በክረምት ወራት በወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ53ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ መሆኑን የወረዳው ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በሳምንታዊ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ኬራቴ ከተማን ሲያፀዱ አግኝተን ካነጋገርናቸው ወጣቶች መካከል ኢብራሂም ከድርና አብዱልሰመድ ያሲን፤ በክረምቱ ወራት በአካባቢ ጥበቃ፣በጤና በመንገድ መሰረተ ልማት፣የችግኝ ተከላ፣ ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ቤት የመስራትና የመንከባከብ ስራዎችን እየሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በክረምት በጎ ፍቃድ ሲተገብሩት የነበረውን የበጎ ተግባር ስራ በበጋ ወቅትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
በወረዳው በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ወ/ሮ ትበዦ መሀመድና ሹክርቴ ዲለሞ በወጣቶች የክረምት የበጎ ተግባር የመኖሪያ ቤታቸው ሙሉ ወጪ ተሸፍኖ ተገንብቶ የተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከዚህ በፊት ይደርስባቸው የነበረው ችግር በወጣቶች በጎ ተግባር የተቀረፈላቸው መሆኑን አንስተው በዚህ ተግባር የተሳተፉ አካላትን አመስግነዋል።
ሌላኛው በወረዳው በሞተር ትራፍክ አደጋ ደርሶበት በህክምና ላይ ያለው ወጣት አብዱልአዚዝ ዴታሞ የወረዳው ወጣቶች በመተባበር ለህክምና የሚሆን 3መቶ 5 ሺ ብር አሰባስበው ድጋፍ እንዳደረጉለት ተናግሯል።
ወጣት ቢኒያም ጌራ የኬራቴ ከተማ ወጣቶች ተወካይ ፣መሀመድ ሀጂ ባርጊቾ ደግሞ የወጣቶች ፌዴሬሽን አስተባባሪ ሲሆኑ የወጣቶችን መዋቅር በማስተባበር የተለያዩ የበጎ ተግባር ስራዎችን ሲከውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በአዲስ አበበ ከተማ በስልጤ ልማት ማህበር አማካኝነት እየተገነባ ለሚገኘው የስልጤ ባህልና ቢዝነስ ማዕከል የሚሆን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በተለያየ ምክንያቶች የጤና እክል ገጥሟቸው ህክምና እየተከታተሉ ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ለህክምና የሚሆን ገንዘብ በማዋጣት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልፀዋል።
በቀጣይም መሰል የልማት እና ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ላይ የወጣቶችን አደረጃጀት በማስተባበር የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን መዘጋጃታቸውን ገልፀዋል ።
በክረምት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሲከወኑ የነበሩ ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ አቶ መሀመድ ሙዜ በስልጤ ዞን የሁልባራግ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው።
በዚህም 53ሺ 4መቶ 56 የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለያዩ የስራ መስኮች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማህበራዊ አንድነትን ከማጠናከር ባለፈ ከመንግሥትና ከህዝብ ሊወጣ የነበረን 18 ሚሊየን 108 ሺ 6መቶ 92 ብር ማዳን ያስቻለ ነው ብለዋል።
ይህን ተግባር በበጋ ወራትም አጠናክሮ ለማስቀጠል ከባላድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ አቶ መሀመድ አንስተዋል።
ዘጋቢ:-አሚና ጀማል ከሆሳዕና ጣቢያችን።

More Stories
ጥራት ያለውን ትምህርት ለዜጎች ለማድረስ እየተጉ ያሉትን ባለድርሻዎች ማበረታታት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ፋይዳው የጎላ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለፀ
በሀገር በቀል ዕውቀት የሚታወቀውን የአካባቢውን እምቅ አቅም አጉልቶ በማሳየት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት ማፋጠን እንደሚገባ ተገለፀ
በሩብ ዓመቱ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ