የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በህገወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩና ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በህገወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩና ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
ህገ ወጥነትና የኮንትሮባንድ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት በማባባስ ከፍተኛ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የገለፁት የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ይህን ህገ ወጥ ተግባር ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ጠንካራ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም ከ56 ሺህ ሌትር በላይ ነዳጅ በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ ተይዞ 15 ሚሊዮን ብር በመሸጥ ለመንግስት ገቢ መደረጉን እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ 177ሺህ ኩንታል የእህል ምርት ወደ ሰንበት ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል። ምርት ያከማቹ የመጋዘን ባለቤቶች ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ አስተዳደራዊ ቅጣት በመቅጣት ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ተደርጓል።
እንደ ሀገር የተጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 626 የንግድ ድርጅቶችን ማሸጉንና 60 ነጋዴዎች ደግሞ በህግ ተቀጥተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም ህገ ወጥነትና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከክልል እስከ ቀበሌ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እየተካሄደ በሚገኘው የክልሉ ሴክቶራል ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።
ሀገራችን የጀመረችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ተግባራዊ እናደርጋለን በሚል መሪ ቃል በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ የክልሉ ር/መ አቶ እንዳሻው ጣሰው፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ም/ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ሰርሞሎ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ብሩክ ፋንታ
More Stories
በጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ
የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ ሊውል እንደሚገባ ተገለጸ
በ2017 ዓ/ም 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለጸ