በጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የወላይታ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።
በ2017 በጀት ዓመት ከ6 ቢልዮን 48 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተጠቁሟል።
የወላይታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጎበዜ ጎዳና በዞኑ የሚስተዋለው ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረትና የህዝቡ የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ሥራ ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት ብለዋል።
የገቢ አሰባሰብ ሥራዓት በማዘመን ለግብር ከፋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ሥራና የተገልጋዩን እርካታ ከማሳደግ አንጻር ሰፊ ሰራዎች መሰራት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
ከግብር ስወራና ታክስ ማጭበርበር ጋር አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለማረም ህገወጦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ መጠናከር እንዳለበትም ምክትል አስተዳዳሪ ጠቁመዋል።
የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይለ ስላሴ እስካሁን ባለው ሂደት የገቢ አሰባሰብ ሥራዓት ዘመናዊ አለመሆን የዞኑ ገቢ ላይ አሉታዊ ጫና ከመፈጠሩ ባሻገር በግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ዘንድ ቅሬታ እየፈጠረ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የገቢ አሰባሰብ ሥራዓት በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር ሰፊ ሥራዎች ተጀምሯል ያሉት አቶ ሀይሌ የተጀመረው ሥራ ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር የገቢ መጠንን ሰፊ ለማድረግ ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፥ ከሙያ ስነምግባር ውጭ የሚንቀሳቀሱ ባለሙያዎችና አንዳንድ ህገወጥ ነጋዴዎች መኖር ለአፈፃፀሙ እንቅፋት እየፈጠረ መቆየቱን አንስተው እነዚህ ግለሰቦች በመለየት ህጋዊና አስተዳዳራዊ እርምጃ የመውሰድ ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 6 ቢሊዮን 48 ሚሊዮን 376 ሺህ ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱንም ጠቁመዋል።
በዚህም 62 ነጥብ 3 በመቶ የዞኑን በጀት በውስጥ ገቢ ለመሸፈን ታቅዷል በማለት ለሰኬታማነቱ ከተለያዩ መዋቅሮች ጋር የዕቅድ ግብ ስምምነት ፊርማ ተካሂዶ ወደ ተግባር ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም አብራርተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ያሉት ሀላፊው፥ ይህም የገቢ አቅምና ከህዝብ ፍላጎት አንጻር ለቀጣይ ሰፊ ሥራ ይፈልጋል ብለዋል።
በዞኑ የቦዲቲ ከተማና ዳሞት ፑላሳ ወረዳ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ አየለ እና አቶ ክፍሌ ጁባቴ በሰጡት አሰተያየት ግብር ከፋዮች ዘንድ ከግዜ ወደ ግዜ መሻሻል መታየቱን ጠቁመው፥ በተለይም የአሰባሰብ ሂደቱን በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር የተጀመረው ሥራ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲሆን የገቢ መጠንን በማሳደግ የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተገቢው መመለስ እንደሚቻልም አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ በቀለች ጌቾ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ