ከህብረተሰቡ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት የመሶብ አንድ ማዕከል ተመራጭ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከህብረተሰቡ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመራጭ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ከሶስት መቶ ሀምሳ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የሚዛን አማን መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው የመሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ተገንብቶ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልም በሚዛን አማን ከተማ የተገነባው መሶብ የአንድ ማእከልም አገልግሎት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።

በዚሁ በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርእሰ መስተዳደር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የዛሬው የማእከሉ መመረቅ ለተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከማስቻሉም ባለፈ ከህብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚቀረፉበት ማእከል ነው ብለዋል።

በማእከሉ ሰላሳ ሁለት የተለያዩ አገልግሎቶች ይሰጣሉ ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ ፤ ማእከሉን በመደገፍ በኩል የሚመለከታቸው አካላት የበኩላችውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ማእከሉ በቀጣይ በአምስት የከተማ አስተዳደሮች እንደሚጀመርም ጠቁመዋል።

ማእከሉ ሶስት መቶ ሀምሳ ሚሊየን ያህል ብር መፍጀቱንም ነው ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) የተናገሩት።

የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው፤ ይህ በክልሉ የመጀመሪያ የሆነው የሚዛን አማን መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ለዜጎች ስልጡን በሆነ መንገድ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል በቀጣይም በዞን ከተሞች ይህ ማእከል ግንባታ ተጠናክሮ ይሰራል ብለዋል።

ግንባታው በአርባ አምስት ቀን ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱንም ጠቁመዋል።

የኢፌዲሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር ወይዘሮ አልማዝ መሰለ፤ በመንግስት አገልግሎት ይታይ የነበረው ችግር ወደ ሰው ተኮር አገልግሎት ለማሳደግ ዘርፉን ለማነቃቃት መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አቅጣጫ ተቀምጦ ወደተግባር ተገብቷል ብለዋል።

የክልሉ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አስራት አዳሮ በበኩላቸው፤ የሚዛን አማን መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት በዘጠኝ ተቋማት እና በሀያ ስምንት አገልግሎቶች ስራ መጀመራቸውን ጠቅሰው ወደፊት አገልግሎቶቹን የማስፋት ስራ ይሰራልም ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቴን፤ የመሶብ ማዕከሉ መከፈት በሀገር፣ በክልሉ እንዲሁም በአካባቢያቸው ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚቀርፍ ነው ብለዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ህይወት አሰግድ በበኩላቸው የአንድ መሶብ ማእከል መመረቁ በገቢ አሰባሰብ ላይ ይታይ የነበረውን ቀልጣፋ አሰራር ችግር ይቀርፋል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን