ሀዋሳ፡ ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሌማት ትሩፋት በመሰማራት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የምዕራብ አባያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት በበኩሉ በሌማት ትሩፍት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በወረዳው የቆላ ሙልዓቶ ቀበሌ አርሶ አደር ገላነህ ቦርኮ በሰጡት አስተያየት ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤ በዶሮ እርባታ ሥራ ላይ በመሠማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀው፥ የእንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማርባት ከቤት ፍጆታ ባለፈ እንቁላል ለገበያ በማቅረብ በየወሩ ከ7 እስከ 8 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር ዘካሪያስ ኤልካ በማር መንደር በመደራጀት ዘመናዊ ቀፎዎችን በመግዛት በተፋሰስ በለማው ቦታ ንብ በማነብ ከእርሻ ስራቸው ጎን ለጎን በዓመት 400 ኪሎ ግራም ማር ለገበያ በማቅረብ ከፍጆታ ባለፈ ከ270 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር ገቢ እንሚያገኙ ገልፀዋል።
በሌማት ትሩፋት ስራዎች በመሳተፍ ሌሎችም አርሶ አደሮች እንደ እነሱ ተጠቃሚ እንዲሆኑም መክረዋል።
የምዕራብ አባያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የእንስሳትና ዓሳ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማሞ ዳንጋርሶ እንዳሉት በወረዳው የማር ፣ የዶሮ ፣ የወተት ፣ የሥጋ ፣የዶሮ እና የዓሳ መንደሮች መደራጀታቸውንና በዚህም 523 የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በሌማት ትሩፋት ከተደራጁት 12 መንደሮች በማር ምርት እና በዶሮ እርባታ 3 መንደሮች ያሉ ሲሆን ለአርሶ አደሮቹ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት ክፍተቶችን እየሞሉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ: ፀሐይ ጎበና – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
በኮሬ ዞን የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መልሶ የማደራጀት ምክክር መድረክ ተካሄደ
በአጋር ድርጅቶች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የመንግስት የልማት ክፍተት በመሙላት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
ከህብረተሰቡ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት የመሶብ አንድ ማዕከል ተመራጭ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)