የግል ጤና ተቋማት ሕገ-ወጥነትን በማስቀረት ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
የክልሉ የግል ጤና ተቋማት አሰሪዎች ማህበር የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ “ፍትሃዊ የፈውስ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ማረጋገጥ ” በሚል መሪ ቃል ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን በጂንካ ከተማ አካሂዷል።
የአሪ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስፋው ዶሪ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልክት አስተላልፈው የግል ተቋማት ውስንነቶችን በመቅረፍ የማይተካ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ እንደገለፁት፤ የግል ጤና ተቋማት ሕገ-ወጥነትን በማስቀረት ፈዋሽነትና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ጤና ክብካቤ ፌደሬሽን አመራር አቶ ሙላቱ ሲሳይ የግል ጤና ተቋማት በመንግስት የሚቀርቡ አገልግሎቶችን በመደገፍ ማህበረሰቡ በቅርበት ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲያገኝ ይሠራል ብለዋል።
ከክልል አስከ ወረዳ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ፍትሃዊ የፈውስ ሕክምናን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ማህበሩ እንደሚተጋ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግል ጤና ተቋማት አሠሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ መንግስቱ ደምሴ ገልፀዋል።
የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት ቅንጅታዊ ሥራን በማጠናከር የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በማህበር ተደራጅተው እንዲወጡ መድረኩ አቅም መፍጠሩን የጉባኤው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በቱርካና ሐይቅና በኦሞ ወንዝ ሙላት ለተፈናቀሉ ተማሪዎች የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረጉ