በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ በፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ስራ ላይ የተሰማሩ  አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናገሩ

በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ በፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ስራ ላይ የተሰማሩ  አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ በፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ስራ ላይ የተሰማሩ  አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በ1ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ 10ሺህ የአቮካዶ ችግኝ እና የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ገልጿል፡፡

በፍራፍሬ ልማት ላይ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አሸናፊ ዳይሻዳና ይርጋለም አስፋው በበኩላቸው ዘርፉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ዘላቂ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን ተረድተው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሙዝ፣  ማንጎ እና አቮካዶ ልማት ላይ በስፋት ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን የጠቀሱት አርሶ  አደሮቹ የገበያ ትስስር አለመኖርና የህገ-ወጥ ደላላ መበራከት አሉታዊ ጫና እያሰከተለ መሆኑንም  አንሰተዋል፡፡

የኦይዳ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ምክትል  ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተረፈ ወንድማገኝ  እንደተናገሩት፤ በ1ሺህ 225 ሄክታር መሬት ላይ 10ሺህ በላይ የተሻሻሉ እና የተዳቀሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው፡፡

የሙዝ ዝርያዎች  ከአርሶ አደር ማሳ ወደ አርሶ አደር ማሳ  የማሰፋት ሥራ እየተሰራ  እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

ባሳለፍነው አመት ከ20ሺህ በላይ የአቮካዶ ችግኞች በተመረጡ ቀበሌያት የተተከለ መሆኑን ጠቁመዋል።

30″40″30″ ፍራፍሬ ልማት ስራን ከሌማት ትሩፋት ፕሮጀክት ጋር በማስተሳሰር የሚተገበር መሆኑን የተናገሩት የኦይዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተገኝ አበበ በተለይ ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ሌሎችም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶች በሰፋት መመረቱን አንሰተው ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከግብርናው ሴክተር የሚቀርቡ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ ከምግብ ፍጆታ ባሻገር ተጨማሪ ለገበያ ማምረት እንደሚገባ አስተዳዳሪው አሳስበው  በግብይት ሥርዓቱ የሚሰተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን