የእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግ አዲሱ የውድድር ዘመን ዛሬ ምሽት ይጀምራል

የእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግ አዲሱ የውድድር ዘመን ዛሬ ምሽት ይጀምራል

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግ የ2024/25 የውድድር ዘመን ዛሬ ምሽት ማንቸስተር ዩናይትድ ከፉልሃም በሚያደርጉት ጨዋታ ጅማሮውን ያደርጋል።

ምሽት 4 ሰዓት ላይ በኦልድትራፎርድ ስታዲዬም ሁለቱ ክለቦች የውድድር ዓመቱን የመክፈቻ ጨዋታ ያከናውናሉ።

ባለፈው የውድድር ዓመት 8ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ በሊጉ የተሳትፎው ታሪክ ዝቅተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ማንቸስተር ዩናይትድ በአዲሱ የውድድር ዓመት ወደ ጥንካሬው ለመመለስ ጥረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ለዚህም ይረዳው ዘንድ ክለቡ አስተዳደራዊ መዋቀሩንና በኤሪክ ቴንሃግ የአሰልጣኝ እስታፍ አባላት ላይ ለውጦችን ማድረጉ ይታወቃል።

በተጨማሪም ማንቸስተር ዩናይትድ ራሱን ለማጠናከር ወደ ዝውውሩ ገበያ በመውጣት እስካሁን አራት ተጫዋቾችን ማለትም ሌኑ ዮሮን ከሊል፣ ጆሹዋ ዜርክዜን ከቦሎኛ እንዲሁም ኑሳይር ማዝራዊንና ማቲያስ ዴላይትን ከባየርሙኒክ ወደ ስብስቡ የቀላቀለ ሲሆን በአንፃሩ አንቶኒ ማርሺያልና ራፋይል ቫራንን ጨምሮ 5 ተጫዋቾች ክለቡን ለቀዋል።

በአሰልጣኝ ማርኮ ሲልቫ የሚመራው ፉልሃም በበኩሉ በአሮጌው የውድድር ዓመት 12ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል።

የምዕራብ ለንደኑ እግርኳስ ክለብ ቁልፉን አማካይ ጆአዎ ፓልሂንሃን ወደ ባየርን ሙኑክ የክለቡ ክብረወሰን በሆነ ሽያጭ ሸኝቶ በምትኩ የአርሰናሉን አማካይ ኤሚል ስሚዝ ሮውን የክለቡ ክብረወሰን በሆነ ግዢ (35 ሚሊዮን ፓውንድ) ወደ ስብስቡ መቀላቀል ችሏል።

በማንቸስተር ዩናይትድ በኩል አዲሱ ፈራሚ ሌኒ ዮሮ፣ ሉክ ሾው ታይለር ማላሲያና ራስሙስ ሆይሉን በጉዳት ምክንያት ከምሽቱ ጨዋታ ውጪ ሲሆን በፉልሃም በኩል ሙሉ ስብስቡ ለጨዋታ ብቁ መሆናቸው ተነግሯል።

የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ በነገው ዕለትም ቀጥሎ ሲካሄድ ኢፕስዊች ከሊቨርፑል ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ፣ አርሰናል ከወልቭስ ከቀኑ 11 ሰዓት፣ ኤቨርተን ከብራይተን፣ ኒውካስል ከሳውዝሃምፕተን፣ ዌስትሃም ዩናይትድ ከአስቶንቪላ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት እንዲሁም ኖቲንግሃም ፎረስት ከቦርንማውዝ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ይጫወታሉ፡፡

እሑድ ዕለት ደግሞ ቼልሲ ከማንቸስተር ሲቲ ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታ የሚያካሂዱ ይሆናል፡፡

ዘጋቢ፡ በሙሉቀን ባሳ