ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች አስተማሪ ናቸው – አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ

ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች አስተማሪ ናቸው – አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች አስተማሪ መሆናቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ገለጹ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ አመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ክልሉ በአዲስ መልክ የተዋቀረበት አንደኛ አመት በተቃረበበት ወቅት ላይ ጉባኤው መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የአደረጃጀት ለውጥ በራሱ ግብ ባለመሆኑ የህዝብን መሠረታዊ የልማት ፍላጎቶችን ለመመለስ ክልሉ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ምክር ቤቱም የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን በማከናወን ለአስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ግብረመልስ ሰጥቷል ብለዋል።

የገጠር መንገድ፣ የመጠጥ ውሃ፣ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች እና ሌሎችም ግንባታቸው ተጠናቅቀው መመረቃቸውንም አስታውቀዋል።

ይሁንና አሁንም ያልተጠናቀቁ የልማት ሥራዎች በመኖራቸው ልዩ ትኩረት ሠጥቶ በመሥራት በአፋጣኝ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ህዝብን እያማረረ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የሰንበት ገበያን አጠናክሮ ማስቀጠልና መዳከም በታየባቸው አካባቢዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።

የተገልጋይ እርካታን በቴክኖሎጂ ለመጨመር የሚደረገው ጥረትም የሚበረታታ ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ በተለይም በከተሞች አካባቢ ረጃጅም እጆች የሚስተዋሉበትን የከተሞች ፕላን ጥሰት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ህዝብን በማሣተፍ በመሠራቱ በአሁኑ ሠዓት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ህዝብ ፊቱን ወደ ልማት አዙሮ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።

ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ