“የግብርና ሥራ ሀብት የሚመነጭበት ዘርፍ መሆኑን እንዲያውቁ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው” – አቶ አበባው ገብረሀና

“የግብርና ሥራ ሀብት የሚመነጭበት ዘርፍ መሆኑን እንዲያውቁ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው” – አቶ አበባው ገብረሀና

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ አበባው ገብረሀና ይባላሉ፡፡ በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ከሀያ ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ ከህፃናት መርጃ ድርጅት ፕሮግራም መሪነት እስከ ቀድሞው የደቡብ ልማት ማህበር የፕሮግራም ዳይሬክተር እንዲሁም የልማት ማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ አሁን ላይ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ደቡብ ማዕከል አደይ ፕሮጀክት ክልላዊ ማናጀር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ በሥራ ቆይታቸው ባከናወኗቸው ተግባራት ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!

በደረጀ ጥላሁን

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ አበባው፦  እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦  ትውልድና እድገትዎ ምን ይመስላል?

አቶ አበባው፦ የተወለድኩት አርባምንጭ ከተማ ሲሆን ከሰባት ዓመቴ ጀምሮ ያደኩት በወላይታ ሶዶ ከተማ ነው፡፡ ከ2ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ወላይታ ሶዶ በሚገኙት በትግል ፍሬ 1ኛ ደረጃ፣ ሶዶ በር አሁን ላይ ቦጋለ ዋለሉ በሚባል ት/ቤት እና በሶዶ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ ትምህርት በዲፕሎማ መርሀ ግብር ከተመረኩኝ በኋላ÷ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በማናጅመንት /በህዝብ አስተዳደር/ የመጀመሪያ ድግሪዬን ሰራሁኝ፡፡ በመቀጠል ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ አድምንስትሬሽን ሁለተኛ ድግሪ የሰራሁ ሲሆን በተጨማሪም በኮሚኒቲ ዴቨሎፕመንት ሌላ ሁለተኛ ድግሪ (ማስተርሴን) በመስራት በከፍተኛ ውጤት አጠናቅቄያለሁ፡፡

ከዚህ ሌላ የተለያዩ ኮርሶችን በሀገርና ከሀገር ውጪ የወሰድኩ ሲሆን በአጠቃላይ ከ20 ዓመታት በላይ መንግስታዊ ባልሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች አገልግያለሁ፡፡

ንጋት፦ የሥራ አጀማመርዎ እንዴት ነበር?

አቶ አበባው፦ ሥራ የጀመርኩት በቀድሞው ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በአሁኑ ኦሞ ባንክ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሲሆን ቀጥሎ በሶዶ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ የቆንቶ ህፃናት መርጃ ፕሮግራም ላይ ነበር፡፡ በዚህ ሥራ የፕሮግራሙ መሪ ሆኜ ሳገለግል ከ700 በላይ የሚሆኑ ወላጅ አጥ ህፃናት በፕሮግራሙ ታቅፈው የተለያዩ የትምህርት እድል እንዲያገኙ በማድረግ በርካቶች በህክምና፣ በምህንድስና፣ በጋዜጠኝነትና በሌሎች የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

የህፃናቱ ወላጆች በደሳሳ ጎጆ የሚኖሩ በመሆኑ መኖሪያ ቤቶች እንዲሰራ፣ የውሃ ማዕከላት እንዲገነባ፣ በማይክሮ ፋይናንስ ታቅፈው የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የገጠር ኤሌክትርፍኬሽን በመጠቀም ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ፤ የመጠጥ ውሃ በየትምህርት ቤቱ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ሶዶ ከተማ በሚገኘው ሆህተ- ብርሀን ት/ቤት በቀድሞ ፓትሪያርክ በአቡነ ተክለ ሀይማኖት ዘመን የተሰራና ያረጀ በመሆኑ አራት መማሪያ ክፍሎች ያሉት አንድ ብሎክ ህንፃ ከነሙሉ ፈርኒቸር በማሰራት አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገናል፡፡ በተጨማሪም በሶዶ በር /ቦጋለ ዋለሉ/ ት/ቤት ለሴቶችና ወንዶች መጸዳጃ ያሰራን ሲሆን የሚኒ ሚዲያ ቁሳቁስ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም እያንዳንዱ ሶስት ተማሪ የሚቀመጥበት 182 የተማሪ መቀመጫ /ዴስክ/ አሰርተን ሰጥተናል፡፡ ለሥራችን በከተማ አስተዳደሩ እውቅናና ሽልማት ተበርክቶልናል፡፡

ንጋት፦ ከዚህ ሥራ በኋላ የሰሩት የት ነበር?

አቶ አበባው፦ መቀመጫውን ሀዋሳ ያደረገው የቀድሞው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ልማት ማህበር የፕሮግራም ዳይሬክተር ሆኜ ተቀጠርኩኝ፡፡ በዚህ ሥራ በጤናው ዘርፍ በተለይም በኤች.አይ..ቪ መከላከል ላይ በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ሴቶች ከዚህ ህይወት እንዲወጡ ፕሮጀክት በመቅረጽ ከሀላባ እስከ ጂንካ ባሉ ከተሞች በመተግበር በርካቶች ከችግሩ ወጥተው በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ የተሰራው ሥራ ውጤት የታየበት ነው፡፡ የዚህ ፕሮግራም ቀጣይ ከፒ.ኤስ.አይ ጋር በመሆን ሙሉ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በትላልቅ ከተሞች የመከላከል ሥራ ተሰርቷል፡፡

ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመሆን በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ፣ የሴቶችን አቅም የመገንባት እና በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይ በደቡብ ኦሞ አካባቢ ፕሮጀክት ተቀርጾ ተሰርቷል፡፡

በግብርናው ዘርፍ አግራ ከሚባል ረጂ ድርጅት ጋር በመሆን በግብርና ሰርቶ ማሳያ ጣቢያዎች ላይ የአርሶ አደሩን ህይወት የሚቀይሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅ አንፃር ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡

በሲዳማ አካባቢ በውሀ ሥራዎች ከፕላን ኢትዮጵያ ጋር በመሆን በሸበዲኖ ወረዳ ፉራ ቀበሌ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በደቡብ ኦሞ አርብቶ አደር አካባቢ ከሮተሪ ኢንተርናሽናል እና ሬን ፋውንዴሽን ከሚባል ተቋም ጋር አመቱን ሙሉ ውሃ ሊሰጡ የሚችሉ የአሸዋ ወንዝ ላይ በተሰሩ ግድቦች /Sand Dam/ በሀመር፣ በና ፀሀይ እና አሌ ወረዳዎች ተሰርተው እስካሁን አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡

በትምህርት ዘርፍ በደቡብ ኦሞ አርብቶ አደር አካባቢ መደበኛ ላልሆነ 7 ሺህ ጥቁር ሰሌዳ አሰርተን አርብቶ አደሮች በየቀያቸው የትምህርት እድል እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በውጪ ሀገር አገልግሎት ላይ ውለው ሙሉ ጥገና የተደረገላቸው ኮምፒውተሮች ከ1 ሺህ 500 በላይ አስመጥተን ለተለያዩ ወረዳዎች እንዲከፋፈሉ ተደርጓል፡፡ በጤና ላይም የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ለምሳሌ ለወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል 115 ዘመናዊ አልጋ፣ አልትራሳውንድ እና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች በመስጠት ሥራ እንዲጀምር ልማት ማህበሩ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለይርጋለም ሆስፒታልም ዘመናዊ ትልቅ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ከጀርመን በማስመጣት አስረክበናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በጌዴኦ አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የድጋፍ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ከዚህ ሌላ የመንጃ ማህበረሰብ አካባቢ ያለውን መገለል ለመከላከልም ከአውሮፓ ኮሚሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሰፊ ሥራ መስራት ተችሏል። እነዚህና ሌሎች ተግባራት በዳይሬክተርነት ደረጃ በነበርኩበት ጊዜ የተሰሩ ትላልቅ ሥራዎች ናቸው፡፡

ንጋት፦ በቀጣይ የተሰማሩት የሥራ መስክስ?

አቶ አበባው፦ የልማት ማህበሩ ቦርድ የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር እንድሆን በሰጠኝ ኃላፊነት ለሰባት አመታት አገልግያለሁ፡፡ በዚህም ትላልቅ ውሳኔዎች የሚፈልጉ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ልማት ማህበሩ የራሱ የሆነ የገቢ ችግር ቢኖረውም የተለያዩ የገቢ ማመንጫዎች በመጠቀም በተለይም ከውጪ ሀገራት የገንዘብ ለጋሾች ጋር በመፃፃፍ የክልሉን ህዝብ የሚጠቅሙ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡

ከልማት ማህበሩ ዋና ዳይሬክትርነት በፈቃዴ በመልቀቅ ሶሊዳሪዳድ “Solidaridad East and Central Africa” የሚባል መንግስታዊ ያልሆነ የኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ተቀላቀልኩኝ፡፡ ድርጅቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡታጅራ ላይ መሰረት በማድረግ የሚሰራ ነው፡፡ የ20 ሺህ አርሶ አደሮች ህይወት የሚቀይር በዓለም ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም ግብርናን በማስተዋወቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ /Acting Now for Food Security and Resilient Food System/ አክቲንግ ናው ፉድ ሰኪውሪቲ ኤንድ ረዚሊያንስ ፉድ ሲስተም የሚባል ፕሮግራም ላይ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ ይህን ሥራ ወድጄው የሰራሁትና አርሶ አደሮች ማሳ ድረስ በመውረድ የሰራሁበት ስለሆነ የምወደው ሥራ ነበር፡፡ ይህን ሥራ ለስምንት ወራት ሰርቻለሁ፡፡

ንጋት፦ አሁን ደግሞ በሚሰሩበት ተቋም ያለዎት የሥራ ድርሻ እና ስለስራው ይንገሩን?

አቶ አበባው፦ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል አደይ ፕሮግራም ክልላዊ ማናጀር ሆኜ እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡ ወጣቶችን መሰረት በማድረግ የሚሰራ ፕሮግራም ሲሆን በማስተር ካርድ የሚደገፍ ትልቅ ሀገር አቀፍ ፕሮግራም ነው፡፡

ፕሮግራሙ ከጀመረ እ.ኤ.አ ከ2023 መጋቢት ጀምሮ 26 ሺህ 560 የሚሆኑ ወጣቶች በግብርናው ዘርፍ የሥራ እድል እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በአራቱም ክልሎች በርካታ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ ሥራው ከወጣቶች ጋር የሚያገናኝና ለሥራ ያላቸውን አመለካከት እንዲቀየር በተለይም የግብርና ሥራ ቢዝነስ እንደሆነ እንዲያውቁ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡  ወንዞችና ሀይቆች ባሉበት አካባቢ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በጓሮ አትክልት፣ በሰብል ልማት፣ በንብ ማነብ በመሳሰሉት ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛል፡፡ ይህም ሀገር ከመቀየር አንፃር ትልቅ ፋይዳ ያለው ፕሮግራም ነው፡፡

በአምስት አመት እቅዳችን ከ110 ሺህ በላይ ወጣቶችን በአራቱ ክልሎች ወደ ሥራ ለማስገባት ታስቧል፡፡ በቀሪ ሶስት አመታት ውስጥ ቀሪዎቹን ወደ ሥራ እናስገባለን፡፡ ወደ ሥራ የገቡ ወጣቶች ውጤት ለመለካት ከየክልሉ የግብርና ቢሮ እና የሥራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ጋር በቅርበት እንሰራለን፡፡ በየ15 ቀኑ ሥራዎችን የመገምገምና የመከታተል ሥራም ይሰራል፡፡

ንጋት፦ በሰራችሁት ሥራ ወጣቶቹ ላይ ለውጥ መጥቷል ብለው ያምናሉ?

አቶ አበባው፦ አሁን ላይ ወጣቶቹ ያላቸው ገቢ ጨምሯል፡፡ ለምሳሌ ለመጀመሪያ 2 ሺህ ጫጩት የሰጠናቸው ከ45 ቀን በኋላ ሸጠው ባገኙት ትርፍ እስከ 4 ሺህ ጫጩት በማስገባት ይሰራሉ፡፡ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች ሰጥተን እንቁላሉን በመሸጥ የዶሮዎቹ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ይህም መንግስት ካስቀመጠው የሌማት ትሩፋት ሥራን የሚደግፍና ውጤታማ የሆነ ሥራ ነው፡፡

በሲዳማ አካባቢ በአትክልትና ፍራፍሬ የተሻለ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ዘሮችን አፍልቶ በመሸጥ÷ በሸበዲኖ እና ወንዶ ገነት አካባቢ የሚታዩ ሥራዎች አሉ፡፡ በሰብል ምርት በስልጤ፣ በከምባታ፣ በሀዲያ እና በዱጉና ፋንጎ በመሳሰሉት ዞኖች ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል። በስልጤ አካባቢ እስከ 30 ሄክታር መሬት ወስደው እየሰሩ ያሉ ወጣቶች አሉ፡፡

በእኛ በኩል ለወጣቶቹ የክህሎትና የአመለካከት ለውጥ ሥልጠና መጀመሪያ ላይ እንሰጣለን፡፡ በዚህም ግብርና አዋጭ ቢዝነስ መሆኑን እንዲረዱ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አስፈላጊ ግብአት እናቀርባለን፡፡ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የአንድ ቀን ጫጩት፣ እንቁላል ጣይ ዶሮ ከነመኖው እናቀርባለን፡፡ በአራቱም ክልሎች የአደይ ፕሮግራም ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ መሆኑን በሙሉ መተማመን የምንገልጸው ነው፡፡

ይህ ፕሮግራም ገንዘቡ ከለጋሽ ድርጅቶች ቢመጣም የምንሰራው ከመንግስት አካላት ጋር ነው፡፡ ተጠሪነታችንም ለግብርና ሚንስቴር ነው፡፡ ያለ መንግስት ድጋፍ መስራት አንችልም፡፡ የመንግስትን ሥራ ተክተን ሳይሆን ድጋፍ ነው የምናደርገው፡፡ በቅንጅት በመስራታችን በአራቱም ክልሎች ከፍተኛ ውጤት መጥቷል፡፡

ንጋት፦ በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ካሉ ቢገልጹልን?

አቶ አበባው፦ ይህን ፕሮግራም ስንደግፍ ወጣቶች ገንዘብ ቶሎ የሚገኝበትን ሥራ የመፈለግ አዝማሚያ ይስተዋላል፡፡ የግብርና ሥራ አድካሚ ነው ብሎ የማሰብ፡፡ ሌላው እንደ ሀገር ለወጣቶች ለግብርና ሥራ ብድር አቅርቦት ችግር መኖሩ፡፡ ይህም ሥራውን አስፍተው እንዳይሰሩ እንቅፋት ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ቦታ ሴት ወጣቶችን መልምሎ ለማቅረብ ዳተኝነት ይታያል፡፡ እንዲሁም ቶሎ ቶሎ የሚቀያየር የገበያ ሁኔታ በተለይ የግብአት ዋጋ መጨመር ውጤታማነታቸው ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ረዘም ላለ ጊዜ የዝናብ መዘግየት ምርትን የማበላሸት ሁኔታን ያስከትላል፡፡ እነዚህ በዋናነት የሚታዩ ናቸው፡፡

ንጋት፦ የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ምን ይመስላል?

አቶ አበባው፦ በተለይ ለወጣቶች በአጭር ጊዜ ገንዘብ ለማግኘት የሚደረግ አዝማሚያን ለመቀየር የሚያስችል የአመለካከት ለውጥ የሚያመጡ ሥልጠናዎች የመስጠት እና የልምድ ልውውጥ ማድረግ የመሳሰሉት እየተሰራበት ነው፡፡ የፋይናንስ እጥረትን ለማስወገድም በዋና መስሪያ ቤት በኩል ከተለያዩ ባንኮች ጋር ግንኙነት የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ አሁን ላይም ከኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ጋር የተጀመረ ሥራ አለ፡፡ ምቹ የሚባል መተግበሪያ ዲጅታል ግብርናን የሚያስተዋውቅ፤ በስልክ ብቻ ብድር እየጠየቁ ለመስራት እየተመቻቸ ይገኛል፡፡

የአየር ለውጥን በተመለከተ ዝናብ እንዳይጠብቁ መስኖን የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል፡፡ በተለይ ቆላማ አካባቢ ላይ በትኩረት ይሰራል፡፡ የዋጋ ንረትን ለመቋቋም ቀድሞ የመገመት ሥራ መስራትና ለዚያ እንዲዘጋጁ ለማድረግ የሚሰራ ይሆናል፡፡

ንጋት፦ ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለ እንዲገልጹ እድሉን ልስጥዎት፡

አቶ አበባው፦ የምንሰራበት አካባቢ የተወለድንበት፣ ያደግንበትና ብዙ ልምድ ያገኘንበት ነው፡፡ የወጣቱን ችግር የኖርንበትና ያየነው ነው፡፡ ስለሆነም የመጣውን እድል ወጣቶች እንዲጠቀሙ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በከተማ አካባቢ ያሉ ወጣቶች የተወሰነ ገንዘብ ይዘው በግብርና ዘርፍ ቢሰማሩ አንድም የሀገራቸውን ኢኮኖሚ ያሳድጋሉ፣ የግል ህይወታቸውንም ያሻሽላሉ፡፡ በአራቱም ክልሎች ያሉ ወጣቶች በተለይ አደይ ፕሮግራም የሚያቅፋቸው ከ15 እስከ 35 አመት ያሉ ወጣቶች በፕሮግራሙ መጠቀም ይኖርባቸዋል።

የአደይ ፕሮግራም በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የሚደገፍ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወስደው የሚሰሩ አሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን የመሳሰሉ አጋዥ ስላሉ ይህን እድል ተጠቅመው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም ያስፈልጋል፡፡

ወጣቶች በስደት ከመሄድ ይልቅ ሀገራቸው ላይ አልምተው መጠቀም ይችላሉ። ተግዳሮት ቢኖርም ተጋፍጠው ውጤት ያመጡ በርካታ ናቸው፡፡ በአንድ አመት ውስጥ ራሳቸውን ቀይረው ሌሎች ወጣቶችን ቀጥረው የሚሰሩትንም አይተናል፡፡ ይህን እድል ሌሎችም መጠቀም አለባቸው እላለሁ፡፡ 

ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ አበባው፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡