“የባለሀብት ልጅ ነኝ ብዬ መቀመጥን አልፈለኩም” – ወ/ሮ ጌጤ ገመዳ

“የባለሀብት ልጅ ነኝ ብዬ መቀመጥን አልፈለኩም” – ወ/ሮ ጌጤ ገመዳ

በገነት ደጉ

ጥረት ለስኬት ዋነኛው መሰረት ነው። ለአንዳንዶች ግን ከቤተሰብ የሚገኝ ጥሪት የስኬታቸው መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ የዛሬዋ የእቱ-መለኛ አምድ ባለተሞክሮ ባለፀጋ ከሚባሉ ቤተሰቦች ቢወለዱም ‹‹ስኬትን በጥረት እንጂ በውርስ ማግኘት አልፈልግም›› በሚል ውጤታማ መሆን የቻሉ እንስት ናቸው። እኛም ያለፉበት የሕይወት ውጣውረድ አለንባቢያን ያስተምራል በሚል እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡

ወ/ሮ ጌጤ ገመዳ ይባላሉ፡፡ ትውልድና እድገታቸው በኦሮሚያ ክልል፣ ልዩ ስሙ ኢዴራ ጋልቻ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ነዋሪነታቸው በጌዴኦ ዞን ገደብ ከተማ ሲሆን የሁለት ሴት ልጆች እናት ናቸው፡፡

ከትዳር አጋራቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባበት ምክንያት ትዳራቸው ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ቢሆንም እንደ እናት ሁለቱንም ልጆች ፍላጎታቸውን በማሟላት አሳድገዋቸዋል። በጥሩ ትምህርት ቤት ከፍለውላቸውም እያስተማሯቸው ነው፡፡

ወ/ሮ ጌጤ የአባታቸው የንግድ ሥራ ለስኬታቸው መሰረት እንደሆናቸው ያነሳሉ፡፡ “አባቴ አርሶ አደር ነበር:፡ ከአርሶ አደርነት ሙያ ጎን ለጎን በጀመረው የንግድ ሥራ ራሱን እያሻሻለ የሙሉ ጊዜ ሥራው አደረገው፡፡ የትውልድ አካባቢው ለንግድ ሥራው ባለመመቸቱ ቤተሰቡን ይዞ አሁን ወደምንኖርበት ገደብ ከተማ መጣ” ሲሉም ሂደቱን ያስታውሳሉ፡፡

በዚህም ምክንያት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ገደብ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ተከታተሉ፡፡ እናትና አባታቸው በመለያየታቸው በቤተሰባቸው ዘንድ ለትምህርታቸው የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነበር፡፡

ቀስ በቀስም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ወደ ንግዱ በመግባት ቤተሰባቸውን ማገዝ ጀመሩ። በልጅነታቸው ወደ ንግዱ አዘንብለው ባካበቱት ልምድ ዛሬ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩና የማንንም እጅ እንዳይጠብቁ እንደረዳቸው ያስረዳሉ፡፡

በኋላም ከትምህርታቸው በተጓዳኝ በ50 ሳንቲም ሎሚ በመረከብ መሃል ከተማና መናኸሪያ አካባቢ እየዞሩ እስከ 5 ብር ድረስ በመሸጥ ሥራ ጀመሩ፡፡ ሥራውን የጥዋት ተማሪ ከሆኑ ከሰዓት እንዲሁም የከሰዓት ከሆኑ በተቃራኒው እያፈራረቁ ነበር የሚሰሩት፡፡

ከጊዜ በኋላ ትምህርታቸውን አቋርጠው ሥራውን አጠናክረው ጥቂት ገንዘብ ሲያገኙ ታላቅ እህታቸውን ፍለጋ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሶላሞ ወደ ሚባል አጎራባች አካባቢ አቀኑ፡፡ በሄዱበትም ከተማ የፍራፍሬ ንግድ በመጀመር ንግዱን አስፋፍተው ወደ ገደብ ከተማ ተመለሱ።

በ2001 ዓ.ም ትምህርታቸውን አቋርጠው ሙሉ ጊዜያቸውን ለንግዱ ሰጡ፡፡ ከዲላ ነጋዴዎች ጭነው የሚያስገቡትን አትክልትና ፍራፍሬ ተረክበው በማጣራት ወደ ስራው በስፋት መግባታቸውን ነው የነገሩን፡፡

ይሁን እንጂ በአካባቢው አባታቸው ትልቅ ከሚባሉ ባለሀብቶች መካከል መሆናቸው “እንዴት የባለሀብት ልጅ ሆነሽ ከሰዎች ጋር ትጋፊያለሽ?” በሚል ከበርካቶች ዘለፋና ነቀፌታን ለማስተናግድ እንደዳረጋቸው ያነሳሉ። ስለሁኔታው ሲያስረዱ የማይረሱትን አንድ ገጠመኝ ያስታውሳሉ፡-

“የሆነ ጊዜ አንዷ ነጋዴ ‘የባለሀብት ልጅ ሆነሽ ከእኛ እየተሻማሽ ትለቃቅሚያለሽ’ አለችኝ። ሁኔታውን መቋቋም አቅቶኝ ለጥል ተገባበዝን። ይሁን እንጂ ከዛም በኋላ የሚደርስብኝ አርፈሽ የአባትሽን ሀብት አትበይም የሚለው ስድብ ስላልቆመ በተፈጠረ ፀብ አንድ ሰው ላይ ጉዳት አድርሼ ስለተፈረደብኝ፤ መሬት ለመግዛት ያጠራቀምኩትን ገንዘብ ለእርቅ እና ለህክምና አውጥቼ ጨርሻለሁ፡፡” ከዚያን ወዲህ ከሰው ጋር መጣላት ቀርቶ ሌሎች ለፀብ ሲዳረጉ አበክረው እንደሚያስጠነቅቁ እና እንደሚመክሩ አክለዋል፡፡

“በሙሉ አቅሜ ወደ ሥራ ለመግባት ስነሳ ቆሻሻ የሚጣልበትን ሼድ በማፅዳት ነበር” የሚሉት ወ/ሮ ጌጤ ይህ ቦታ እንኳን ለሥራ በአይን ለማየት የሚያስጠላ ነበር ይላሉ። ይሁንና ለምን አፅድተን አንሰራም በሚል ከአራት ጓደኞቻቸው ጋር ተነጋግረው በማፅዳትና በማሳመር አነስተኛ የምግብ ሥራ ጀመሩ፡፡

በኋላም ከመንግስት ህጋዊ እውቅና በማግኘት “ዳራሮ” በሚል የማህበር ሥም ተደራጅተው ወደ ኢንተርፕራይዝ ጽህፈት ቤት አቀኑ፡፡ ጽ/ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ሥራ እንዲጀምሩ አገዛቸው፡፡ በወቅቱም በከተማው የአነስተኛ ምግብ አገልግሎት የሚሰጥ ሌላ ተቋም ስላልነበረ ገበያ ደራላቸው። አምስቱ የማህበሩ አባላት ሥራን ተከፋፍለው በመግባባት መሥራታቸው ደግሞ ወደ ስኬት የሚያደርጉትን ጉዞ አቀለለላቸው፡፡

“በዚህ ሁኔታ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ከሰራን በኋላ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሳችኋል በሚል ከህግ አግባብ ውጪ የመስሪያ ቦታውን ለሌሎች እንድንለቅ ተደረግን” ይላሉ፡፡ ሌሎቹ የማህበሩ አባላት በተስፋ መቁረጥ ሥራውን ለቀው ሲወጡ እሳቸው ግን የግላቸውን ምግብ ቤት በመክፈት አገልግሎት መሥጠታቸውን ቀጠሉ፡፡

ሰርቼ መለወጤን ማመን ያልፈለጉ ሰዎች ግን አሁንም አባቷ በሰጣት ገንዘብ ነው የተነሳችው በሚል ጥረቴን ከአባቴ ሃብት ጋር ሊያያይዙ ሞከሩ፡፡ “እውነት ነው! አባቴ መኪና፣ የቡና ማሳና መፈልፈያ ጨምሮ ወፍጮ ቤት ያለው ባለሀብት ነው፡፡ ነገር ግን የአባቴ ሀብት የእኔ ነው ብዬ መቀመጥን አልመረጥኩም፡፡ ምክንያቱም እኔ ሰርቼ ያተረፍኩት ሀብት ነው የእኔም የልጆቼም የሚሆነው” ሲሉ ነው የስኬት መንገዳቸው ያለተስፋ መቁረጥ መሥራታቸው መሆኑን ያጫወቱን፡፡

“የባለሀብት ልጅ ነኝ ብዬ መቀመጥን አልፈልግም በሚል እሳቤ አስፓልት ላይ ወጥቼ የጀመርኩት ሥራ ዛሬ ላይ ወደ ስኬት እየመራኝ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የገጠሙኝ ችግሮችና ፈተናዎች አበረቱኝ እንጂ ካሰብኩበት ለመድረስ አላገዱኝም” ሲሉም ፅናታቸውን ይናገራሉ፡፡

“ስራ መስራትን እወዳለሁ” የሚሉት የትጋት ማሳያዋ እንስት፤ የንግድ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት በከተማው በሚገኙ ሁለት የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ የጽዳት ሰራ በመስራት የራሳቸውንና የልጆቻቸውን ኑሮ ለማሻሻል መሞከራቸውን ያስታውሳሉ፡፡

“ጥዋት እስከ 2 ሰዓት በወር 3 ሺህ 600 ብር እየተከፈለኝ ጽዳት እሰራለሁ፡፡ ከሶስት ሰዓት በኋላ ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬ በመሸጥ ገቢዬን ለማሳደግ እሞክር ነበር፡፡ በዚህም ያሰብኩትን በማሳካት ዛሬ ላይ ደርሻለሁ” ሲሉ የተጓዙበትን የስኬት መንገድ አጋርተውናል፡፡

ከሚያገኙት ገቢ ባንክ በመቆጠብ ባጠራቀሙት ብር በተለምዶ ሞላ ጎልጃ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መሬት በመግዛት ቋሚ ንብረት ማፍራት ችለዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ቦታው ላይ አናናስ፣ አቮካዶና ቡና በመትከል ገቢ ማግኘት መጀመራቸውን ነግረውናል፡፡

በዚህ ጊዜ ጥረታቸውን ያዩት አባታቸውም ገደብ ከተማ ላይ 300 ካሬ ሜትር ቦታ በመስጠት ለልጃቸው ስኬት እጅ በመስጠት አጋርነታቸውን አሳዩዋቸው፡፡ የሚያገኙትን ዕድል ወደ ገንዘብ የመቀየር ልምዳ ያላቸው ወ/ሮ ጌጤ በስጦታ ባገኙት መሬት ላይ በአካባቢው በብዛት የሚፈለገውን የእንሰት ተክል በመትከል ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡

በእንሰት ማሳው ውስጥ ለእለት ቀለብ የሚውሉ እንደ ቦሎቄ፣ በቆሎ፣ ጎመንና የመሳሰሉትን በመትከል እየተንከባከቡ ሲሆን የድካማቸውን ፍሬ ማየት በመጀመራቸው ደስተኛ ናቸው፡፡

አሁን ላይ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ስራ የሚተዳደሩት ወ/ሮ ጌጤ ሱቃቸው በረንዳ ላይ በቆሎ እሸት እና ድንች በዳጣ በመሸጥ ገደብ ከተማ ላይ ዝናቸው እንደናኘ ነግረውናል፡፡ ከሚያገኙት ገቢ ግብርን በታማኝነት ከሚከፍሉ ዜጎች መካከል ተጠቃሽ ሆነው ለሁለተኛ ጊዜ ታማኝ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ በመሆን ተሸልመዋል፡፡

“አብዛኞቹ ነጋዴዎች ገቢዎች ሲመጡ ሱቃቸውን ሲዘጉ ይታያል፡፡ እኔ ሀገሬን እወዳታለሁ እያሉ ግብር መክፈል የማይፈልጉ ወገኖችን ሳይ እናደዳለሁ፡፡ ግብርን በወቅቱ ከመክፈል ባለፈ በአካባቢዬ የወደቁትን ሳነሳ ሀገሬን እረድቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህም ሌላ በከተማችን የታማኝ ግብር ከፋዮች ቁጥር ከጨመረ የሚስተዋለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ጨምሮ የመሰረተ-ልማት ጥያቄዎች ይመለሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት እኔ የምሰራው ለራሴ ብቻ አይደለም የሚል ፅኑ እምነት ላይ ደርሻለሁ” ይላሉ፡፡

በተለይም እርሳቸውን እያዩ በደንብ ስራ እየሰሩ ግብርን የሚሰውሩ በርካታ ነጋዴዎች ስለመኖራቸው አስታውሰው ግብር የዜግነት እና የልማት ግዴታ በመሆኑ ያለግዳጅ ግብር በመክፈል ለልጆቻችን ቅርስ እናስቀምጥ ሲሉ መክረዋል፡፡

በወረዳው ያሉ አመራሮች ጥረታቸውን እና ታማኝ ግብር ከፋይ መሆናቸውን በአርዓያነት በማንሳት እንደሚያባረታቷቸው አልሸሸጉም። “ወደፊት ትልቅ ነጋዴ በመሆን ከዚህ በተሻለ ታማኝ ግብር ከፋይ ሆኜ አካባቢዬን በማስጠራት ዝናን ማትረፍ እንፈልጋለሁ” በማለት ዕቅዳቸውን አጋርተውናል፡፡

“ብዙውን ጊዜ ሰው ያመነበትን ስራ ዓላማዬ ብሎ ሲሰራ ሞኝነት ይመስላቸዋል” የሚሉት እቱ መለኛችን፤ “እኔ ግን በየቀኑ ያለተስፋ መቁረጥ ሥራዬን ከመሥራት ባለፈ በመቆጠብ ዛሬ መድረስ ወደምፈልገው ደረጃ እየገሰገስኩ ነው” ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በአካባቢዬ የሚገኙ እናቶችም ይህን ያህል ብር አለኝ ምን ልስራ? እያሉ እንደሚያማክሯቸው አስረድተዋል። “የሚሰራ ሰው ይታመናል እና ሴቶች ቁጭ ከማለት ይልቅ ያገኙትን ሥራ ሳይንቁ በመሥራት ኑሮን ለማሸነፍ መትጋት አለባቸው” ሲሉ መክረዋል፡፡