የህዝቡን ዘላቂ ሠላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ የፀጥታ አካላት የጋራ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ የወላይታ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

የወላይታ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ፀጥታ ምክር ቤት የ2018 ዓ.ም የ6 ወራት አፈፃፀምና የቀጣይ መሪ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻዎች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የዞኑ አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ፤ በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ለማስፈን በፀጥታ ዘርፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የፀጥታ ጉዳይ ቅንጅታዊ አሠራርን የሚፈልግ ነው በማለት ባለፉት ጊዜያት የተረጋጋና ዘላቂ ሠላም የሰፈነበት አካባቢን ለመፍጠር በተደረገው ሥራ የመጡ ለውጦች ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ በግንቦት ወር በሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሬዳት ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል።

በተለይም በዞኑ አልፎ አልፎ የሚታየውን ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድና ለመከላከል እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ሊሆን ይገባል ሲሉ አጽንኦት ስጥተዋል።

ሠላም የማስከበር ሥራ የጋራ አንድነትን የሚፈልግ ነው በማለት ለዚህም ተቀናጅቶና ተቀራርቦ መስራት ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።

የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ የሆኑት ሀምሳ አለቃ ተሰማ ኡቱላ በንግግራቸው፤ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ የህዝቡን ሠላምና ፀጥታ ለማስከበር በተሰራው ጠንካራ ሥራ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

የፀጥታ መዋቅሩ በጥንቃቄና በትጋት መመራት እንዳለበት በማንሳት የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ሀላፊነታቸውን በአገባቡ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የህዝቡን ሠላምና ፀጥታ ለማስከበር ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ጠንካራ ሥራዎችን በማስቀጠል እንደ ድክመት የታዩ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት ብለዋል።

በዞኑ አልፎ አልፎ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የህዝቦችን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።

የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ካቢኔ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የህግ የበላይነትን በማስከበር በህዝቦች መካከል አንድነትና መከባበር እንዲኖር ለማድረግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ባለፉት ጊዚያት የህግ የበላይነትን ለማስፈን የተጀመረው ሥራ አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን ያነሱት ምክትል ሀላፊው፤ የፀጥታ ሥራዎች ግልፀኝነትና ተጠያቂነት በተሞላበት መልክ መሰራት አለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዜጎች ሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር ያለውን ውስንነት ለመቅረፍ በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ መዋቅሮች ልዩ ትኩረት ይሻል ያሉት ምክትል ሀላፊው፤ በቀጣይም ዘርፉን በትኩረት ለመምራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አክለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም የህዝቡን ሠላም በተጨባጭ ለማረጋገጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እውን ለማድረግ የበኩላቸውን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ በቀለች ጌቾ – ከዋካ ጣቢያችን