በአለምሸት ግርማ
የአንድ ሀገር ዲሞክራሲያዊነት ከሚረጋገጥባቸው ተግባራት መካከል ሀገሪቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፖሊሲዎች መውጣት፣ መሻሻልና መፅደቅ ይገኙበታል። በሀገራችንም የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት እየቀረቡ ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ይገኝበታል።
በውይይቱም ረቂቅ አዋጁ ከአባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን አስነስቷል። በተለይም ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ጫናው ከፍተኛ መሆኑንና ከመኖሪያ ይልቅ በንግድ ድርጅቶች ቢሆን የተሻለ እንደሆነ ነው የተነሳው።
በአንፃሩ ከመድረኩ በከተማ ንብረት ታክስ ለመበየን በመሬት ማሻሻያና በህንፃ ላይ የንብረት ታክስ እንዲሰበሰብ በማድረግ በከተሞች መካከል ያለውን ያልተመጣጠነ ዕድገትን ለማስቀረት እንደሚያስችል ተነስቷል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከተማነት ለሀገር ዕድገት መገለጫ ሆኖ የመታየቱን ያህል በሂደቱ ወደ ከተማ እየፈለሰ በሚመጣው ሕዝብና ካፒታል ክምችት ምክንያት የሚፈጠረውን ጥግግት ለማስተናገድ የሚችል የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የመሠረተ- ልማትና አገልግሎት አቅርቦት ማከናወን ፈታኝና ትልቅ አቅምን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ በከተማ ልማት ፓሊሲና ስትራቴጂ እንደተመለከተው ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ አስተማማኝ ሠላምና መረጋጋት፣ ዘርፈ ብዙ የመሠረተ ልማት አገልግሎት፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን መቅረፍ፣ ምቹ የመኖሪያ አካባቢን መፍጠር፣ ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እንዲኖር ማድረግ፣ የወጣቶች ማዕከላትን ማስፋፋት በዋንኛነት የሚጠቀሱ መፍትሔ የሚሹ የከተሞቻችን ነዋሪዎች ጥያቄዎች ናቸው
እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚቻለው ከሌሎች መካከል፣ ከተሞች አስተማማኝ የሆነ የገቢ ምንጭ ሲኖራቸው በመሆኑ የገቢ ምንጩን ማሳደግ የሚያስችል ሥራን ማከናወን አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡
የንብረት ታክስ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በአብዛኛዎቹ የዓለም አገሮች በከተማ እና በገጠር በሚገኝ መሬት ላይ “የመሬት ታክስ” በሚል ስያሜ ሲሰበሰብ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜም በዓለማችን አገሮች የከተማ መሠረተ ልማትን እና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የግንባታ ወጪ ለመሸፈን የሚውል ፋይናንስ በማሰባሰብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ የሚገኘው የንብረት ታክስ ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያም ከ1937 ዓ.ም. ጀምሮ ከንብረት ላይ በተለያዩ መጠሪያዎች መጠነኛ ክፍያ ሲሰበሰብ ቆይቷል፡፡
በአገራችን ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያት ከተሞች በተፋጠነ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኙ በመሆኑ በከተሞች ውስጥ ከሚገኘው ሀብት ውስጥ እያደገ የመጣውን የመንግሥት የወጪ ፍላጐት በተወሰነ ደረጃ ለመሸፈን የሚያስችል የተሻለ ሀብት ማሰባሰብ እንዲቻል ዘመናዊ የንብረት ታክስ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ይሆናል፡፡
በዚህም መሰረት የከተሞችን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ራሱን የቻለ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል። ከእነዚህ ጥናቶች አንዱ በንብረት ባለቤትነት ላይ ታክስ ማስከፈል የሚቻልበትን ሁኔታ የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ጥናት በፌዴራል እና በክልል ደረጃ በተቋቋሙ ስቲሪንግ ኮሚቴዎች እና የቴክኒክ ኮሚቴዎች የሚመራ ነበር፡፡
በፌዴራል ደረጃ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፤ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የገቢዎች ሚኒስቴር የተሳተፉበት ሲሆን፤ በተመሳሳይ በክልል ደረጃ የከተማ ልማት፤ የፋይናንስ እና የገቢዎች ቢሮ ተሳትፈውበታል፡፡ በእያንዳንዱ የጥናት ደረጃ የጥናቱ ውጤት ለፌዴራል እና ለክልል የቴክኒክ ኮሚቴዎች እና የስቲሪንግ ኮሚቴዎች እየቀረበ ሲመረመር እና አቋም ሲያዝበት ቆይቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በእያንዳንዱ የጥናት ደረጃ ከ 10 በላይ የሆኑ የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል አካላት ውይይት አድርገውበታል፡፡ የተለያዩ የጥናት ቡድኖች በድሬዳዋ፤ በባህር ዳር እና በመቀሌ ከተሞች ላይ የተከናወነው የናሙና ጥናት በአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና በአለም ባንክ በተቀጠሩ ባለሙያዎች እንዲገመገም ተደርጎ በጥናቱ የተገኘው ውጤት ትክክለኛነት ተረጋግጧል፡፡
በሌላ በኩል ንብረት የመገመት እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች በብቃት ለማፍራት ስርዓት ተቀርጾ በአራት ዙር ለንብረት ገማቾች በዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት የተሰጠ ሲሆን፤ ከላይ በተጠቀሱት ሶስት ከተሞች የንብረት ግመታ እና የግብር አከፋፈል ስርአት ተዘጋጅቷል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ – መንግሥት የንብረት ታክስ ለየትኛውም የመንግሥት አካል ተለይቶ ሳይሰጥ ቆይቶ የነበረ ቢሆንም፤ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 99 መሰረት የፌዴሬሽን እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ የንብረት ታክስ የመጣልና የመሰብሰብ ሥልጣን የክልል መንግስታት እንዲሆን፤ የንብረት ታክስ አጣጣል የተጣጣመ እንዲሆን ማድረግ እንዲቻል የንብረት ታክስን ማእቀፍ የሚወስን አዋጅ የፌዴራል መንግስት እንዲያወጣ እና ክልሎች ይህንን አዋጅ ተከትለው የየራሳቸውን የንብረት ታክስ ህግ እንዲያወጡ ወስነዋል። በዚህም መሰረት በፌደራል መንግስት የሚወጣው የንብረት ታክስ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል።
የንብረት ታክስ መጣል አስፈላጊነትን በሚመለከት የከተማ ነዋሪውን ኑሮ ለማሻሻል በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት የሚያስፈልጋቸው ወጪ ከተሞቹ ከሚሰበስቡት ገቢ ጋር በፍፁም የሚጣጣም አልሆነም፡፡
በሌላ በኩል በከተሞች ውስጥ የሚፈራው ቋሚ ንብረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከከተሞቹ ዕድገት ጋር እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የክልል መንግሥታት ከዚህ ሀብት ተገቢውን ድርሻ በታክስ አማካኝነት እየሰበሰቡ አይደለም፡፡ በንብረት ታክስ አማካኝነት የሚሰበሰበው ገቢ በከተማ ውስጥ ያለውን በከፍተኛ ሁኔታ የተራራቀ የኢኮኖሚ ደረጃ ለማቀራረብ ጭምር ከፍተኛ እገዛ ሊኖረው የሚችል ቢሆንም ይህንን ለማሟላት አልተቻለም።
በአገራችን የሚገኙ ከተሞች ከመሬት ጋር የተያያዘ ንብረትን ለወጪያቸው መሸፈኛ የሚሆን ገቢ በመሰብሰብ ረገድ በተገቢው ሁኔታ አልተጠቀሙበትም፡፡ በአጠቃላይ የአገራችን ከተሞች አብዛኛውን ወጪያቸውን የሚሸፍኑት የክልል መንግስት ከፌዴራል መንግስት ከሚያገኙት የበጀት ድጋፍ ድርሻ እንዲሁም ከክልል መንግሥት በገቢ ግብር፣ በተጨማሪ እሴት ታክስ/ ተርንኦቨር ታክስ አማካኝነት ተሰብስቦ ከሚያገኙት ድጎማ ነው። በመሆኑም ከመሬት ጋር ከተያያዘ ንብረት መንግሥት የሚያገኘው ገቢ እጅግ በጣም አነስተኛ በመሆኑ በመሬት እና በሕንፃ ላይ ዋጋን መሠረት ያደረገ ዘመናዊ የንብረት ታክስ መጣል አሰፈላጊና ወቅታዊ ይሆናል፡፡
በከተሞች ውስጥ የሚገኘው ንብረት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህ የቋሚ ንብረት ዋጋ (እሴት) መጨመር በክልል እና በማዘጋጃ ቤት ደረጃ የሚከናወኑ የመሰረተ-ልማት አቅርቦት ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡
ይሁን እንጂ የንብረቱ እሴት መጨመር ተጠቃሚ የሆነው የንብረቱ ባለቤት የሆነው ሰው ወይም ድርጅት የከተማው አስተዳደር ለመሰረተ-ልማት ግንባታ ሥራዎች የሚያወጣውን ወጪ በመጋራት ረገድ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ በመሆኑም ከተሞች የመንግስት አገልግሎቶችን እና የመገልገያ ቦታዎችን በተሻለ ጥራት፤ በዘመናዊ ዘዴ እና ከፍ ባለ ጥራት ለማቅረብ፤ ለማደስ እና ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ወጪ በንብረት ዋጋ ማደግ ምክንያት ከሚጣል ታክስ እንዲሰበስቡ ለማድረግ የንብረት ታክስ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
አንዳንድ አገሮች የንብረት ታክስ ከመሬት እና ከህንጻ በተጨማሪ በተሽከርካሪ፤ በማሽነሪ፤ በአክሲዮን፤ በቦንድ ወ.ዘ.ተ ላይ እንዲከፈል ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ከመሬት እና ከህንጻ ወጪ በሌሎች ንብረቶች ላይ የንብረት ታክስ እንዲጣል ማድረግ ኢኮኖሚው ሊሸከመው የሚችል ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑም ታክሱ በከተማ ውስጥ በሚገኝ መሬት፤ በመሬት ማሻሻያ እና በህንጻ ላይ ብቻ እንዲጣል ተደርጓል።
የአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን በሚመለከት የንብረት ታክስ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ በሚገኝ መሬት፤ የመሬት ማሻሻያ እና ህንጻ ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል። ይህም የኢትዮጵያ ህዝቦች እና ብሄር ብሄረሰቦች አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት በህገ-መንግስቱ የገቡትን ስምምነት ከግብ ለማድረስ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ በታክሱ ምክንያት ካፒታል ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው እንዲሸጋገር በማድረግ በክልሎች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ያልተመጣጠነ እድገት መከላከል ያስችላል።
አዋጁ በሁሉም አካባቢዎች በተጣጣመ ሁኔታ ሊተገበሩ የሚገባቸውን መሰረታዊ የንብረት ታክስ ድንጋጌዎች ብቻ የሚይዝ በመሆኑ፤ ክልሎች ይህንን አዋጅ መሰረት በማድረግ ከተጨባጭ ሁኔታቸው ጋር በተጣጣመ አኳኋን የየራሳቸውን የንብረት ታክስ ህግ እንዲያወጡ ይጠበቃል። ለዚህም እንዲያግዝ የገንዘብ ሚኒስቴር ክልሎች በሞዴልነት የሚጠቀሙበት የህግ ረቂቅ በማዘጋጀት ለክልሎች ያሰራጫል። ይህንን ሞዴል ህግ እና በአዋጁ የተዘረዘሩትን የንብረት ታክስ አጣጣል መርሆዎች እና ሌሎች ድንጋጌዎች በመከተል የክልል መንግስታት የንብረት ታክስ ህግ ያወጣሉ።
የንብረት ታክስ አጣጣል ፍትሀዊ እና ከመክፈል አቅም ጋር የተዛመደ እንዲሆን ለማድረግ ከተሞችን፤ በከተማ ውስጥ ያለውን መሬት እና ህንጻዎችን በደረጃ እና በአገልግሎት አይነት መመደብ አስፈላጊ ይሆናል። በዚህም መሰረት ከተሞች ቻርተር ያላቸው እና የከተማ አካባቢ አስተዳደር ተብለው እንደሚመደቡ፤ የክልል መንግስታት የከተማ እና የመሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሚያወጣውን መስፈርት መሰረት በማድረግ ቻርተር ያላቸውን ከተሞች እና የከተማ አስተዳደሮችን በየፈርጁ እንደሚመድቡ በአዋጁ ተመልክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ በየፈርጁ በተመደቡት ከተሞች ውስጥ ያለውን ቦታ ክልሎች በደረጃ ከፋፍለው በመመደብ ይህንኑ ህዝቡ እንዲያውቀው ያደርጋሉ። በሌላ በኩል በደረጃ በተመደበው የከተማ መሬት ላይ ለተገነባው ህንጻ የከተማው አስተዳደር የሚሰጠው አገልግሎት ህንጻው በሚሰጠው አገልግሎት አይነት የሚለያይ በመሆኑ ህንጻዎች በአዋጁ በተመለከተው መሰረት የመኖሪያ፤ የማምረቻ ኢንዱስትሪ፤ የንግድ፤ የማህበራዊ አገልግሎት ወ.ዘ.ተ ተብለው የሚመደቡ ሲሆን፤ ከማምረቻ ኢንዱስትሪም በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ስጋት የሚያስከተለው ኢንዱስትሪ ተለይቶ ይመደባል። በመሆኑም በክልል መንግስታት በንብረት ላይ የሚጣለው ታክስ ምጣኔ ይህንን ዝርዝር አመዳደብ እና የሚወጣውን ደረጃ መሰረት በማድረግ እንዲለያይ ይደረጋል።
የንብረት ታክስ ለማስከፈል መሰረት የሚሆነውን ዋጋ በሚመለከት አገሮች የተለያየ አስራርን ይከተላሉ። በዚህም መሰረት የንብረቱ የኪራይ ዋጋ፤ የንብረቱ ጠቅላላ የገበያ ዋጋ እንዲሁም ከንብረቱ የገበያ ውስጥ የተወሰነው መቶኛ ለንብረት ታክስ መሰረት ሲሆን ይታያል። የንብረት ታክስ ማስከፈያ ምጣኔም የተመረጠውን የንብረት ታክስ መሰረት በመከተል ከፍ ወይም ዝቅ ይደረጋል። ለንብረት ታክስ መሰረት ሊሆኑ ከሚችሉ አማራጮች ውስጥ በአብዛኛው የአለም አገሮች የሚሰራበት የገበያ ዋጋ ሲሆን፤ በሙሉ የገበያ ዋጋ ወይም ከገበያ ዋጋ ውስጥ የተወሰነው መቶኛ ለታክሱ መሰረት እንዲሆን ሲደረግ ይታያል።
በአገራችን ስራ ላይ እንዲውል የተመረጠው ከገበያ ዋጋ ውስጥ የተወሰነው መቶኛ ለታክሱ መሰረት እንዲሆን ማድረግ ነው። ለዚህም ምክንያቱ የንብረት ታክስ እንዲከፈል የሚደረገው የንብረት የገበያ ዋጋ እንዲያድግ ምክንያት ከሚሆኑት መካከል የከተማ አስተዳደሮች የሚያከናውኗቸው የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች፤ የጸጥታ አገልግሎቶች ወዘተ. ዋንኛው በመሆናቸው ታክሱ በጠቅላላው የንብረቱ ዋጋ ላይ ሳይሆን ከንብረቱ የገበያ በተወሰነው መቶኛ ላይ እንዲሆን መደረጉ ምክንያታዊ ያደርገዋል፡፡ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በከተሞች የንብረት የገበያ ዋጋ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በሙሉው የገበያው ዋጋ ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን መደረጉ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫናን የሚያስከትል ሆኖ በመገኘቱ ነው። ይሁን እንጂ የንብረት ታክስ የማስከፈያ መጣኔ ተፈጻሚ የሚሆንበት የገበያ ዋጋ መቶኛ የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ከፍ ወይም ዝቅ ማለት የሚገባው በመሆኑ መቶኛውን የመወሰኑ ስልጣን በውክልና ለገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሰጥ ተደርጓል።
ይቀጥላል…
More Stories
“ሳንቲም ሲጥሉልኝ አመስግኜ ነው የምመልሰው” – ወጣት ማህቶት በለጠ
“ጥበብ ነገሮችን በተለየ መንገድ ማየት መቻል ነው” – ተወዛዋዥ ተስፋ ጽዮን ንጉሴ
ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!