“መታወቂያው የአንድ ሰው ልዩ መለያ ነው” – አቶ መፈክር ጥላሁን

በመለሰች ዘለቀ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ መፈክር ጥላሁን ይባላሉ፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ሪጅን ዳይሬክት ቻናል ሴልስ ማናጀር ናቸው፡፡ በማርኬትንግ የትምህርት ሙያ የመጀመሪያ ድግሪ ያላቸው ሲሆን በድርጅቱ ከ20 አመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ ብሄራዊ ድጅታል መታወቂያ ምንነት፣ጠቀሜታ እና በምዝገባ ሂደት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን እንግዳ በማድረግ ጋብዘናቸዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ንጋት፡- ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሠግናለሁ፡፡
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሠግናለሁ፡፡
ንጋት፡- ዲጅታል መታወቂያ ማለት ምን ማለት ነው?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- ዲጂታል መታወቂያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዋሪዎችን የተመጠነ የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃ በመሰብሰብ አንድን ሰው ልዩ በሆነ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ስርዓት ነው። የፋይዳ ቁጥር/ዲጂታል መታወቂያ/ የያዙ ነዋሪዎች በሀገሪቱ ውስጥ ማንነትን በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት ያስችላል። የታሰበው የተለያዩ የህዝብ አገልግሎቶችን ለማግኘት እንደ ብሔራዊ እና የግል መለያ ሆኖ እንዲያገለግል ነው።

አላማው በሀገር አቀፍ ደረጃ የባዮሜትሪክ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓትን በመተግበር ሁሉም ብቁ የኢትዮጵያ ዜጎች እና ነዋሪዎችን መመዝገብ ነው፡፡

ንጋት፡- የመታወቂያ ምዝገባው ሂደት ምን ይስላል?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ፣ ምዝገባና የማረጋገጥ አገልግሎትን በተመለከተ በተመዝጋቢዎች ነፃ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ምዝገባ የሚከናወን ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ተመዝጋቢዎች ከተመዘገቡ በኋላ መረጃዎቻቸውን በዘላቂነት መቆለፍ ቢፈልጉ ይህንንም አማራጭ ያካተተ ነው። ማንኛውም ተመዝጋቢ ከመመዝገቡ በፊት የፈቃድ መስጫ ፎርም መሙላት አለበት። በፈቃድ መስጫ ሰነዱ ላይ ተመዝጋቢው የሚሰጣቸው መረጃዎች ለምን አገልግሎት እንደሚውሉ፣ እንዲሁም ምዝገባው ሙሉ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ ይገልጻል። ተመዝጋቢዎች ሲመዘገቡ ብቻ ሳይሆን የማረጋገጥ አገልግሎት ሲያገኙም በሙሉ ነፃ ፈቃዳቸው ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል፡፡

ተመዝጋቢዎች በምዝገባ ወቅት ባዮሜትሪክና ዴሞግራፊያዊ መረጃ መስጠት አለባቸው። በዚህም አግባብ የአሥር ጣት አሻራ፣ የዓይን አሻራና የተመዝጋቢው ፎቶ እንደ ባዮሜትሪክ መረጃ የሚወሰድ ሲሆን ሙሉ ስም፣ የትውልድ ቀን፣ የመኖሪያ አድራሻ፣ ዜግነትና ፆታ እንደ ዴሞግራፊክ መረጃ ይወሰዳል።

ተመዝጋቢዎች መረጃዎቻቸው ወደ ማዕከላዊ ዳታቤዝ ከገቡ በኋላ ባለ 12 አኃዝ ልዩ ቁጥር በስልክ መልዕክት የሚላክላቸው ሲሆን፣ እያንዳንዱ ተመዝጋቢ ያለው ቁጥር ከሌላ ተመዝጋቢ የተለየ ነው። ይህም አንዴ ጥቅም ላይ ከዋለ ለሕይወት ዘመን የማይቀየርና ደግሞ ጥቅም ላይ የሚውል ልዩ ቁጥር ነው። እንደ ግብር ከፋይ (TIN) እና መሰል መለያዎችም በልዩነት አንድ ለአንድ (1:1) ተያያዥ ይሆናል። ከስልክ መልዕክት በተጨማሪም በስልክ አፕልኬሽንና በመታወቂያ ካርድ ታትሞ ለዜጎችና ነዋሪዎች ለማቅረብ እየተሠራ ነው።

ንጋት፡- መታወቂያው ምን አይነት ጠቀሜታ አለው?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ግለሰቦች ማንነታቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችል እና ለአገልግሎት አቅራቢዎች ታማኝ እና ፈጣን የሙሉ ጊዜ ዲጂታል ማረጋገጫ በመሆን የሚያገለግል የመታወቂያ ሥርዓት ነው። ጠቀሜታውም፦ መሠረታዊ “የመታወቅ መብትን” የሚሰጥ ትክክለኛ እና ሕጋዊ የማንነት ማረጋገጫ ነው።

በሁሉም አካባቢዎች የተለያዩ የገቢ ደረጃ ላይ ላሉ እና የከተማ መስፋፋት ውስጥ ለሚካተቱ ማህበረሰቦች፣ ፍትሃዊ ተደራሽነት እንዲኖር የሚያስችል የመታወቂያ ሥርዓት ነው። በባዮሜትሪክ ላይ የተመሠረተ መለያ ሲኖርው የአንድ ሰው ካርድ ወይም የምስክር ወረቀት መጥፋት ማለት ማንነትን ማጣት ማለት አይደለም። በአገልግሎት ሰጪ እና በተጠቃሚው መካከል ለሚደረጉ ግብይቶች ተአማኒነትን ይጨምራል፤ ይህም ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል። በሁሉም የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖሊሲ ነክ ጉዳዮች ተጠያቂነትን እና ግልፅነትን ያበረታታል።

ንጋት፡- ዲጂታል መታወቂያ ማግኘት የሚችለው ማነው?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ሕጋዊ ነዋሪ በሙሉ ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ብቁ ነው። በ “ረቂቅ አዋጁ” ነዋሪ የሚገለፀው “በሕጋዊ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ወይም የሌለው የተፈጥሮ ሰው እንዲሁም በሀገሪቱ ሕግ መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ወይም የሚሰራ የውጭ ሀገር ዜጋ ነው።” ይህም የሚያካትተው ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በላይ የሆኑ ልጆች መመዝገብ ይችላሉ። ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት በቅርቡ ልዩ የምዝገባ ፕሮግራም የምንጀምር ይሆናል። ኢትዮጵያዊ እና ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ የነዋሪነት ማረጋገጫ ያላቸው፣ የመኖሪያ አድራሻ ማረጋገጫ ሰነድ ያላቸውም ሆነ የሌላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የነዋሪነታቸው መስፈርት “በአዋጁ መሰረት” የተረጋገጠ፣ የት እንደሚኖሩ ምንም ዓይነት ሰነድ የሌላቸው ሰዎች፣ የዲጂታል መታወቂያ ያለው ሰው እንደ ምስክር ይዞ በመቅረብ መመዝገብ ይችላሉ። ማንኛውም ለምዝገባ ብቁ የሆነ ሰው id.et/proof ላይ በተጠቀሰው መሰረት ተቀባይነት ያለው የማንነት ማረጋገጫ ማቅረብ ይኖርበታል።

ንጋት፡- በፋይዳ ምዝገባ ወቅት ምን ዓይነት መረጃ ይሰበሰባል?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- የሥነ-ሕዝብ መረጃ እና የባዮሜትሪክ መረጃ ብቻ የሚሰበስብ ሲሆን ይህም የሚሰበሰበው የግለሰቡን ማንነት በተለየ ሁኔታ ለመለየት ብቻ ነው። ለሥነ ሕዝብ መረጃ ሙሉ ስም፣ የትውልድ ቀን፣ ጾታ፣ ዜግነት እና የአሁን አድራሻ ይሰበሰባል። ለባዮሜትሪክ መረጃ ደግሞ የጣት አሻራ፣ የአይን አሻራ (አይሪስ) እና የፊት ፎቶግራፍ ለፍፁም መለያ እርምጃዎች ይሰበስባሉ። እንደ ስልክ ቁጥር እና የኢሜይል አድራሻ ያሉ ሌሎች መረጃዎች ልዩ የሆነውን FIN (Fayda Identi¬cation Number/ ፋይዳ መለያ ቁጥር) ለተመዝጋቢው ለማድረስ እንደ አማራጭ ያገለግላሉ።

ንጋት፡- የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለማግኛት ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- የሚፈለጉት ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ በአማካይ ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ይፈጃል።

በተሳካ ሁኔታ ከተመዘገቡ በኋላ፣ በሲስተም በኩል የምዝገባ ድግግሞሽን የማጣራት እና የማረጋግጥ ሥራዎች ከጥቂት ደቂቃዎች አንስቶ እስከ ጥቂት ቀናት ሊወስድ ይችላል። ከዚያ በኋላ፣ የእርስዎ FIN (የፋይዳ ልዪ ቁጥር) FAN (የፋይዳ ተለዋጭ ቁጥር) በፅሁፍ መልዕክት በተመዘገቡበት ስልክዎ ይላክልዎታል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ለማኑዋል እና ሌሎች ማረጋገጫዎች ከጥቂት ቀናት በላይ ሊወስድ ይችላል። ልዩ ቁጥርዎን ከ “9779 ወይም ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ማዕከል” አጭር የፅሁፍ መልዕክት በስልክዎ የሚደርስዎ ይሆናል ወይም ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ድረ-ገጽም ማረጋገጥ ይቻላል። አንድ ሰው ዴሞግራፊክ መረጃውን (ሙሉ ስም፣ ስልክ ቁጥር፣ አድራሻ፣ ወዘተ…) እና ባዮሜትሪክ ዳታውን በማንኛውም ጊዜ በኦንላይን ላይ ወይም በአካል በመቅረብ ማስረጃዎችን ማስተካከል ይችላል። ይህ አገልግሎት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሚጀምር ሲሆን በአሁኑ ጊዜ መረጃ ማደስ አይቻልም።

ንጋት፡- ለምዝገባ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ምን ምንድን ናቸው?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- አሁን ላይ የሚኖሩበት ትክክለኛ አድራሻ እና የማንነት ማረጋገጫ ያስፈልጋል። አንድ ግለሰብ ለመመዝገብ ትክክለኛ ሰነድ ማቅረብ ካልቻለ ዲጂታል መታወቂያ ያለው ሰው ምስክር በማቅረብ መመዝገብ ይችላል።

በምዝገባ ወቅት ተመዝጋቢዎች ማንኛውንም ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በማቅረብ መመዝገብ ይችላሉ። ይህም መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የትውልደ ኢትዮጵያዊ ካርድ (Yellow Card)፣ የልደት ምስክር ወረቀት፣ የትምህርት ማስረጃ፣ የሥራ ፈቃድን ይጨምራል። ተመዝጋቢዎች ማንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ ሰነድ ማቅረብ ካልቻሉ ለዲጂታል መታወቂያ የተመዘገበና ልዩ ቁጥር ያለው ግለሰብ በሚሰጠው ምስክርነት መሠረት ሊመዘገብ ይችላል። በመሆኑም በተለያየ ምክንያት ማስረጃ ማቅረብ ያልቻሉ ግለሰቦች ከመታወቂያ አሰጣጥ አገልግሎት እንዳይገለሉ በምስክር አማካይነት የሚደረግ ምዝገባ ያግዛል። በተጨማሪም የቅድመ ምዝገባ አገልግሎት በፕሮግራሙ በበይነ መረብ መመዝገብ ይቻላል።

ንጋት፡- መታወቂያ ቁጥር (FIN) ከጠፋ እንዴት መልሶ ማግኘት ይቻላል?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- የፋይዳ ቁጥር እንዳይጠፋ በጥንቃቄ እንዲያዝ ይመከራል። ድንገት ከጠፋ ወይም በጽሁፍ መልእክት ካልደረስዎት ስማርት ስልክዎን በመጠቀም በቴሌብር ሱፐርአፕ ላይ በሚገኘው የፋይዳ መተግበሪያ ላይ በመግባት ልዩ ቁጥርን ወደ ስልክ መልዕክት ሳጥን መላክ ይችላሉ ወይም ጥያቄውን በድረ ገጻችን id.et/help ላይ በመላክ መከታተል ይቻላል።
ንጋት፡- ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገብ ግዴታ ነው ወይ ?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መብት እንጂ ግዴታ አይደለም። ሆኖም ግን የዲጂታል መታወቂያ አዋጁ እንደሚለው፡- “በሚመለከተው ተቆጣጣሪ/ሬጉሌተር ተቋም ይሁንታ መሰረት ማንኛውም አካል አገልግሎትን ለማቅረብ ዲጂታል መታወቂያን የግዴታ መስፈርት ሊያደርግ ይችላል፡፡

ንጋት፡-የውጭ ሀገር ዜጎች ዲጂታል መታወቂያ ማግኘት ይችላሉ?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- አዎ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በህጋዊ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የየነዋሪነት መታወቂያቸውን ወይም ሌሎች ተዛማጅ ሰነዶችን በመጠቀም ዲጂታል መታወቂያ ማግኘት ይችላሉ።

አካታችነትን ለማረጋገጥ ዲጂታል መታወቂያ የሚሰጠው ለዜጎች ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎችም ጭምር በመሆኑ ስደተኞች፣ ፍልሰተኞች፣ የውጭ አገር ዜጋ ሠራተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ዲጂታል መታወቂያ የማግኘት መብት አላቸው። በተለያየ ምክንያት የጣት አሻራቸው የጠፋ ወይም አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአማራጭ የዓይን አሻራ በመስጠት መመዝገብ ይችላሉ፣ በዚህም አካታችንነትን ማረጋገጥ ይቻላል።

ንጋት፡- የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜ አለው ወይ?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- የዲጂታል መታወቂያ ለግለሰቡ ልዩ የሆነ የሕይወት ዘመን መለያ ቁጥር ነው። ሆኖም ግን የካርድ እና የባዮሜትሪክ መረጃ በተወሰነ ጊዜ መታደስ አለበት። አሁን ላይ የካርድ እና የባዮሜትሪክ መረጃ በየ10 ዓመቱ የሚታደስ ይሆናል።

ንጋት፡- የታተመ የዲጂታል መታወቂያ ካርድ እንዴት ማግኘት ይቻል ይሁን?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- የካርድ ህትመት አገልግሎት ለማግኘት የኢትዮጵያ ፓስታ አገልግሎት (ኢትዮ ፖስት) ዋና መስሪያ ቤት በመሔድ ክፍያዎን በማጠናቀቅ መውሰድ ይችላሉ። ለካርድ ህትመት አገልግሎት ከመሔድዎ በፊት የፋይዳ ልዩ ቁጥሩ በተመዘገቡበት ስልክ የፅሁፍ መልዕክት እንደተላካ ማረጋገጥ ይኖርበታል:: በተጨማሪም ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የተመዘገቡበትን ስልክ ቁጥር ለካርድ ህትመት በሚመጡበት ጊዜ ይዘው መገኘት እና ከተላከው የፅሁፍ መልዕክት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል። የፋይዳ ልዩ ቁጥር ካልደረሰ ድረ-ገጻችን id.gov.et/help ላይ መመልከት ይቻላል።

ንጋት፡- ዲጂታል መታወቂያ የቀበሌ መታወቂያን ያላቸው ግንኙነት ምንድነው?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- አይተካም፤ የከተማ እና የክልል የመንግሥት ነዋሪ መታወቂያ ካርድ የሚሰጡት በአካባቢ አስተዳደር ነው። ነገር ግን “ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጥ ነው። ሁለቱም “ቀበሌ” እና “ፋይዳ” እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲሰሩ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው። ዲጂታል መታወቂያ ማንነትን የሚያረጋግጥ መሠረታዊ መታወቂያና አገልግሎት ለማግኘት የሚጠቅም ሲሆን የቀበሌ መታወቂያ ግን የአንድ የተወሰነ አካባቢ ነዋሪነት መግለጫ ተግባራዊ መታወቂያ ነው። ዲጂታል መታወቂያ የመኖሪያ አካባቢ ገደብ ሳይደረግበት በሀገሪቱ ውስጥ በየትኛውም ቦታ በተፈቀደ አካል ሊሰጥ የሚችል የአንድ ሰው ልዩ መለያ ነው። በአንፃሩ የቀበሌ መታወቂያ ሊሰጥ የሚችለው በሚኖርበት ቀበሌ ብቻ ነው፡፡

ንጋት፡- በመጨረሻ ስለ ዲጅታል መታወቂያ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካልዎት?
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- የዜጎችን የመታወቅ ሰብዓዊ መብት የሚያረጋግጥ፣ ተጠቃሚ አካላትን ከማጭበርበርና ከምዝበራ የሚጠብቅ፣ ጊዜና ሀብት ቆጣቢ፣ እንዲሁም አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ የመታወቂያ ሥርዓት ነው። የመታወቂያ ሥርዓቱ የተመዝጋቢዎችን ሙሉ ፈቃድ መሠረት ያደረገ፣ የግል መረጃዎችን ለመጠበቅ ገደቦችንና ክልከላዎችን ያስቀመጠ ነው።

የተመዝጋቢዎችን ማንኛውም መረጃ የሚይዙ አካላት መረጃውን ለሌላ ማንኛውም አካል ማስተላለፍም ሆነ፣ ተመዝጋቢው ከተመዘገበበትና የማረጋገጥ አገልግሎትን ከጠየቀበት ዓላማ ውጪ ለሌላ ማንኛውም ዓላማ መጠቀም አይችሉም። መዝጋቢ አካላት በአዋጁ ከተቀመጡት መረጃዎች ውጪ ማንኛውንም መረጃ መሰብሰብ አይችሉም። ይህም ተመዝጋቢዎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከትና በጤና ሁኔታ መገለል እንዳይደርስባቸው ይከላከላል። ለዲጂታል መታወቂያ አስፈላጊ ከሆኑት መረጃዎች ውጪ የሰበሰበ አካል፣ እንዲሁም የተመዝጋቢዎችን መረጃ ከሕግ አግባብ ውጪ ለሦስተኛ አካል አሳልፎ የሰጠ አካል በህግ ሊጠየቅ ይችላል፡፡

ዲጅታል መታወቂያ ለማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለታካዊ አገልግሎቶች ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ማንኛውም ዜጋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን መልዕክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

ንጋት፡- ስለሰጡን ማብራሪያ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ መፈክር ጥላሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡