ባለፉት ዓመታት በኩታ ገጠም እርሻ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማስፋት የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን በFOLUR (FOOD LAND USE RESTORATION) ፕሮጀክት የታቀፉ ወረዳዎች በ2026 በሚተገበር መሪ ዕቅድ ዙሪያ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ ውይይት በይርጋጨፌ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሀግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክለልል ግብርና ቢሮ አማካሪ አቶ አበባየሁ ኢሳይያስ፥ እንደሀገር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ፕሮጀክቱ ባደረገው ድጋፍ ለውጥ እየታየ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት በኩታ ገጠም አስተራረስ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማስፋት የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ባለድርሻዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ አበባየሁ አሳስበዋል፡፡
ፍሎር ኢትዮጵያ ፕሮጀክት በፓይለት በተመረጡ ወረዳዎች በተቀናጀ መሬት አያያዝ፣ በቡና ምርታማነትን ማሳደግና የምግብ ስርዓትን ማሳለጥ፣ የተፈጥሮን ደን መጠበቅና መንከባከብ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሰፍን በማድረግ ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማስፋፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍሎር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አለምበጁ ክፍሌ ተናግረዋል፡፡
የአየር ብክለት ለመከላከል ከ4 ሺህ 890 በላይ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ በፓይለት ፕሮጀክቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዴኦ ዞን ባቀፋቸው በይርጋጨፌ፣ በወናጎና ኮቾሬ ወረዳ ማሰራጨታቸውንና በአጠቃቀም ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ስልጠና በመስጠት ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አቶ አለምበጁ አብራርተዋል፡፡
የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ አርሶአደሩን በኩታ ገጠም በማደራጀት በወናጎና ኮቾሬ ወረዳ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስፋት በዚህ ዓመት በይርጋጨፌ ወረዳ አርሶአደሮችን በማደራጀት ለቡና ተከላ የማሳ ቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
የይርጋጨፌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔ በበኩላቸው፥ ፎሎር ኢትዮጵያ ፕሮጀክት በተቀናጀ የመሬት አያያዝ፣ በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶችንና በልማት ለተደራጁ ሴቶች ድጋፍ በማድረግ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስታውሰዋል፡፡
በወረዳው በፕሮጀክቱ በታቀፈ በቆንጋ ቀበሌ 52 አርሶአደሮችን በኩታ ገጠም በማደራጀት 32 ሄክታር መሬት ያረጁ የቡና ዛፎችን በአዲስ ለመተካት የማሳ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አቶ ዳዊት ጠቁመው፥ ምርቱ እስኪደርስ የመሬትን ለምነት የሚጨምሩ ሰብሎችን በመትከል ባለይዞታዎቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በፕሮጀክቱ ድጋፍ በይርጋጨፌ ወረዳ በቆንጋ ቀበሌ ቡናን በኩታ ገጠም ለማልማት የሚከናወኑ የማሳ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን የመስክ ምልከታ ተካህዷል፡፡
በመርሀግብሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አማካሪ አቶ አበባየሁ ኢሳይያስን ጨምሮ በክልሉ በፎሎር ኢትዮጵያ የሚሠሩት ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ፣ ወናጎና ኮቾሬ ወረዳ አስተዳዳሪዎችና የፕሮጀክቱ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የእምነት ተቋማት ለአገረ መንግስት ግንባታ ቁልፍ ሚና ያላቸው በመሆኑ ለሀገር ብልጽግና ኃይል አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ ተመላከተ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ብልፅግና እንዲረጋገጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቷ ተገለጸ
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምዕመናን ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው