የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ግብርና ልማት ቢሮ የ2018 በጀት አመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በወልቂጤ ከተማ ገምግሟል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ልክነሽ ስርገማ በዚህ ወቅት እንዳስታወቁት፤ በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በሴክተሩ በሁሉም ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት አበረታች በመሆናቸው ተደራሽነታቸውን ማስፋት ወሳኝነቱ የጎላ ነው።
በክልሉ በግብርና ዘርፍ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ በሪፖርትና በመስክ ምልከታ ወቅት ማረጋገጣቸውን በመጥቀስ፤ ይህም የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ውጤት መሆኑን ሰብሳቢዋ ወ/ሮ ልክነሽ ስርገማ አመላክተዋል፡፡
የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ በማጎልበት የህዝብ ተጠቃሚነት ለማሻሻል በምክር ቤቱ የዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ የሚሰጡ ግብረ መልሶች ከተጠሪ ተቋማትና ከማኔጅመንት ጋር መገምገም እንደሚገባ የጠቀሱት ወ/ሮ ልክነሽ፤ በተለይም መስኖ ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአፈር አሲዳማነትን በመቀነስ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ተግባር በቀጣይም በማጠናከር በዘርፉ እምርታዊ ለውጥ እንዲመዘገብ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት።
በ6 ወሩ ለሰብል ልማት ሊውል በሚችል መሬት ላይ የተተከለ ባህር ዛፍን በማስወገድ በሌላ ሰብል ለመተካት የተጀመረውን ስራ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በመድረኩ የቢሮውን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንዳሉት፤ በቢሮው 6ቱ የግብርና ዘርፍ ምሰሶዎችን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነው።
በቀጣይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶአደሩን ብሎም የመላው ማህበረሰብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ክልሉን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ከመቼው ጊዜ በላይ በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት።
ከክልሉ ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በባለፉት 6 ወራት በቢሮው በተከናወኑ ጠንካራና መሻሻል በሚገባቸው ስራዎች ላይ ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አንስተዋል።
ከክልሉ ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እና የቢሮው ማኔጅመንት አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ተግባርን እውን ለማድረግ የተቀናጀ የግብርና ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የሀድያ ዞን ግብርና መምሪያ ገለፀ
የህዝቡን ዘላቂ ሠላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ የፀጥታ አካላት የጋራ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ የወላይታ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ቦታዎች ለምተው የሚፈለገው ውጤት እንዲመዘገብ እንክብካቤ ማድረግና ከንክኪ ነፃ መሆን እንዳለባቸው የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ አሳሰቡ