋጽኦ ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም እኔ የሚጠበቅብኝን ማድረግና የራሴን አሻራ ማሳረፍ ላይ ነው ትኩረት ያደረኩት፡፡ ሙያዬን እወደዋለሁ፡፡ የመስራት አቅም እንዳለኝም አውቃለሁ፡፡ ሥራዬን የምሰራውም በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው፡፡”
በዚህች ምድር ላይ ሳለን፣ በህይወት ጉዟችን የተለያዩ ነገሮች እንደሚያጋጥሙን እሙን ነው፡፡ ሁሉ ነገር በሂደት የሚታይና የሚታለፍ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትዕግስትና ጥንካሬን ይጠይቃል፡፡ ቁም ነገሩ ያለው መውደቁ ላይ ሳይሆን ወድቆ መነሣቱ ላይ ነውና፡፡ ይህን የተገነዘበ ሰው ደግሞ በመውደቅ ውስጥ መነሳትም እንዳለ ይረዳል፡፡ ስለሆነም ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን እርሱም በችግር ውስጥ በጽናት ያልፋል፡፡ ይህ ነው የአብዛኞቹ ስኬታማ ሰዎች የአሸናፊነት ምስጢር፡፡
ወደ ትብለጽ የህይወት ተሞክሮ ስንመጣም የምንገነዘበው ይህንኑ ነው፡፡ ቤተሰቦቿ ለሥራዋ መቃናት የከፈሉት መስዋዕትነት እንዳሰቡት ውጤታማ አለመሆኑ የፈጠረባት ስሜት በቀጣይ የህይወት ጉዞዋ አንድ ትምህርት አስተማራት፤ የራሷን ሃላፊነት መውሰድ እንዳለባት፡፡ ከዚህ በመነሳሳትም ከክበቡ በመውጣት ወሊማ ባንድን ተቀላቀለች፡፡ ይህ እርምጃዋም ለሚያጋጥሟት ችግሮች በራሷ መፍትሔ መስጠትን የተለማመደችበትን አጋጣሚ የፈጠረላት ነበር፡፡
ከባንዱ ጋር መስራት የጀመረችው በ1999 ዓ/ም የነጻ አገልግሎት በመስጠት ነበር፡፡ በዓመቱ ደግሞ የስራ ቅጥር ፈጽማ፣ ደመወዝ እየተከፈላት በቋሚ ሰራተኛነት ሥራ ጀመረች፡፡ በባንዱ የነበራትን ቆይታና ከሙያዋ አንጻር ያበረከተላትን አስተዋጽኦ አስመልክቶ ላነሳሁላት ጥያቄ ስትመልስም፡-
“በባንዱ ቆይታዬ ብዙ ነገር ተምሬአለሁ። ክበብ ስንሰራ ህዝብ ፊት ወጥተን ችሎታችንን ማሳየት ነበር የሚያስደስተን፡፡ በእርግጥ የአሁን መሠረቴ በዚያ ያሳለፍኩት ጊዜ ነበር፡፡ እዚህ ግን ሙያዬን ለማሳደግ የረዱኝን ነገሮች ነበሩ፡፡ በባንዱ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች ይገኛሉ፡፡ ሙዚቃ የምንጫወተው በእነዚህ የሙዚቃ መሳሪያዎች ታጅበን ነው፡፡ አዘውትረን ልምምድ መስራታችን ሙያዬን እንዳዳብር አግዞኛል፡፡ በተለይም ደግሞ የባህል ሥራዎችን ስሰራ ብዙ ነገሮችን እንዳውቅ አድርጎኛል፡፡ እዚህ አብረን ከምንሰራቸውም ሆነ ከእኛ በፊት ከነበሩት ባለሙያዎች ብዙ ልምድ ለመቅሰም ችያለሁ፡፡
“ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ መድረኮች ላይ ስራዬን ለማቅረብ የቻልኩበትን ዕድል ፈጥሮልኛል። በስራ ምክንያት የተለያዩ የሀገራችን ከተሞች የሄድንባቸው አጋጣሚዎችም አስደሳች ጊዜያትን ያሳለፍኩባቸው ነበሩ፡፡ ከሌሎች ባለሙያዎችና ከታዋቂ አርቲስቶች ጋር ለመገናኘትና ለመሥራት አስችሎኛል፡፡ ይህም ብዙ ነገር እንድገነዘብ አድርጎኛል” ብላለች፡፡
ከባንዱ ጋር በነበራት ቆይታ የሰራቻቸውን ሥራዎች አስመልክታ ስትናገርም፣ ከተለያዩ ሁነቶች ጋር በተያያዘ የሰራቻቸውን ስራዎች ሳይጨምር ከአስር በላይ የቪዲዮ ነጠላ ዜማዎችን እንደሰራች ገልጻለች፡፡ በቅርቡ የተመረቀው “አፊኒ” የተሰኘው ፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ የእሷ መሆኑንም አጫውታኛለች፡፡
በእንደዚህ ያለው የሥራ ወቅት፣ በጉዞም ሆነ በመድረክ ላይ መቼም ገጠመኞች አይጠፉምና የተለየ የምትለውን ገጠመኟን ታጫውተኝ ዘንድ መጠየቄ አልቀረም፡፡ እሷም እንዲህ በማለት ቀጠለች፡-
“ከባንዱ ጋር ሥራ በጀመርኩ ወቅት ሴት ድምጻዊ እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ከዚህ የተነሳ በተለይ ዝግጅት ሲኖር ስራ ይበዛብኝ ነበር፡፡ ወንድና ሴት በመሆን የምንጫወተው ሙዚቃ ሲኖር፣ የሴቷን ቦታ ሁሌም እኔ ነበርኩ የምሸፍነው፡፡
አንድ ጊዜ “ፋሮ” የሚባለውንና ወጣት ወንድና ሴት በጋራ የሚጫወቱትን ሙዚቃ ከአንድ ባለሙያ ጋር ሰራንና ቀጥሎ ደግሞ “ሀኖ” የሚባለው የትልልቅ ሰዎች ጨዋታ ቀጠለ፡፡ ሁለቱ ስራዎች በተለያየ ዓይነት ባህላዊ አልባሳት ነበር የሚሰሩት፡፡ ከመድረክ ጀርባ ሆኜ ለመጀመሪያው ስራ የለበስኩትን ልብስ (ጉርድና አላባሽ) አውልቄ ሌላ ልብስ ቀይሬ፣ እናቶች የሚለብሱትን ቀሚስ ለብሼና ካባ ደርቤ ለቀጣዩ ስራ “ሀኖ” ወደ መድረክ ተመለስኩ፡፡ መድረክ ላይ የምጫወተው ከአንጋፋው የሲዳምኛ ድምጻዊ አዱኛ ዱሞ ጋር ነበር፡፡ በዚህ መሀል ግን ያላስተዋልኩትን አንድ ስህተት ሰርቼ ነበር፡፡ ጉርድ ቀሚሱን ስቀይር፣ ባለዚፑ አላባሽ ግን እታች ጉልበቴ ጋ ደርሶ ነበር እንጂ አላወለኩትም፡፡ ስለቸኮልኩ ይህን ሳላስተውል ነበር ወደ መድረክ የወጣሁት፡ ፡ ሙዚቃውን እየተጫወትን እያለ የሆነ ነገር ይሰማኛል፡፡ በውስጤ ‹ምንድነው? እላለሁ› ትኩረቴ ግን ሥራዬ ላይ ስለነበር ነገሩን ልብ አላልኩትም፡፡
በመሀል ላይ ሴቶች ክብ ሰርተው፣ እኔ መሀላቸው ሆኜ የምዘፍንበት ክፍል አለ፡፡ እነሱ ሸፍነውኝ እየዘፈንኩ ሳለ አላባሹ ወልቆ መሬት ወደቀ፡፡ አጋጣሚው ያልጠበኩት ቢሆንም ይህ የሆነው ቢያንስ ሴቶቹ በከለሉኝ ጊዜ መሆኑ ጥሩ ሆኖልኛል” በማለት ከማትረሳቸው ገጠመኞቿ መካከል አንዱ የሆነውን አጫወተችኝ፡፡
ስታስባቸው የሳቋ ምንጭ የሚሆኑ ሌሎች መሰል ገጠመኞችም ደግሞ አሉ፡-
“ሽልማት ሊሰጥህ መጥቶ አንገትህን አንቆ ይዞ የሚያስጨንቅህ፣ ሰውነትህን ሲደባብስ ውሎ አንድ ብር ሚሸጉጥልህ፣ አንድ ብር ለመሸለም የመቶ ብር ምራቅ ግንባርህን የሚቀባህ፣ አለ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በጆሮህ ግጥም ይነግርህና ዋናውን የሙዚቃ ግጥም ያስጠፋሀል፡፡ አንዳንዱ እጅህን ከነማይኩ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ይይዛል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ጭራሽ ማይኩን ተቀብሎህ ይዘፍናል፡፡ ይህን ጊዜ እሱ እስከ ሚጨርስና ማይኩን እስከ ሚሰጥህ ድረስ በትዕግስት ከመጠበቅ ውጪ ሌላ ምን አማራጭ ይኖርሀል?”
ይህን ያለችኝ እየሳቀች ነበር፡፡ በእርግጥም ነገሩ ፈገግ ከማሰኘትም በላይ ነበርና እኔም ስሜቷን መጋራቴ አልቀረም፡፡ በሳቃችን መካከል የመጨረሻ ያልኩትን ጥያቄዬን አስከተልኩ፤ “በቀጣይ ምን እንጠብቅ?” በማለት፡፡ እርሷም እንዲህ ስትል ምላሿን ሰጠችኝ፡-
“ሁለተኛውን አልበሜን ሰርቼ ጨርሻለሁ፡፡ ፕሮዲዩሰር እንዳገኘሁ ሁሉ ነገር ተጠናቆ ለህዝብ ይደርሳል፡፡”
እኔም ያሰበችው ተሳክቶና ሥራዋ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለህዝብ ጆሮ ይደርስ ዘንድ እየተመኘሁ ስለነበረን መልካም ቆይታ አመስግኛት ተሰነባበትን፤ “ኬሩ ጣዶንኬ” (ቸር ይግጠመን) በማለት፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው