በአለምሸት ግርማ
የማዕከላዊ ባንኮች ዋና ዋና ግቦች በሕግ የተደነገጉና የታወቁ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ግቦች መካከል የዋጋና የፋይናንስ መረጋጋትን ማስፈን፣ የፋይናንስ ተቋማትን መቆጣጠር፣ ቀልጣፋ የክፍያ ሥርዓት መዘርጋት፣ ገንዘብ ማተም፣ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ማስተዳደርና ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረግ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጡ አዋጆች በየጊዜው ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል፡፡
ቀደም ብሎ ብሔራዊ ባንክን ያቋቋመው ቻርተር ቁ. 30/1955 ከወጣ በኋላ በ1955፣ በ1968፣ በ1986 እና በ2000 የወጡ የገንዘብና የባንክ አዋጆች አሉ፡፡ እነዚህ አዋጆች የወጡባቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዐውዶች የተለያዩ ቢሆንም፣ ለብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ሚናና ተቋማዊ ህልውና ዕውቅና የሰጡ፣ የብሔራዊ ባንክን ሥልጣንና ኃላፊነት፣ የባንኩን አስተዳደር፣ ባንኩ ከሌሎች የመንግሥት አካላት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የሚወስኑ ሕጋዊ ማዕቀፎችን በግልጽ ያብራሩና ያስቀመጡ፣ የባንኩን ካፒታል ያሳደጉ ነበሩ፡፡
ይህን መሠረት በማድረግ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ይፋ አድርጓል። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት የገንዘብ ፖሊሲው ዘመናዊ ኢኮኖሚዎች ከተደራጁ በኋላ የገበያ እንቅስቃሴዎችን በመዳኘት በኢኮኖሚ ውስጥ የሚፈጠሩ ሀብቶችን ለማጠራቀም ወይም ለማከማቸት ጥቅም ላይ የሚውል እንዲሁም ከገንዘብ እንቅስቃሴ ጋር የሚያያዙ ሁኔታዎች የሚመሩበት የፖሊሲ ማዕቀፍ ነው። ይህ ፖሊሲ በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የገንዘብ ሥርጭት፣ እንቅስቃሴ፣ አስተዳደር እና ገንዘቡ ሊሰጥ የሚገባውን ጥቅም ያስተዳድራል። የገንዘብ ፖሊሲ እና የበጀት ፖሊሲ አንድ ኢኮኖሚ የሚመራባቸው ሁለት መሠረታዊ ፖሊሲዎች ናቸው።
በተጨማሪም የገንዘብ ፖሊሲ ገንዘብ በሰዎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ወይም የሚገባውን ውጤት እና በኢኮኖሚው ውስጥ ልንፈጥራቸው የምንፈልጋቸውን እውነታዎች ለማምጣት የምጠቀምበት የፖሊሲ ማዕቀፍ ነው። የበጀት ፖሊሲ የመንግሥት የገቢ እና የወጪ ሁኔታን የሚያስተዳድር የፖሊሲ ማዕቀፍ ነው። የመንግሥት የወጪ እና የገቢ ሁኔታ ገንዘብ ከሚተዳደርበት የገንዘብ ፖሊሲ ጋር በጣም ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ለዚህም ይመስላል ላለፉት 16 ዓመታት ያለገደብ ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ሲበደር የነበረው የፌደራል መንግሥት፤ ከአገር ውስጥ ገቢ ከ15 በመቶ የበለጠ ገንዘብ በብድር ማግኘት እንዳይችል የሚገድብ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው።
ለምክር ቤቱ የቀረበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ፤ መንግሥት የተበደረውን ገንዘብ በአንድ ዓመት ውስጥ ካልመለሰ ከተቋሙ ሌላ ብድር መውሰድ እንደማይችልም ያስቀመጠ ነው። አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ያለገደብ ብድር እንዲወስድ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደውን በ2000 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ የሚቀይር ነው። የሀገሪቱን ማዕከላዊ ባንክ ለመምራት ከ1955 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ አዋጆች የጸደቁ ሲሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ካለው አዋጅ በስተቀር ቀሪዎቹ አዋጆች ለመንግሥት በሚሰጥ የቀጥታ ብድር ላይ ገደብ ያስቀመጡ እና ገንዘቡ የሚመለስበት ጊዜ የተወሰነበት ነበር። በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በአንጻሩ፤ “ባንኩ ለመንግሥት እና ለፋይናንስ ተቋማት ብቻ ብድር እንደሚሰጥ ከመግለጽ ውጭ ለመንግሥት በሚሰጠው ቀጥታ ብድር ላይ ግን ምንም ገደብ ሳይጥል ያለፈ የመጀመሪያው አዋጅ” እንደሆነ ከአዲሱ ረቂቅ ጋር የቀረበው ማብራሪያ ያስረዳል።
በዚህ አዋጅ ላይ በብሔራዊ ባንክ እና በፌዴራል መንግሥት መካከል የሚኖረው የብድር ሥርዓት በአግባቡ አለመደንገጉ “የነባሩ አዋጅ አንዱ መሠረታዊ ችግር” እንደሆነ በማብራሪያው ላይ ተጠቅሷል። የፌደራል መንግሥት የሚያጋጥመውን የበጀት ጉድለት ለመሸፈን ያለገደብ ብድር እንዲወስድ መደረጉ በገበያ ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን በመጨመር በአገሪቱ ውስጥ በተከታታይ ዓመታት ለተፈጠረው የዋጋ ግሽበት መንስኤ እንደሆነ የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ባለሙያዎች ሲገልጹ ቆይተዋል። ይህንን ሀሳብ የሚጋሩት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ተንታኙ ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ፤ “መንግሥት የበጀት ጉድለት በገጠመው ቁጥር ያለገደብ ብድር ሲወስድ” የነበረ መሆኑ ይህ አሠራር “ከቁጥጥር የወጣ የዋጋ ግሽበት” ማስከተሉን ይናገራሉ።
ዶ/ር አብዱልመናን፤ ባለፉት 16 ዓመታት ከተከሰተው “ማቆሚያ የሌለው የዋጋ ግሽበት ዋና ምክንያት” መንግሥት ያለገደብ ከብሔራዊ ባንክ ብድር እንዲወስድ መደረጉ እና ገንዘቡ ወደ ኢኮኖሚው መግባቱ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ባለፉት ዓመታት በየዓመቱ በመቶ ቢሊዮን ብሮችን ከብሔራዊ ባንክ ሲበደር የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት “ዘግይቶም ቢሆን” ነገሩን ተረድቶ በአዲሱ ረቂቅ ላይ ይህንን ገደብ ማቀመጡን እንደሚደግፉት ገልጸዋል። በረቂቅ አዋጁ ብሔራዊ ባንክ እንዲኖረዉ ከተደረጉ አዳዲስ ሥልጣንና ተግባራት መካከል አንቀጽ 6(1) ላይ የሰፈረውና ብሔራዊ ባንክ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመመካከር የዋጋ መረጋጋትን ግብ ያስቀምጣል የሚለው ነው፡፡
ዋጋን የማረጋጋት ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስላሉ ባንኩ ከእነዚህ መሥሪያ ቤቶች ጋር በመመካከር የዋጋ መረጋጋት ግብ (Price Sta bility Target) ያስቀምጣል/ይወስናል። ሆኖም፣ የዋጋ መረጋጋትን ግብ ከተወሰነ በኋላ ባንኩ የዋጋ ማረጋጋት ግቡን ለማሳካት የመረጠዉን የገንዘብ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሣሪያ የመጠቀም ሥልጣን እንዳለው በረቂቁ ተደንግጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲን ለማስፈጸም እና በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን ለመቆጣጠር ይረዳው ዘንድ የራሱን የአጭር ጊዜ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ በማውጣት በፋይናንስ ተቋማት እና በባንኩ መካከል ግብይት (Open Market Operation) ለመፈጸም የሚያስችለው አዲስ ድንጋጌ በአንቀጽ 6(4) ላይ ተካቷል፡፡ አዲሱ ረቂቅ፤ ከቀድሞው አዋጅ በተለየ ሁኔታ ብሔራዊ ባንክ “በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለፌዴራል፣ ለክልል፣ ለማንኛዉም የታችኛው የመንግሥት የአስተዳደር እርከን፣ የከተማ አስተዳደር ወይም የመንግሥት ተቋም ብድር” መስጠት እንደማይችል ያስቀምጣል።
የፌደራል መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ብድር ማግኘት የሚችለው ከ12 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የሚመለስ “የኦቨር ድራፍት አገልግሎት” እንደሆነ በረቂቁ ላይ ሰፍሯል። ይህ አይነቱ የብድር አሰጣጥ መንግሥት በተገደበ ጊዜ ውስጥ የተገደበ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲያገኝ የሚያስችለው መሆኑን የሚያስረዱት ዶ/ር አብዱልመናን፤ በብዙ አገራት የተለመደ አሠራር መሆኑን ገልጸዋል። አዲሱ ረቂቅ በአንጻሩ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ በኦቨር ድራፍት አገልግሎት ማግኘት የሚችለው ገንዘብ “ካለፉት ሦስት የበጀት ዓመታት አማካይ ዓመታዊ ጠቅላላ የመንግሥት የአገር ውስጥ ገቢ ከ15 በመቶ መብለጥ” እንደሌለበት አስፍሯል። መንግሥት ከባንኩ የሚወስደው ገንዘብ “በገንዘብ ፖሊሲ ተመን ላይ ተመሥርቶ የሚሰላ የወለድ ተመን” እንደሚጣልበት ያሰፈረው አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ፤ ገንዘቡ በ12 ወራት ውስጥ መመለስ እንዳለበትም ይደነግጋል።
ለመንግሥት የተሰጠ ጊዜያዊ ኦቨር ድራፍት የመክፈያ ጊዜው ሲደርስ ሊከፈል ይገባል እንጂ አይተላለፍም ሲልም በገንዘቡ አመላለስ ላይ አጽንኦት ይሰጣል። ከዚህም ባሻገር የፌደራል መንግሥት በቀጣዩ ዓመት ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት የሚችለው በዚህ አገልግሎት የወሰደውን ገንዘብ በተቀመጠለት የመክፈያ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የተከፈለ እንደሆነ ብቻ መሆኑን ይገልጻል። የፋይናንስ ተንታኙ ዶ/ር አብዱልመናን፤ መንግሥት ገንዘቡን ሳይከፍል ተጨማሪ እንዳይወስድ መደረጉን ቢደግፉትም “ከዚህም ጠበቅ ያለ አንቀጽ” ረቂቁ ውስጥ ቢካተት የሚል አስተያየትም አላቸው።
ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ልቅ የነበረው የመንግሥት ብድር ላይ ገደብ ቢያስቀምጥም “ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ” መንግሥት ከገደቡ በላይ የሆነ ገንዘብ ከብሔራዊ ባንክ ሊጠይቅ እንደሚችል ያስቀመጠ ሲሆን፤ ረቂቁ፤ “ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ’” በማለት ከሚያስቀምጣቸው ጉዳዮች ውስጥ “ያልተጠበቀ የማኅበረሰብ ጤና፣ የተፈጥሮ አደጋ እና ድርቅ” ይገኙበታል። “አግባብነት ያለውን ሕግ መሠረት አድርጎ የታወጀ አጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወይም በፌዴራል መንግሥት ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ጉልህ የውጭ የኢኮኖሚ ለውጦችም” ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እነዚህን ሁኔታዎች መሠረት በማድረግ ተጨማሪ ብድር የሚሰጠው፤ “የዋጋ መረጋጋትን የማረጋገጥ ዓላማ ሳይጣረስ፣ የፌዴራል መንግሥትን የመንግሥት ብድር ጣሪያ ባከበረ መልኩ” እንደሆነ ሰፍሯል። የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ፤ ይህ ዓይነቱ አማራጭ አሠራር “ከዓለም አቀፍ የተሻለ ተሞክሮ አኳያ የማይመከር” እንደሆነ አልሸገገም። ይሁንና ይህ የልዩ ሁኔታ አሠራር በረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲካተት የተደረገው የአገሪቱን “ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት” እንደሆነ ይጠቅሳል።
ይህ ዓይነት ድንጋጌ መኖሩን በበጎ የሚመለከቱት ዶ/ር አብዱልመናን ለአፈፃፀሙ ወጥነት ግን ተጨማሪ ህጎች መካተት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል። የማዕከላዊ ባንክ ሕግ ግልጽና በተቻለ መጠን ምሉእ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ የሚወጣው ሕግ የባንኩን ተልዕኮና ኃላፊነት ማለትም የባንኩን የፖሊሲ ዓላማ፣ ባንኩ ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚያከናውናቸውን ተግባራትና እነዚህንም ተግባራት ለመፈጸምና ለማስፈጸም ያለውን ሥልጣን በሚገባና ግልጽ በሆነ መንገድ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም፣ የዚህ ረቂቅ ሕግ ዓላማና ግብ የባንኩን ሥልጣንና ተግባር፣ የባንኩን አስተዳደር፣ ተአማኒነት፣ ተጠያቂነትና የአሠራር ሥርዓት ግልጽ ለማድረግና ሕጋዊ መልክ ለማስያዝ ነው፡፡
የአዋጁ የመጨረሻ ክፍል በአብዛኛው የያዘው ልዩ ልዩ አዳዲስ ድንጋጌዎችን ነው፡፡ በዚህ ክፍል የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ጥበቃ፣ ግብር፣ ንብረት ግዥ እና አወጋገድ፣ የማዕከላዊ ባንክ ዲጂታል ገንዘብ እና አስተዳደራዊ እርምጃ በተመለከተ አዳዲስ ድንጋጌዎች ተካተዋል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው