“የተፈጥሮ ሃብት ልማት ቀዳሚና ቁልፍ ሥራችን ነው”  – አቶ መምሩ ሞኬ

በመሐሪ አድነው

ንጋት፡- የንጋት እንግዳ ለመሆን ፍቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍላችን ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ መምሩ፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- በመጀመሪያ ራስዎን ያስተዋውቁን!

አቶ መምሩ፡- የትውልድ ቦታዬ በአሁኑ ሲዳማ ክልል በቀድሞ ሃገረ ሠላም ወረዳ ዊራማ በምትባል ቀበሌ ነው፡፡ አንደኛ ደረጃ ትምህርቴን በዊራማ ቀበሌ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ወይም በወቅቱ አጠራር ሚሽን ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፡፡ በወቅቱ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚባለውን ከ7 እስከ 8ኛ ክፍል በሃገረ ሠላም ከተማ ደጃዝማች ባልቻ ትምህርት ተማርኩኝ፡፡ የደረጃ ተማሪ ስለነበርኩኝ በመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ድርጅት የትምህርት እድል ተሰጥቶኝ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በጌዴኦ ዞን በዲላ ሆስቴል ለመማር ችያለሁ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ውድድሩ ከፍተኛ ስለበር ወደ ኮሌጅ የሚያስገባኝ ውጤት አልመጣልኝም ነበር፡፡

ስለሆነም ወደ ትውልድ አካባቢዬ ተመልሼ በልማት ጣቢያ ሠራተኝነት የሚያበቃኝን የትምህርት እድል አግኝቼ ከአጋርፋ ግብርና ኮሌጅ በሰርተፊኬት ተመርቄ በ1988 ዓ.ም ሥራ ጀመርኩኝ፡፡ ታታሪ ሠራተኛ ነበርኩኝ፡፡ የምታትረው ግን የደረጃ እድገትም ሆነ የትምህርት እድል ማግኘት እንደሚቻል ግንዛቤ ኖሮኝ ሳይሆን ለሥራ ካለኝ ፍቅርና ህብረተሰቡን ለማገልገል ከነበረኝ ፍላጐት በመነሳት ነበር፡፡ ተነስቼ ወደ ሥራ ለመሄድ ካለኝ ናፍቆት የተነሳ፡፡ ሌሊቱ እንኳን ቶሎ አይነጋልኝም፡፡ እውነት ለመናገር ይህን የማደርገው ሹመትና ሽልማት ጠብቄ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ሳላውቀው በሥራዬ ግንባር ቀደም ሆኛለሁ፡፡ ከዚያ የዲፕሎማ የትምህርት እድል ተሰጥቶኝ በሃዋሣ ግብርና ኮሌጅ በከፍተኛ ማእረግ በአጠቃላይ እርሻ (General Agriculture) ተመርቄ ዲፕሎማ ያዝኩኝ፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠንከሮ በመሥራት የትምህርት ደረጃም የደመወዝ መጠንም ማሳደግ ይቻላል የሚለው ሃሳብ በውስጤ ገባ፡፡ የሥራ ትጋቴም ጨመረ፡፡ ወዲያውኑ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በራሴ ገንዘብ ለመማር ወሰንኩኝ፡፡ ምክንያቱም ጽህፈት ቤት ገብቻለሁ፤ ደመወዜም በእጥፍ ጨምሯል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ኮሌጅ በማህበረሰብ ልማት (Community devel­opment) ድጋሚ በከፍተኛ ውጤት በ2007 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪዬን ወሰድኩኝ፡፡

በአጭር ጊዜ የወረዳው ግብርና እና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ እንድሆን ሹመት ተሰጠኝ፡ እኔ ግን ላለመቀበል አንገራግሬ ነበር፡፡ በአስገዳጅ ሁኔታ ሃላፊነት ተሰጠኝና ለአምስት አመታት በሃገረ ሠላም አገለገልኩኝ። ከዚያም በሸበዲኖ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሆኜ ሠራሁ፡፡ ከአንድ አመት ተኩል በኋላ ወደ ቀድሞው ሲዳማ ዞን ምክትል የግብርና መምሪያ ሃላፊ ሆኜ መጣሁ፡፡ በዚህ ፍጥነት ማደግ የቻልኩት ከልጅነቴ ጀምሮ ያዳበርኩት የስራ ተነሳሽነትና ህብረተሰቡን የማገልገል ፍላጐት እንደዚሁም ከሌብነት እጆቼን በማንፃቴ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ሥራዬን ስሰራ በተመደብኩበት ቦታ ውጤት ማምጣት አለብኝ ብዬ ነው እንጂ ይህን ሠርቼ ያንን አገኛለሁ ብዬ አልነበረም። እንደገና ከ6 ወር በኋላ የቀድሞ ሲዳማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ ሆንኩኝ፡፡ እዚያም ለ5 አመታት ውጤታማ ሥራን ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያም በቀድሞ የደቡብ ክልል አማካኝነት የውጪ የትምህርት እድል አግኝቼ ወደ አንድ አመት ተኩል ያህል በደቡብ ኮሪያ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ላይ የሁለተኛ ዲግሪዬን ከዲፖርትመንቴ ተሸላሚ ሆኜ አጠናቅቄአለሁ፡፡ በአጠቃላይ በትምህርቴም ሆነ በስራዬ ለያዝኩት ዓላማ መሳካት ቁርጠኛ ነኝ፡፡ ይህን ደግሞ ከልጅነቴ ጀምሮ ያዳበርኩት ነው፡፡

ንጋት፡- የውጭ ሃገር ትምህርትዎን ጨርሰው ከተመለሱ በኋላ የነበረው ሁኔታ እንዴት ነበር?

አቶ መምሩ፡- ከደቡብ ኮሪያ እንደተመለስኩኝ አጋጣሚ ደቡብ ክልል አልፈረሰም ነበርና በደቡብ ክልል ስር በሲዳማና በጌዴኦ ላይ የሚሠራ “የእሴት ሠንሠለት ኘሮጀክት” የሚባል ኘሮጀክት ውስጥ ለሁለት አመት ሠራሁ፡፡ እዚያ እያለሁ ሲዳማ ክልል ሆኖ ተዋቀረ፡፡ ከዚያ በኋላ በሲዳማ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ሆኜ ወደ አንድ አመት ያህል ካገለገልኩኝ በኋላ የክልሉ መንግስት አሁን ወዳለሁበት የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አድርጐ ሾመኝ፡፡

ንጋት፡- ደቡብ ኮሪያ በነበሩ ወቅት ይሄ ነገር ቢኖረን ብለው የተመኙት ነገር ነበር?

አቶ መምሩ፡- ጥሩና የተሻለ ነገር ሲያይ ሠው ለራሱ ይመኛል፣ ይቀናልም፡፡ ከዚህ አንፃር ቻይና ሃገር ላይ የቻይናን እድገት፣ የቻይናን ጥረትና የእድገት ጉዞ፣ የህንድን የለውጥ መንገድ እንደዚሁም የቬትናምን የልማት እድገት በፅሁፍ ካነበብኩትና በታሪክ ከሰማሁት በላይ በአካል ተገኝቼ የመጐብኘት እድል አጋጥሞኛል፡፡ በልማታዊ መንግስታትና ፈጣን እድገት በማምጣት የሚገለፁ የእሲያ ሃገራት ናቸው፡፡ በእነዚህ ሃገራት የተመዘገበው የእድገት ለውጥ በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ ላይ በችግርና በድህነት ስቃይ ያየ ትውልድ በአጭር ጊዜ በተከናወኑ የልማት ተግባራት ትውልዱ ሳያልፍ አሁን ላይ የተንደላቀቀ ህይወት ለመኖር እድል አግኝቷል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት የእለት ጉርስ ያልነበረው ትውልድ ጠንክሮ በመስራቱ ምክንያት የተሻለ ህይወት ለመኖር ችሏል፡፡

ይህ ነገር ታዲያ እድገት በአንድ ትውልድ ማስመዝገብ ይቻላል የሚለውን መልእክት ያስተላልፋል ማለት ነው፡፡ የእሲያ ሃገራት እድገት በአንድ ትውልድ የመጣ ፈጣን እድገት በመሆኑ በእኛም ሃገር ይህ ነገር መሆን ይችላል የሚለውን መንፈሳዊ ቅናትና ተስፋ ያሳድርብሃል፡፡

ነገር ግን እነዚህ ሃገራት በተፈጥሮ ፀጋም ይሁን ከአየር ንብረት አኳያ ሲታይ እንደ እኛ ሃገር የተመቸ ነገር ያላቸው አይደሉም። ለምሳሌ የደቡብ ኮሪያ የመሬት ሽፋን 67 በመቶው ደንና ተራራ ነው፡፡ እናም ባለችው 33 በመቶ መሬት ምርት አምርቶ፣ የመኖሪያ፣ የኢንቨስትመንት ከተማና ሌሎችን ጨምሮ በ33 በመቶ የሆነች መሬት ነው በምግብ ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ ሚና የሚጫወተው፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛ መሬት፣ ውሃና ሥነ ምህዳሩ እጅግ ምቹ ነው፡፡ ደቡብ ኮሪያዎች ብዙ ፍላጐት ባላቸው ሃገራት ዙሪያቸው ተከቦ እያለ ያንን ተቋቁመው ባለቻቸው አነስተኛ መሬት ላይ አምርተው መቀየር ከቻሉ እኛ ለመቀየር ከእነርሱ እጅግ ያጠረ ጊዜ ነው የሚወስደው፡፡ በመሆኑም እኛም ቁርጠኛ ሆነን የእነርሱን ተሞክሮ ብንወስድና የተሻለ አምርተን የተሻለ ኑሮ ብንኖር ብዬ ነው ስመኝ የነበረው፡፡ በርካታ የተመቻቹ ፀጋዎች እያሉን ማደግ ያልቻልነው ለምንድነው ብዬም እቆጫለሁ፡፡ የሚገርመው ኮሪያዎች በሃገራቸው እና በብሔራዊ ጥቅማቸው ጉዳይ አንድ ሃሳብ ነው ያላቸው፡፡ “እኛ ኮሪያኖች” እንጂ “እኔ” የሚል የግለኝነት አስተሳሰብ የላቸውም፡፡ ለህዝባቸው እና ለሃገራቸው ጥቅም በጋራ ነው የሚቆሙት፡፡

በአንድ ወቅት ሃገራቸው የዶላር እጥረት በገጠማት ጊዜ የመላው ሃገሪቱ ሴቶች ፀጉራቸውን ተላጭተው በማዋጣት ለመንግስት አስረክበው ያ ፀጉር ወደ ሂዩማን ሄር ተቀይሮ ለውጭ ሃገር ገበያ ቀርቦ / ኤክስፖርት ተደርጐ/ ብዙ ዶላር መሰብሰብ የቻሉበትና የሃገራቸውን ችግር የፈቱበት ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ናቸው ኮሪያውያኖች፡፡

በሌላም ወቅት ሃገሪቱ ላይ የኢኮኖሚ ድቀት ደርሶ ሁሉም ዜጐች የጋብቻ ቀለበቶቻቸውን ጨምሮ የአንገት፣ የጆሮና የእጅ ጌጣጌጦቻቸውን ወርቆቻቸውን አጠቃላይ ልክ እንደእኛ ሃገር ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ለባንክ አስገብተው ያ ተሽጦ ነው ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ማንሰራራት ምክንያት የሆኑት፡፡

እኛም ለሃገር ጥቅም በጋራ ብንቆምና መለያየቶችንና ግለኝነትን ብናስወግድ እነርሱ ካደጉበት በእጥፍ ባጠረ ጊዜ ውስጥ መለወጥ እንችላለን፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁላችንም ጥረትና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡

በልማት ተጠቃሚነታቸው ዙሪያ የመጡ ለውጦች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ አስችሎአቸዋል፡፡

እኛም ሃገር የተጀማመሩ ነገሮች ለምሳሌ አረንጓዴ አሻራና የበጋ ስንዴን የመሳሰሉ የልማት ስራዎች በንቅናቄ እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ በእንደዚህ መልኩ በጋራ ከሠራን የማንለወጥበት ነገር አይኖርም፡፡

ንጋት፡- አሁን ወደ ክልሉ እንመለስና የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴው በሲዳማ ክልል በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ መምሩ፡- የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራችን ቀዳሚና ዋነኛው ቁልፍ ሥራችን ነው፡፡ ይህ ዘርፍ የማይነካው አካባቢ የለም፡፡ ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው፡፡ የመሬት አጠቃቀማችንም የሚሻሻለው በዚህ ነው፡፡ በመሆኑም ላለፉት አመታት እንደሃገር ወደ 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በዚህ አመት ወደ 4ዐ ቢሊዮን ለማድረስ እየተሠራ ያለው፡፡ እንደ ሲዳማ ክልል እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በእነዚህ ውስጥ የደን ፣ የፍራፍሬና ጥምር ደንና የእንስሳት መኖ ታሳቢ ተደርገዋል፡፡ በሂደት ወደ ጥራት መሻገር አለብን በማለት የፍራፍሬ እና የእንስሳት መኖ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለን ወደዚያ እያሳደግን እንገኛለን፡፡ በዚህ አመት ደግሞ ወደ 300 ሚሊዮን ችግኞችን በማቀድ 287 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ ተካሂዷል፡፡

የፅድቀት መጠናቸው ሲታይ እስከ አሁን ባለው ወደ 85 በመቶ ፀድቀዋል። ለችግኙ መፅደቅና አለመፅደቅም የአየር ንብረት ተፅእኖ የራሱ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የዚህ አመት ተከላው ተጀምሯል፡፡ በቀጣይ የአንድ ጀምበር ተከላ አለ፡፡ ይህ ቡናን ሳይጨምር ነው፡፡ ቡናን ባለፈው አመት ወደ 24 ሚሊዮን ችግኞች ተክለናል፡፡ የፍራፍሬ ችግኞች 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ናቸው። አብዛኛው አቦካዶ ነው፡፡ አቦካዶን ከሃገር ውስጥ ምግብነት ባሻገር “ለአግሮ ኘሮሰሲንግ ግብአትነት ስለሚውል በስፋት እየሰራንበት ነው፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ውጤት በአንድ በኩል የአፈርና ውሃ መሸርሸርን፣ የአፈር ብክለትንና፣ የአፈር መሸርሸርን ተከላክሏል፡፡ የተጐዱ መሬቶችም ሲያገግሙ አይተናል፡፡ አንዳንድ አካባቢዎችም ላይ ምንጮች መፍለቅ ችለዋል።

የደን ሽፋን ጨምሯል፤ የእንስሳት መኖ እያደገ ነው፡፡ በተለይ የጠረጴዛ እርከኖች በተሠሩባቸው አካባቢዎች ሠብል ወደ ማልማት የተገባበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ስንመለከት ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግም ረገድ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ብለን ማየት እንችላለን፡፡

ንጋት፡- የመኸር ወቅትን ጨምሮ የበልግ ምርት እንክብካቤ እና የመስኖ ልማት ስራ በአጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ የአመቱ ሥራ አፈፃፀም ምን ይመስላል?

አቶ መምሩ፡- የአመቱን አፈፃፀም ስናይ የተሻለ አፈፃፀም አለው፡፡ የግብርና ልማት ሥራ ግቡ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ ይህ ማለት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ ገበያ ላይ የተመሠረተ ምርት በማምረት ለገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ማለት ነው፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለአግሮ ኘሮሰሲንግ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ የግብርና ልማት ሥራ እነዚህ አራት አይነት አበይት ተልእኮዎች አሉት፡፡ ለዚህ ማእከላዊው ነገር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂ መጠቀም፣ የግብአት አጠቃቀም ማሻሻልና የኤክስቴንሽን ስርዓቱ እንዲዳብር ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን ስናከናውን መጥተናል፡፡

የባለፈውን የመኸር ምርትን ስናይ ወደ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በማቀድ ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ሠብል ተሰብስቧል፡፡ አፈፃፀሙም ወደ 88 በመቶ አካባቢ ነው፡፡ የአምናው ምርት በዚህ አመት ስለሚሰበሰብ አልተለየም፡፡ ያቀድነውን መቶ በመቶ ባናሳካም የተሻለ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡ የመስኖ ልማት ሥራዎች በዚህ አመት በሁለቱም ወደ 68 ሺህ ሄክታር በማቀድ 66 ሺህ ሄክታር ለማሳካት ችለናል። ይህ ማለት ከ94 በመቶ በላይ ተሳክቷል። ከዚህም ባለፈ የአካባቢውን ገበያ በተሻለ ሁኔታ አረጋግቶ አልፏል፡፡ በተለይ በአትክልት ማለትም በሽንኩርት፣ በቲማቲም ፣ በጥቅል ጐመን አቅርቦት ረገድ ገበያ በማረጋጋት በጐ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

የበልግ ልማት ሥራችን በአጠቃላይ ወደ 112 ሺህ ሄክታር ነበር የታቀደው ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የበቆሎ ልማት ሥራ ነው፡፡ በቆሎ አሁን ወደ 63 ሺህ ሄክታር ለምቷል፣ ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ነው የምንጠብቀው፡፡ ሆኖም ግን በዚህ አመት ከበልግ ወቅት ዝናብ መቆራረጥ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ችግር አጋጥሟል፡፡ ከአየር ንብረት ተፅእኖ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ላይ ምርቱ እየተሰበሰበ ስላለልሆነ ውጤቱን በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ እንደዚያም ሆኖ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በቆሎም ደርሶ እሸትም እየተበላ ይገኛል። ጥሩ ምርት የታየባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንም አይተናል፡፡

በዚህ አመት የግብአት አጠቃቀማችን እጅግ የተሻለ ነው። ከ266 ሺህ ኩንታል በላይ ለማቅረብ አቅደን ከ85 በመቶ በላይ አሳክተናል፡፡ አጠቃቀሙን ከማሻሻልና ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አንፃር ካልሆነ በስተቀር በዚህ አመት በማዳበሪያ አቅርቦትም ሆነ ስርጭት ዙሪያ እንደ እጥረት ሆኖ ያጋጠመን ችግር የለም፡፡

ንጋት፡- ጊዜዎትን ሰውተው ከእኛ ጋር ቆይታ ስላደረጉ በዝግጅት ክፍላችን ስም በድጋሚ አመሠግናለሁ፡፡

አቶ መምሩ፡- እኔም አመሠግናለሁ፡፡