ህብረት ሥራ ማህበራት ለሀገር ብልፅግና መሪ ተዋናይ ናቸው ሲል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ገለፀ

ህብረት ሥራ ማህበራት ለሀገር ብልፅግና መሪ ተዋናይ ናቸው ሲል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ገለፀ

ሀዋሳ፣ ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህብረት ሥራ ማህበራት ከመደመር እሳቤ  የተጣመሩ በመሆናቸው ለሀገር ብልፅግና መሪ ተዋናይ መሆናቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ገለፀ።

የጋሞ ገበሬዎች አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ግብይት ኅብረት ሥራ ዩኒየን 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

ጉባኤው  “ህብረት ሥራ ማህበራት የድህነት አከርካሪ መስበሪያ ብቻ ሳይሆኑ የዜጎችን ብልፅግና ማብሰሪያ ተቋምም ናቸው” በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።

በጉባኤው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ፎላ ህብረት ሥራ ማህበራት ከመደመር እሳቤ  የተጣመሩ በመሆናቸው ለሀገር ብልፅግና መሪ ተዋናይ ናቸው ብለዋል።

ህብረት ሥራ ማህበራት መቻቻል፣ አንድነት፣ ህብረትና የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚንፀባረቅባቸው ተቋማት ስለሆኑ ህብረት ሥራን ማጠናከር የሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጫ ሥራ መሆኑን አቶ ሳሙኤል አክለዋል።

 የጋሞ ዞን ምክትል  አስተዳዳሪ እና የዞኑ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት  መምሪያ ሐላፊ  አቶ መኮንን ቶንቼ በበኩላቸው መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት ለዩኒዬን መሰረት መሆናቸውን ጠቅሰው ለጋራ እድገትና ተወዳዳሪ ለመሆን በማህበር መቀናጀት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

 የጋሞ ገበሬዎች አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ግብይት ኅብረት ሥራ ዩኒዬን ቦርድ አመራር ሰብሳቢ አቶ ሲሳይ ቦጋለ፣ የህብረት ሥራ ማህበራት እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እንዲሁም መተባበርንና አንድነትን መሰረት አድርገው መቋቋማቸውን ጠቅሰው እነዚህ ማህበራት ለሀገር ብልፅግናና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 የኅብረት ሥራ ዩኒዬኑ የሚሰራቸውን የተለያዩ ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል የተሻለ የአመራር ብቃትና ክህሎት ያለውን የሰው ኃይል የሚጠይቅ መሆኑን አቶ ሲሳይ አክለዋል።

የህብረት ሥራ የአካባቢ ፀጋዎችን በመጠቀም በማህራዊውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ለህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የጋሞ ዞን ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋፅዮን ዘነበ ናቸው።

አክለውም በዞኑ ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም ቀጣይነት ያለውን እድገት ለማስመዝገብ የለውጥ ሥራዎች እየተሰሩ እንዳሉ ጠቁመው በዞኑ የተደራጁ 975 የህብረት ሥራ ማህበራትና 3 ዩኒየን መኖሩን ጠቁመዋል።

ዘጋቢ: አስናቀ ካንኮ ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን