በ2017 ዓ/ም 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2017 ዓ/ም 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የጌዴኦ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያው በ2016 ዓ/ም ገቢ አፈፃፀምና 2017 ዓ/ም ዕቅድ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የውይይት መድረክ በዲላ ከተማ በማካሄድ ላይ ነው፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደውን ገቢ በተገቢው መሰብሰብ የተሻለ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በገቢ አሰባሰብ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስቀረት ሁሉም አመራሮች፣ ባለድርሻዎችና ባለሙያዎች በቅንጅት በመንቀሳቀስ ለዕቅዱ ስኬታማነት መሥራት እንዳለባቸው አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡
አክለውም ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ቅንጅታዊ ሥርዓት በመዘርጋትና በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ በየጊዜው ዕቅዱንና አፈጻጸሙን በመገምገም ለተሻለ ውጤት እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡
የዞኑ ዋና የመንግሥት ተጠሪና የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበባየሁ ኢሳይያስ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ ለመመለስ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት መከተል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ሁሉም የዞኑ አመራሮች በሥሩ ያሉ መዋቅሮችን በመከታተል፣ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ የተሻለ ገቢ በመሰብሰብ ዕቅዱን ለማሳካት መረባረብ እንደሚያስፈልግ አቶ አበባየሁ ጠቁመዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ገቢዎች መምሪያው ኃላፊ አቶ ጌቱ ታምሩ በ2017 ዓ/ም 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን በመግለጽ በገቢ አሰባሰብ የሚታዩ ውስንነቶችን በመፍታት በተሻለ ሁኔታ ለመሰብሰብ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
በ2016/17 ዓ/ም የደረጃ “ሐ” ገቢ አሰባሰብ ከዕቅድ በላይ መከናወኑን በመግለጽ በደረጃ “ለ”ና “ሀ” የተጀመሩ የአሰባሰብ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ተሻሽሎ የቀረበው የታክስ አዋጅ፣ ደንብ እና መመሪያዎች ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በገቢዎች መምሪያ የታክስ ትምህርት ኮሙኒኬሽን እና ቅሬታ አጣሪ አስተባባሪ አቶ ተካልኝ ጽጌ ረቂቁን ባቀረቡበት ወቅት አዋጁ የግብር አከፋፈል ሥርዓት ይበልጥ ፍትሃዊ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያዎች እንደሆነ በገለፃቸው አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በህገወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩና ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ
በጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ
የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ ሊውል እንደሚገባ ተገለጸ