“የአካል ጉዳተኛነቴ ከማንም በታች አላደረገኝም” – አቶ ፍንድጋ ፍላቴ

በአብርሃም ማጋ

አቶ ፍንድጋ በአካል ጉዳተኛነቱ የተነሳ ከማንም በታች አለመሆኑን ከመግለፁ አስቀድሞ ክስተቱ ከባድ ፈተና ነው ይላል። “የአካል ጉዳት ሰዎች ወደውት ሳይሆን በተፈጥሮ፣ በአደጋና በአጋጣሚ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ክስተቱ በቅድሚያ አእምሮን ይጐዳል፡፡ በተለይ ግንዛቤ በሌለበት አካባቢ አንድ ሰው አካል ጉዳት ሲገጥመው በእርግማን ተረግዞ እንደተወለደ ይቆጠራል፡፡ ሁሌ ከሰው በታች እንደሆነ አእምሮውን አሳምኖ የችግርና የመከራ ህይወት ይገፋል፤ ልመናንና ተረጅነትን የግሉ ስጦታዎች አድርጐ ተቀብሎ ኑሮውን ይገፋል” በማለት ይዘረዝራል፡፡

ነገር ግን የአካል ጉዳተኝነት ምንጭ ከእርግማን ጋር ተያያዥነት እንደሌለው ገልፆ የአእምሮ ጉዳት የሌለው ሁሉ በክስተቱ ሳይበገር ሰርቶ ራሱን ለመለወጥ ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅበታል ይላል፡፡ ለዚህም ይመስላል የ37 ዓመቱ ወጣት ፍንድጋ በልጅነቱ በተከሰተበት የአካል ጉዳተኝነት ሳይበገር ራሱን ከምሁራን ተርታ ያሰለፈው፡፡ ወጣት ፍንድጋ ፍላቴ በሐዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ በፊንጫዋ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሎቄ ቤተመንግስት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ1979 ዓ.ም ነው የተወለደው፡፡ ገና የ4 ዓመት ልጅ እያለ ወላጆቹ ለከብቶቻቸው ሳር ፍለጋ ተጐዳኝተው በሐዋሣ ዙሪያ ወረዳ ወደምትጠራው ቀበሌ ይሄዳሉ፡፡

ከእለታት አንድ ቀን ከታላቅ ወንድሙ ጋር ጥጆችን ውሃ ለማጠጣት ወደ ሐዋሣ ሐይቅ ጉዞ ጀመሩ፡፡ ሐይቁ ከመኖሪያ ቤታቸው ወደ አንድ ሰዓት ገደማ የሚያስኬድ ሲሆን ተጉዘው ደረሱ፡፡ እንደደረሱ ገና ፍንድጋ ሐይቁን ሲያይ የ6 ሰዓት ፀሐይ በሐይቁ ላይ የፈጠረው ነፀብራቅ በዓይኑ ላይ ሲያርፍ ራሱን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ በዚሁም ከቁጥጥሩ ውጭ የሆነ ሐይል ገፋፍቶት ሩጫውን ወደ ሐይቁ ያደርጋል። ነፀብራቁን ተከትሎ ወደ ሃይቁ ይገባል። ወንድምየውና ሌሎችም እረኞች ተከትለውት ከሐይቁ ውስጥ አወጡትና ተሸክመውት ወደ ቤት አደረሱት፡፡ በሁለተኛ ቀን ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ የቀኝ እግሩ የእሱ አልነበረም፡፡ በድን ሆኖ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አልነበረውም።

በአካባቢው ሰዎች ልክፍት ነው የሚል ውሳኔ ተሰጥቶት ሐኪም ቤትም ሳይወሰድ ሶስት ወር ሙሉ ተኝቶ ቆይቶ በጉልበቱ መዳህ ይጀምራል፡፡ በዚሁ እያለ አንድ ቀን አባትየው ወደ ትውልድ ቀዬአቸው መጥተው ኖሮ አንዲት አካል ጉዳተኛ ልጅ በክራንች ስትንቀሳቀስ ያያሉ፡፡ የማን ልጅ እንደሆነች ጠይቀዋት ከተረዱ በኋላ አባቷን ክራንቹን ከየት እንዳገኙ ጠይቀው መረጃ አገኙ፡፡ መረጃውም ያመላከተው በቱሎ ቅዱስ ጳውስ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል መሆኑን ሲሆን በጠዋት ተነስተው ልጃቸውን በትከሻቸው ላይ ተሸክመውት ያደርሳሉ፡፡

ቤተክርስቲያንዋም ክራንቹን ያገኘችው በኦሮሚያ ውስጥ ኩየራን አልፎ ጅጌሣ በሚባል ስፍራ ከምትገኘውና የራሷ ቅርንጫፍ ቤተክርስቲያን እንደሆነ ነገሯቸው፡፡ ቢሆንም የቱሎ ቤተክርስቲያኑዋ ተባብራ በራሳቸው መኪና አደረሱት፡፡ ልጁ ለተወሰኑ ወራት ጅጌሣ ከቆየ በኋላ ክራንቹ መጣለት፡፡ በቆይታው ጊዜ ያለውን አጠቃላይ ወጪውን የቻለችለት ቱሎ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ነበረች፡፡ አቶ ፍላቴም ትልቅ ተስፋ ሰንቀው ልጃቸው ትምህርቱን ተምሮ ማንም የደረሰበት ደረጃ እንደሚደርስ እየነገሩት ከማበረታታት አልቦዘኑም ነበር፡፡ በዚሁም በእሳቸው ዘንድ የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው ገልፀው ቤተክርስቲያኑዋን ልጃቸውን እየረዳች እንድታስተምረው ይማፀናሉ፡፡ ከቤተክርስቲያኑዋ ዓላማዎች አንዱ የተቸገሩተንና የአካል ጉዳተኞችን መርዳት በመሆኑ ምንም ሳታንገራግር በእሺታ ተቀበለችው፡፡ ተቀብላውም በራስዋ ስር ባለው ቱሎ ቅዱስ ጳውሎስ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት አስገባችው። ደብተር፣ ስክሪብቶና ልብስ በእነሱ ይሸፈን ነበር፡፡ በወቅቱ ማደሪያ ቤት ስላልነበራቸው በአባቱ ቤት እያደረ መማር ጀመረ፡፡

የአባቱ ቤት ብዙም ስለማይርቅ ጠዋት በጊዜ ወጥቶ እየተመላለሰ መማሩን ቀጠለ፡፡ ፍንድጋ ልበ ሙሉና ጠንካራ ልጅ በመሆኑ ወገቡን ጠበቅ አድርጐ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በትምህርት ቤቱ አጠናቀቀ፡፡ በመቀጠልም ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍልም ሐዋሣ ታቦር አጠቃላይ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ ቤት ገብቶ ተምሯል፡፡ ሐዋሣ ሲማርም የእነሱ እርዳታ አልተለየውም ነበር፡፡ ሆኖም ተጨማሪ እርዳታ እንዲያገኝ አስበው ለደቡብ ዕዝ እርዳታ ሰጪ ድርጅት የትብብር ደብዳቤ ጽፈውለት የቅንጬና የዘይት እርዳታን በተጨማሪነት ያገኝ እንደነበረም ተናግሯል፡፡

የቱሎ ሚሲዮኖች ለትምህርቱ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች የቤት ኪራይ፣ ልብስ፣ ደብተር፣ ስክሪብቶ እና የመሳሰሉትን ወጪዎችን ከመሸፈን አልፎም ክራንቹ ሲያረጅበት በየወቅቱ ጅጌሣ በራሳቸው መኪና ወስደው እንደሚያስቀይሩለት ከምስጋና ጭምር ተናግሯል፡፡ ተማሪ ፍንድጋ 1ዐኛ ክፍል ሲያጠናቅቅ ብሔራዊ ፈተና ተፈትኖ የዲፕሎማ ትምህርት ለመማር የሚያስችል ውጤት አምጥቷል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የአካል ጉዳተኛነቱን ያላገናዘበ ምደባ ነበር፡፡ ምደባውም ሐዋሣ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ (TTC) ሲሆን ከተመረቀ በኋላ ክራንች ይዞ ቆሞ ማስተማር ከባድና የማይችለው ነገር መሆኑን ተገንዝቦ ሳይገባ ይቀራል፡፡ ይሁን እንጂ ኮሌጅ ያልገባው እቤት ቁጭ ለማለት ሳይሆን ሌላ አማራጭ ፈልጐ ነበር፡፡

አማራጩም ዛየን ቴክኖሎጂና ቢዝነስ ኮሌጅ መማር ሲሆን በውሳኔው መሠረት የመግባት እድል አግኝቶ በአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ሰለጠነ። ኮሌጁ በክፍያ የሚያስተምር ቢሆንም እሱ ግን የነፃ ትምህርት እድል ተሰጥቶት ነበር የተማረው፡፡ የነፃ ትምህርት እድል ያገኘው የሐዋሣ ከተማ አስተዳደር የአካል ጉዳተኞች ማህበር ለኮሌጁ በፃፈለት ድጋፍ ትብብር ደብዳቤ ሲሆን ተምሮም በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ ከዚያም በዲፕሎማው ቱላ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ በሠራተኝነት ተቀጠረ፡፡ ለተወሰኑ ዓመታት እንደሠራም ባለው የትምህርት ደረጃ ከፍ የማድረግ ፍላጐት ነፃ የትምህርት እድል ማፈላለግ ጀመረ፡፡

ቀደም ሲል ቱላ ከተማ እንደተመደበ የተቋቋመውና የመሠረተው የአካል ጉዳተኞች ማህበር ለሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የትምህርት እድል እንዲሰጠው የትብብር ደብዳቤ ጽፎለት የመማር እድል አገኘ፡፡ በዚሁም በአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት በ2010 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ አሁን በት/ቤቱ የትምህርት ደረጃውን የሚመጥን ደመወዝ እየተከፈለው በስራ ላይ ይገኛል፡፡ ከመደበኛ ሥራው ውጭ የቱላ ከተማ አካል ጉዳተኞች ማህበር መሥራችና ሠብሳቢ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ተግባራት በጉዳዩ ዙሪያ እየሠራ ይገኛል፡፡ ተግባራቱም በክፍለ ከተማው ባሉት 12 ቀበሌያት ውስጥ ቤት ለቤት እየዞሩ ሁሉም የአካል ጉዳተኞች የትምህርት፣ የጤና፣ የፍትህ አገልግሎቶችን እንደማንኛውም ጉዳት አልባ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግን ያጠቃልላል፡፡

በትምህርት ዙሪያ ህፃናት እንዲማሩ ከማድረግ አኳያ ለወላጆች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት በክፍለ ከተማው ብቻ 196 ህፃናት የትምህርት እድል አግኝተዋል፡፡ ከነዚህም 50ዎቹ ከዲፕሎማ በላይ ሲሆኑ 12 የሚሆኑት በመንግስት ሥራ ተቀጥረው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ 12ኛ ከፍል ያጠናቀቁት በርካቶቹ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በኮምፒውተር ሥራ እንዲሁም በፀጉር ሥራ በማህበር ተደራጅተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

በትምህርት ወቅት የቦታ ርቀት በመኖሩ የትራንስፖርት ችግር፣ ትራንስፖርት እንኳን ቢገኝም አንዳንድ ጊዜ ለአካል ጉዳተኞች የቦታ ጥበትና አለመመቻቸት፣ ማግለል፣ ካፍቴሪያዎችና ሆቴሎች አካል ጉዳተኞችን የሚያስተናግዱበት ሁኔታዎች አለመኖር፣ የመፀዳጃ ቦታዎች አለመመቻቸት፣ ትምህርት ሲማር በፎቅ የገነቡ ክፍሎች ሊፍት ስላልነበራቸው ከፍተኛ ችግር ፈጥሮበታል። በተለይም የዲኘሎማና የዲግሪ ትምህርቱን ሲማር በከፍተኛ ሁኔታ ይቸገር ነበር፡፡ ወጣት ፍንድጋ ወደ ትዳር ዓለም የገባው በ2005 ዓ.ም ሲሆን ባለቤቱ ጉዳት አልባና የዲግሪ ተማራቂ ነች፡፡

መጀመሪያ ላይ ጉዳት አልባዋ ሴት ከእኔ ጋር ትዳር አትይዝም የሚል ፍራቻ ቢያድርበትም ሲጠይቃት ምንም ሳታንገራግር ፍቃደኛ መሆኗ እንዳስደሰተው ይናገራል፡፡ ይህንን ሰምተው ጓደኞቹዋ ምን ሆነሽ ነው አካል ጉዳተኛ የምታገቢው ቢሏትም ውሳኔዋን አልቀየረችውም፡፡ እንዲያውም የአእምሮ ጉዳት እስከሌለው ድረስ እንደማንኛውም ሰው ተንከባክቦ ያኖረኛል የሚል በሙሉ እምነት ምላሽ ትሰጣቸው ነበር፡፡ በዚሁም በቤተክርስቲያን ሥርዓት በደመቀ ሁኔት ተጋብተው 2 ወንድና አንድ ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ባለቤቱም በቱላ ክፍለ ከተማ በመንግስት ሥራ ተቀጥራ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በ2009 ዓ.ም ላይ በቱላ ከተማ ውስጥ በገዛው የመኖሪያ ቤት ከቤተሰቡ ጋር እየኖረ ይገኛል፡፡

ባስተላለፈው መልእክትና “በክፍለ ከተማዋ አንዳንድ የአካል ጉዳተኞች ወላጆች እገሌ አካል ጉዳተኛ ልጅ ወልዷል የሚባል ሃሜት በመፍራት ልጆቻቸውን እቤት በመደበቃቸው ምክንያት የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎችንም ማህበራዊ አገልግሎቶችን የማያገኙ ህፃናት በመኖራቸው ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ድርሻውን መወጣት አለበት” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡