“የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት“
በፈረኦን ደበበ
በሰሜን አፍሪካ አንዲት ሀገር ትገኛለች፡፡ እንደ ጎረቤቶቿ በማዕድንና በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ሲሆን እነዚህን በአግባቡ በሥራ ላይ ለማዋልም መልካም ዕድሎችን መላበሷ ልዩ አድርጓታል፡፡
በበርካታ ተፈጥሮና ታሪካዊ መስህቦች የታደለችው ሀገር ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የፖለቲካ መዋቅርም ሲኖራት በመሪዎቿ ጥንካሬና ታታሪነት ሠላሟ ሳይደፈርስ ህይወቷን ማስቀጠል ችላለች። ውዝግብ የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ሲነሱ መሪዎች ሀገራዊ ዕሴትን በሚያጠናክሩ ዘዴዎች ላይ ማተኮራቸውም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ይህች ዝነኛ የሆነችው ሀገር ሞሮኮ ስትሆን ከሜዲቴራኒያን ባህርና ከአትላንቲክ ውቂያኖስ ጋር መዋሰኗም ከተለያዩ ሀገራት ጋር ወዳጅነቷን ለማጠናከር ረድቷታል፡፡ በተለይ ከውቂያኖሱ ማዶ ካለችው ስፔንና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም ጥብቅ ግንኙነት ፈጥራ ቆይታለች፡፡
በንጉሳዊ ሥርዓት የሚትተዳደረው ሀገር ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ለውጥ በማካሄድ ላይ ስትሆን አሁን እየመሯት ያሉት ንጉስም መሀመድ vl ወይም መሀመድ 6ኛ ይባላሉ፡፡ ከዛሬ 25 አመታት በፊት አባታቸው ሲሞቱ ስልጣኑን የተረከቡት ንጉሱ ሰሞኑን የንግሥና በዓላቸውንም አክብረዋል፡፡
በመርህ ደረጃ በህግ የሚመሩና ከዚህ አንጻር “ህገ-መንግሥታዊ ንጉስ” ተብለው ቢጠሩም በተለይ መከላከያ፣ ኃይማኖትና ሌሎች ሀገርን በሚመለከቱ ጉዳዮች የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ መሆናቸው የሥልጣን ወሰናቸውን ያሳያል፡፡
እንደ መረጃ ምንጮች ከሆነ በህግ ትምህርት እስከ ዶክተሬት የተማሩትና የሀገራቸውን ህገ-መንግሥት ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ ለውጦች ማምጣታቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ከቀድሞዎቹ ቅኝ ገዢዎች ባለፈ ከቻይና ሩሲያና ባህረ-ሰላጤው ሀገራት ጋር ግንኙነታቸውን እያጠናከሩት የሚገኙት ንጉሱ አስደናቂ ማህበራዊ ልማትና ዕድገት እንዳመጡ ይነገርላቸዋል፡፡
“የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት” በሚል ርዕስ አፍሪካ ኒውስ የተባለው የዜና ማሠራጫ ሰሞኑን የገለጻት ሀገር የተሳካ መዋቅራዊ ለውጥና አመቺ የንግድ ሁኔታ የፈጠረች ሲሆን የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማስፋፋቷም በአፍሪካ በመኪና ምርትና በአየር በረራ ተጠቃሽ እንድትሆን አስችሏታል ብሏል፡፡
በቅድሚያ ለምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ትኩረት አድርገው እንደተነሳሱ የሚነገርላቸው ንጉሱ ቀጥሎም ድህነትን በማስወገድና የህዝቡን ኑሮ ሁኔታ በሚያሻሽሉ ጉዳዮች ላይ አዘንብለዋል ሰብአዊ ልማትን ለማምጣት የዘረጉትን ሀገራዊ ዕቅድ ጨምሮ፡፡
ሠላምና ልማትን ለማምጣት ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ጥረት እያደረጉ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ የገጠር መሠረተ-ልማት፣ ትምህርትና ጤናን ጨምሮ በርካታ መሻሻሎች ማምጣታቸውም ተገልጿል፡፡
የመጣ ለውጡንም ሂችሚ ለህሚቺ የተባሉት ፖለቲካ ተንታኝና በጀኔቫ የዓለም ሠላም ጥናት ተቋም ኃላፊ እንደገለጹት አመርቂ ነው፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላላ ምርት በፈረንጅ አቆጣጠር ከ1999 ጀምሮ በእጥፍ ማደጉንም ተናግረዋል፡፡
የዕድሜ ጎልማሳው ንጉስ በትምህርት ዘርፍ ባለው ኢንቨስትመንትና በተማሪዎች ምዝገባ ያስገኙት ውጤት ሲጠቀስ በጤናው ዘርፍም አመርቂ እንደሆነ ተገልጿል የክብካቤ እና የተሻሻለ የህክምና አገልግሎት ስለተጀመረ፡፡
ተንታኙ ገልጸዋል እንደተባለው ሌላው ትኩረታቸው በዲፕሎማሲው መስክ ሲሆን ከቻይና፣ ሩሲያ እና ሌሎች ሀገራት ጋር የፈጠሩት ተጠቃሽ ነው፡፡ የግንኙነቱ መጠናከር ሀገሪቱ ከምዕራባዊያን ባለፈ ከሌሎች ባለ ብዙ ወገን አጋሮች ጭምር ወዳጅነት እንድትፈጥር ይረዳታል ተብሏል፡፡
ይሁን እንጂ ከዚህ የልማት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ተግዳሮቶች መኖራቸው አልቀረም፡፡ ሀገሪቱ ከምዕራባዊ ሠሀራ ጋር በገባችበት ይገባኛል ጥያቄ መነሻ ውዝግቦች አልፎ አልፎ ይሰማሉ፡፡
እንደ ሌሎች አፍሪካ ሀገራት ሥር የሰደደ ፖለቲካዊ ቀውስ ባይኖሩባትም የወጣቶች ሥራ አጥነትና የሀብት ያለመመጣጠን የመሳሰሉ ማህበራዊ ችግሮች በስፋት እንዳሉባት ይነገራል፡፡ እነዚህ መንግሥት የነደፋቸው የተለያዩ ማህበራዊ ክብካካቤና አካታችነት ዕቅዶችን እንዳያፋልሱ ሥጋት አለ፡፡
ፋና ወጊ የሆነው የሀገሪቱ ዕድገት በተግዳሮች እንዳይደናቀፍም ባለሙያው የምክር ሀሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ በማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የጀመረቻቸው ማሻሻያዎች ማጠናከር እንደሚገባትም አሳስበዋል፡፡
More Stories
“ሳንቲም ሲጥሉልኝ አመስግኜ ነው የምመልሰው” – ወጣት ማህቶት በለጠ
“ጥበብ ነገሮችን በተለየ መንገድ ማየት መቻል ነው” – ተወዛዋዥ ተስፋ ጽዮን ንጉሴ
ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!