“ተገልጋዮችን በቅንነት ካላገለገልኩኝ ቅር ይለኛል” – አቶ ኪሩቤል ዘካሪያስ
በአብርሃም ማጋ
አቶ ኪሩቤል በርዕሱ የተጠቀሰውን የግል ሃሳባቸውን ሲያብራሩ “ለተገልጋዮች እንጂ ለራሴ ጥቅም ብዙም ቦታ አልሰጥም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በዋናነት ለሰዎች በጐ ነገር ማድረግ እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ፡፡ የሰው ልጅ ሲቸገር ማየት በፍፁም ያልተቸሩት ባህሪያቸው ነው፡፡
በመሆኑም በእሳቸው ዘንድ ቀርቦ ያልተፈታ ጉዳይ መኖሩን እንደማያስታውሱም ይናገራሉ፡፡ በኃላፊነት በሰሩባቸው ጊዜያት በሠራተኞች ዘንድ ቅሬታዎች ሲፈጠሩ ቅራኔ የተፈጠረባቸውን አካላት በማገናኘት አባታዊ እርቅ እንደሚፈጥሩም በአንደበታቸው አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ ባሻገርም በርካታ ዓመታትን በመረብና በእግር ኳስ ተጫዋችነት ባሳለፉባቸው ወቅት ከባልደረቦቻቸውና ከአለቆቻቸው ጋር ተጣልተውና ተቀያይመው እንደማያውቁም ያብራራሉ፡፡
ታዲያ በዚህ መነሻችን አቶ ኪሩቤል ዘካሪያስ ማን ናቸው? የሚለውን ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አቶ ኪሩቤል ዘካሪያስ በሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ቦርቻ ወረዳ በቆራንጐገ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሾንዶሎ ጐሮ በሚባል መንደር በ1957 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
አስተዳደጋቸውም እንደማንኛውም አርሶ አደር ልጅ ነበር፡፡ በልጅነታቸው ጥጆችና ፍየሎችን በማገድ፣ የማገዶ እንጨት ሰብሮ በማምጣት፣ የቻሉትን ያህል የእርሻ ሥራ በመስራት፣ አደግ ሲሉም በበሬ እያረሱ አባታቸውን እያገዙአቸው ነበር ያደጉት። ለቤተሰቦቻቸውና ለጐረቤቶቻቸው በመታዘዝና በመላላክ ተወዳዳሪ አልነበራቸውም፡፡
ትምህርት ቤት የገቡትም በልጅነታቸው ሲሆን በቦርቻ ወረዳ ፉላሣ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥር በተከፈተው ትምህርት ቤት ገብተው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ተም ረዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ ከሁለቱ መኖሪያ ቀዬአቸው አንድ ሰዓት የሚያስኬድ በመሆኑ በእግራቸው እየተመላለሱ ነበር የተማሩት፡፡
ትምህርት ቤቱ የእግርና የመረብ ኳስ ሜዳና ኳሶችንም በተገቢው ሁኔታ ያሰናዳ በመሆኑ ከትምህርት ሰዓት ውጭ ኳስ በመጫወት ያሳልፉ ነበር፡፡
በመሆኑም በእግርና በመረብ ኳስ ጐበዝና ብቁ ከመሆን ወደ ኋላ አላሉም፡፡ በሁለቱም ስፖርቶች ታዋቂና አንቱ የተባሉ ሰው ለመሆን ሲበቁ መሠረቱ ትምህርት ቤቱ መሆኑን አበክረው ይናገራሉ፡፡
በፉላሣ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ቻሉ፡፡ ሆኖም ትምህርት ቤቱ ከ6ኛ ክፍል በላይ ስለማያስተምር 7ኛ ክፍልን ለመማር ወደ ሐዋሣ መጥተው መማሩ የግድ ሆነባቸው፡፡ ወደ ሐዋሳ መጥተው የገቡት በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር ባለው ኮምቦኒ ት/ቤት ነበር፡፡
በኮምቦኒ ት/ቤት የ7ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እያሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመረብ ኳስ ቡድን ሐዋሣ መጥቶ በኮምቦኒ ት/ቤት ውስጥ ልምምድ ማድረግ ይጀምራል፡፡
በመሆኑም እሳቸው በነበራቸው ፍቅርና ችሎታ አብረዋቸው ልምምድ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ባሳዩት ከፍተኛ ችሎታ በአሰልጣኙ ተመዝነው ቡድኑ አዲስ አበባ ሲመለስ አብረዋቸው ይሄዳሉ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱም ለአንድ ወር ያህል ትምህርት ቤቱን አስፈቅደው ነበር፡፡
ቡድኑ በቻይና ሃገር የመረብ ኳስ ግጥሚያ ከአቻ ቡድን ጋር ለማድረግ ሲሄድ እሳቸው ሳይመለመሉና ሳይሄዱ ቀሩ፡፡ ይህም የሆነው ችሎታ ስለአነሳቸው ሳይሆን ዕድሜያቸው ገና 16 ብቻ በመሆኑ ነበር፡፡ በወቅቱ ለግጥሚያ የሚመለመሉት ከ18 ዓመት በላይ የሆኑት ብቻ ነበሩ፡፡
በዚሁም ተመልሰው ወደ ሐዋሣ ከተማ መጥተው የ7ኛ ክፍል ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ቀጠሉ፡፡ የ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በኮምቦኒ ት/ቤት እየተማሩ ሳሉም የወቅቱ የሲዳሞ ክፍለ ሃገር የእግር ኳስ ቡድን ሲመሠረት እሳቸውም ከተጫዋቾቹ አንዱ ለመሆን በቁ፡፡
በኮምቦኒ የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው በጥሩ ውጤት ወደ 9ኛ ክፍል ተዛውረው ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በታቦር አጠቃላይ ሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቅቀዋል፡፡
በ1972 ዓ.ም ላይ በት/ቤቱ የ1ዐኛ ክፍል ተማሪ እያሉ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የመረብና የእግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድሮች ይጀምራሉ፡፡
በወቅቱ በሁለቱም ስፖርቶች ኮከብ ተጫዋች ስለነበሩ በቀዳሚነት በትምርት ቤቱ ሁለት የመረብና የእግር ኳስ ቡድን ተመሥርቶ ልምምድ ያደርጋሉ፡፡
በእርግጥ የትምህርት ቤቶች ውድድር ለእሳቸው እንግዳ ነገር አልነበረም፡፡ ቀደም ሲል በፉላሣ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ እያሉ ከተለያዩ ካቶሊክ ት/ቤቶች የደርሶ መልስ ግጥሚያ እያደረጉ ከፍተኛ ልምድ ቀስመዋል፡፡
በ1ኛ ደረጃ እያሉ በት/ቤታቸው ተሰልፈው የገጠሙአቸው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ት/ ቤቶች ለአብነት በወላይታ ከሶዶና ከጫርቾ፣ በዲላ ከደቦስኮ፣ አራሞ፣ በአለታ ወንዶ ከሻፍናና ከደንጐራ፣ በሐዋሣ ከቱሎና ከኮምቦኒ ካቶሊክ ት/ቤቶች ጋር እየገጠሙ ከፍተኛ ልምድ አካብተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት በታቦር ት/ቤት በሁለቱም ስፖርቶች በብቸኝነት ሲመለመሉም በደስታ ተቀብለው ልምምድ ሲያደርጉ ቀዳሚ ሚና ከመጫወት ያገዳቸው አልነበረም፡፡
በዚሁም መሠረት ት/ቤታቸው በሲዳሞ ክ/ሃገር ካሉት ከሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ት/ ቤቶች በሁለቱም ስፖርቶች ገጥሞ የአሸናፊነት ድል ሲቀዳጅ የእሳቸው ሚና ከፍተኛ ነበር። እሳቸው በብቸኝነት በሁለቱም ስፖርቶች እኩል ችሎታ ሰንቀው የተጫወቱት ሚና ጥንካሬያቸውን በማጉላት በአብዛኞቹ ዘንድ አግራሞትንና አድናቆትን እንዲያተርፉ አስችሎአቸዋል፡፡
በተለይም በመረብ ኳስ በከፍተኛ ደረጃ ወደላይ የመዝለል ችሎታቸውን ተጠቅመው ዘለው ኳሷን ወደታች (ቀበራ) ሲመቱ የተመልካቾች ልብ አብሮ ይዘላል። እሳቸው ኳስ ለመቅበር ሲዘሉ ተመልካቾች ኳሷ እስክትመታ ድረስ ከ1 እስከ 3 ቁጥሮችን መቁጠር የተለመደ ተግባር ነበር፡፡ የመቱት ኳስ ውጤት አልባ ሲሆንና በተቃራኒው ቡድን ሲመለስ ማየት ዘበት ነበር፡፡
ከዚህ በመቀጠልም የታቦር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከጋሞ ጐፋ፣ ከባሌ፣ ከሲዳሞና ከአርሲ ክ/ሃገራት አሸንፈው ከመጡ ት/ቤቶች በባሌ ጐባ ከተማ በሁለቱም ስፖርቶች ውድድር አድርጐ ሻምፒዮን መሆን ቻለ፡፡
በመጨረሻም በሃገር አቀፍ ደረጃም የአሸናፊዎች አሸናፊ እና የዋንጫ ተሸላሚዎችን ለመለየት በአዳስ አበባ ከተማ በሁለቱም ስፖርቶች በተደረገው ውድድር ት/ቤቱ በመረብ ኳስ የአሸናፊነት ድል ተቀዳጅቶ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡ በዚህን ወቅት የመጨረሻዋና የ15ኛዋ ነጥብ የተቆጠረችው እሳቸው ዘልለው የመቱት ቀበራ/ስማች/ እንደሆነም ከአንደበታቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡
ይህ ዋንጫ አሁንም በት/ቤቱ ውስጥ ሲገኝ የእሳቸው አሻራ ከፍተኛ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ በዚህ ስኬቱ ት/ቤቱ ኢትዮጵያን ወክሎ በቱኒዚያ በተካሄደ የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና ውድድር ላይ እንዲሳተፍ ዕድሉን አግኝቶ 3 ቀናት ሲቀሩት ሀገሪቷ ከቱኒዚያ ጋር የነበራት የፕሮቶኮል ስምምነት በመሰረዙ ቀርቷል፡፡
ከዚህ በመቀጠልም የሲዳሞ ክ/ሀገር የመረብና የእግር ኳስ ቡድን ሲቋቋም እሳቸው በቀዳሚነት ተመልምለው ወደ ጨዋታ ገብተው ለ8 ዓመታት ያህል በመጫወት ላቅ ያለ ሚና ተወጥተዋል፡፡
በወቅቱ በ1975 ዓ.ም በሐዋሣ እርሻ ልማት ክለብ ውስጥ በቋሚነት ተቀጥረው በሁለቱም ስፖርቶች እየተጫወቱ እንደነበርም አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ውጭም የሐዋሣ ከነማ ሲመሠረትም ተቀጥረው ተጫውተዋል፡፡ በምእራብ ሸዋ እግር ኳስ ክለብም ውስጥም ተቀጥረው ለተወሰኑ ዓመታት ሠርተዋል፡፡
አቶ ኪሩቤል ዘካሪያስ በዋናነት በመረብና በእግር ኳስ ይታወቁ እንጂ በሌሎች ስፖርቶችም የማይናቅ ችሎታ አላቸው፡፡
ለአብነት ያህል በቅርጫት ኳስ፣ በከፍታና በምድር ዝላይ፣ እንዲሁም በሩጫም ጥሩ ችሎታ ነበራቸው፡፡ ሁሉንም ዓይነት ስፖርት በአንዴ ማስኬድ ስለማይቻል ብቻ ነበር ወደ ሁለቱ ያዘነበሉት፡፡
አቶ ኪሩቤል በአጠቃላይ በትምህርት ቤት ቆይታቸው በስፖርት ዓለም ያሳለፏቸው ዓመታት ሳይቆጠሩ በክለቦች ውስጥ ብቻ ለ12 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በ1984 ዓ.ም ከእርሻ ክለብ ወጥተው ወደ ሌላ ቢሮ ተቀጥረዋል፡፡
በ1987 ዓ.ም በቀድሞው ሲዳማ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ውስጥ የፋይናንስና አስተዳደር ሃላፊ ሆነው ይመደቡ እንጂ ለሐዋሣ ከነማና ለሲዳማ ቡና ሙያዊና ቴክኒካዊ እገዛ ከማድረግ አልቦዘኑም ነበር፡፡
ለአብነት ያህል ሐዋሣ ከነማን በማሰልጠንና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ሰብሳቢ በመሆን፣ አሰልጣኞችን በማማከር እንዲሁም የቦርድ አባል በመሆንም ሠርተዋል፡፡ በዚህም የሐዋሣ ከነማ ከ1996 ዓ.ም እስከ 1998 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ሲያሳካ ውጤቱ ላይ የእሳቸው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡
ከዚያም በሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ ውስጥ በተመሳሳይ በማማከር እና በመምራት ከ1996 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ለ18 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡
በአጠቃላይ በስፖርቱ ዓለም በነበሩባቸው ጊዜያት በርካታ የዋንጫ ሽልማቶችን በግልና በቡድን አግኝተዋል፡፡
ለአብነት ያህል በ1972 ዓ.ም የታቦር ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትን በመወከል የመላ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውድድር ላይ ሻምፒዮና በሆኑ ጊዜ ኮከብ ተሸላሚ ነበሩ፡፡
በመላ ኢትዮጵያ እርሻና ኢንዱስትሪ በወንጂ ከተማ በተዘጋጀው ውድድር ላይ የሲዳማ እርሻ ልማት ዋንጫ ሲያነሳ ከወጣቶች ልዩ ተሸላሚ ነበሩ፡፡
በሐዋሣ ከተማ ከፍተኛ 2 ውድድር፣ ከ14ቱ ቀበሌያት የመረብ ኳስ ዋንጫ ሲያሳካም ኮከብ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡
ለዚህም አበርክቷቸው የሐዋሣ ከነማ በስፖርት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ተጫዋቾች የቀበሌ መኖሪያ ቤት ሲሰጥ እሳቸውም አንዱ ነበሩ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ውጪ የተለያዩ አገሮች በስፖርት ምክንያት ሄደዋል። ከታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ቡሩንዲ፣ ኩባ፣ ሩሲያ፣ ሀንጋሪ እና ቡልጋሪያ ቡድኖች ጋር የመረብ ኳስ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ሲደረጉም ተሳትፈዋል፡፡
የእርሻ ክለብ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ ከ4 በላይ ዋንጫዎች ክለባቸው ሲያነሳ በእግር ኳስ ተጫዋችነት ተሳትፈው ምስጉንና ሁለገብ ስፖርተኛ ተብለው ውዳሴ አግኝተዋል፡፡
አቶ ኪሩቤል ዘካሪያስ በ1987 ዓ.ም በሲዳማ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ከተመደቡ በኋላ ለ8 ዓመታት ያህል በኃላፊነት በሰሩባቸው ጊዜያት አራቱን ዓመታት በመምሪያ ኃላፊ ተወካይነት አገል ግለዋል፡፡
በተጨማሪም በእነዚህ ዓመታት ቀደም ሲል በዲፕሎማ ደረጃ የነበረውን የትምህርት ደረጃቸውን በማሳደግ በማኔጅመንት ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡
ከዚያም ወደ ቀድሞ ሲዳማ ዞን አስተደደር ተዛውረው በባለሙያነት በሲዳማ ዞን ፋይናንስ መምሪያ በሰው ሃብት አስተዳደር ውስጥ በከፍተኛ ባለሙያነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
አቶ ኪሩቤል ልዩ ባህሪያቸው ምን እንደሆነ ጥያቄ አቅርበንላቸው የሰጡን ምላሽ፦
“አገልግሎት ፈልጐ የሚመጣውን ሰው በቅንነት ካላገለገልኩኝ ቅር ይለኛል፡፡ ሁሌ ለራሴ ጉዳይና ጥቅም ብዙ ቦታ አልሰጥም፡፡ ለሰው ልጅ በጐ ነገር መሥራት ያስደስተኛል” በማለት መልካም የአገልግሎት አሰጣጣቸውን አብራርተውልናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የመስሪያ ቤቱን ሠራተኞች ባህርይ ለይተው የመረዳት ትልቅ ተሰጥኦ አላቸው፡፡
ቅሬታዎች ሲፈጠሩ ሁለቱንም በማገናኘት የተረጋጋ ባህርያቸውን በማጉላት አባታዊ ዳኝነት በማካሄድ ችግሮቹን ፈትነው ያስታርቃሉ፡፡ ይህ እሳቸው የሚሰጡት ዳኝነት ከአድሎአዊነት የነፃ በመሆኑ ዘላቂ ሰላም ይፈጠራል፡፡
አንዳንድ ሠራተኞች በሥራ ላይ ችግር ሲፈጥሩ ሲያዩ ከመቅጣት ይልቅ ለብቻው ጠርተውት በማስረጃ የተደገፉ ችግሮቹን እየገለፁ በጥንቃቄ ይመክራሉ፡፡ ምክራቸው አጥንት ውስጥ ሰርጐ የሚገባ በመሆኑ በርካቶቹ ተምረው ከስህተታቸው ይመለሳሉ።
በአጠቃላይ ሰውን የማጥቃት ባህርይ የማይታይባቸውና ከችኮላ የፀዱ ሲሆኑ በሠሩባቸው ጊዜያት ከማንም ሰው ጋር ተጣልተውና ተቀያይመው አያውቁም፡፡ የአመራር ጥበብና ብልሃትም በከፍተኛ ደረጃ ተላብሰዋል፡፡
አቶ ኪሩቤል ዘካሪያስ የሁለት ወንድና የሶስት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ አንዱ ወንድ ልጃቸው የእሳቸውን ፈለግ ተከትሎ የእግር ኳስ ተጫዋች ሲሆን አንደኛው ደግሞ የግል ሥራ ይሠራል፡፡ ሁለቱ ሴት ልጆቻቸው ደግሞ በነርስነት ሙያ ተመርቀው አንደኛዋ በሪፈራል ሆስፒታል ትሰራለች፡፡ የመጨረሻዋ ልጃቸው ገና የ11 ዓመት ስትሆን የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪ ነች፡፡
More Stories
በኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን አዘጋጅነት በደቡብ ኦሞ ዞን ያሉ የአርብቶ አደር ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ውይይት በቱርሚ ከተማ እየተካሄደ ነው
የምግብ ዋስትና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ከስራ እድል ፈጠራ ጋር በጥምረት እየተሰራ ነው – የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ
ወጥ የሆነ ሀገራዊ አንድነትና እሳቤ ኖሮን ህዝቡን አቀናጅተን እንድንመራ የሚያስችል ስልጠና አግኝተናል ሲሉ በኣሪ ዞን 3ኛ ዙር የመካከለኛ ሰልጠኝ አመራሮች ገለፁ