ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ተግባርን እውን ለማድረግ የተቀናጀ የግብርና ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የሀድያ ዞን ግብርና መምሪያ ገለፀ

የሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊዎችና ማኔጅመንት አካላት በግቤ ወረዳ የበጋ መስኖ እና አጠቃላይ የተቀናጀ ግብርና ተግባራትን ምልከታ አድርገዋል።

የሀድያ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ሀብታሙ ታደሰ በምልከታው ወቅት እንደተናገሩት፤ በዞኑ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተቀናጀ የግብርና ተግባራት ላይ አበረታች ስራዎች ተሠርተዋል።

በምርት ዘመኑ 36 ሺህ ሄክታር ማሳ በሽንኩርት እና በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑንም ተናግረዋል።

በዚህም የተለያዩ በውሃ አማራጮችን በመጠቀም በዓመት ከሦስት ጊዜ በላይ በማምረት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የስራ ዕድል በመፍጠር ድህነትን የማሸነፍ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑም ኃላፊው ገልጸዋል።

ሁሉም አርሶ አደሮች በፍጥነት ህይወትን የሚቀይሩ ምርቶችን በክላስተር ደረጃ በማምረት ገቢያቸውን ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የግብርና ኤክስቴንሽን ስራዎችን ይበልጥ ለማሳለጥ የባለሙያዎች ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ዶ/ር ሀብታሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የግቤ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ማርቆስ ቀጭኔ በበኩላቸው በቡናና ቅመማ ቅመም፣ በእንስሳት እርባታ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፎች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በበጋ መስኖ ልማት 3 ሺህ 6 መቶ 79 ሄክታር ማሳ የዘር ሽንኩርትን ጨምሮ በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን የማስፋት ስራ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ዘርፉ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባሻገር ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር እና ገበያ በማረጋጋት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም አቶ ማርቆስ ተናግረዋል።

ለአምራቾች የምርት መሸጫ ቦታዎችን ለማመቻቸት ከዞን ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጀት እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

አርሶ አደር ፀጋዬ ቀጭኔ እና የሀብተወልድ ፍሬሶ መታሰቢያ መስኖ ልማት ባለቤት አቶ ተድላ ሀብተወልድ በወረዳው በሜጋቾ እና በኦሞጮራ ቀበሌ በበጋ መስኖ የዘር ሽንኩርት ብዜት ላይ የተሰማሩ ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ የሽንኩርት ዘር ብዜት ላይ ያደረጉት ሙከራ ተሳክቶ በአሁኑ ሰዓት በሰፋፊ ማሳዎች ላይ የሽንኩርት ዘር እያመረቱ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ የሽንኩርት ዘር በቅርበት ከማግኘቱ ባለፈ ተፈላጊነቱ በመጨመሩ የገቢ አቅማቸውን እያሳደገ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ወይንሸት አየለና ትዕግስት ወርቅነህ ከመስኖ ልማት ማሳ ለንግድ ስራቸው የሚሆን የቲማቲም ምርት በጅምላ ለመረከብ መጥተው ያገኘናቸው ነጋዴዎች ናቸው።

በተሰማሩበት ንግድ ስራ ለገበያ አቅራቢያ ካለው የመስኖ ልማት ማሳ በተመጣጣኝ ዋጋ የጓሮ አትክልቶችን ተረክበው በአካባቢው ገበያ ለሸማቹ ማህበረሰብ እንደአቅሙ በችርቻሮ እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል።

የመስኖ ልማቱ ለንግድ ስራቸው ምቹ አጋጣሚ የፈጠረና የአካባቢውን ገበያ በማረጋጋት ለሽማቾች ትልቅ ጥቅም እያስገኘ መሆኑንም አስረድተዋል።

ዘጋቢ: ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን