የችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች ባለቤት

የችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች ባለቤት

በአስፋው አማረ

በዓለማችን ላይ ስመጥር ከሚባሉ ተመራማሪዎች መካከል ለችግሮች መፍትሔን በማፍለቅ አንቱታን ያተረፉ በርካታ ሴት ተመራማሪዎች ይገኛሉ፡፡ በሀገራችንም በርካታ ሴት ተመራማሪዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዛሬው እቱ መለኛ አምዳችን ይዘን የቀረብንላችሁ መምህርት ፅጌሬዳ ደርጋሶን ነው፡፡

የተወለደችው መተሃራ ከተማ ሲሆን እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ በመርቲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡ በመቀጠል ከ9ኛ እስከ 12 ኛ ክፍል ደግሞ መርቲ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡ የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን ማጠናቀቋን ተከትሎ ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ መግባት ችላለች፡፡ የትምህርት ክፍል ድልድል ላይ መምህርት ጽጌሬዳ ባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ደረሳት፡፡

ከልጅነቷ ጀምሮ የምትወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች ደግሞ ሒሳብና ፊዚክስ ነበሩ፡፡ ይህን ተከትሎ በጣም አዘነች፡፡ ወደ ፊዚክስ የትምህርት ክፍል የመቀየር ፍላጎት ነበራት፡፡ በመጨረሻም ፍላጎቷ ከንቱ ሆኖ አልቀረም “ከባዮሎጂ ወደ ፊዝክስ የትምህርት ክፍል ቅያሪ አደረኩኝ” ስትል ትናገራለች፡፡ በወቅቱ ከባዮሎጂ ወደ ፊዚክስ ትምህርት ክፍል ስትቀይር በርካታ ተማሪዎች ተገርመው ነበር፡፡ ጥያቄም ፋጥሮባቸዋል? ለምን ቀየርሽ? ይከብድሻል? የሚሉ ሀሳቦችን ይሰነዝሩላት እንደነበር አስታውሳናለች፡፡ “እኔ ግን የጓደኞቼን ፍራቻ ሳይሆን ፍላጎቴን ማስቀደም ስለነበረብኝ ነው የቀየርኩት” ብላለች፡፡ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሒሳብ፣ ፊዝክስና ጂኦ ፊዚክስ የትምህርት ክፍል በብዙ ተማሪዎች የሚፈሩ መሆናቸውን ትናገራለች፡፡

“እኔም ከልጅነቴ ጀምሮ ቁጥር ነክ የሆኑ ትምህርቶች ላይ ከሌሎቹ የተሻልኩ ስለነበርኩኝ ወድጄውና በፍላጎት የመረጥኩት የትምህርት ክፍል ነው” ስትል የልጅነት ፍላጎቷን ማሳካት መቻሏን አውግታናለች፡፡ የስራ ዓለምን የተቀላቀለችበትን አጋጣሚ ስትናገር፦ “ወደ ሥራ ዓለም ከመግባቴ በፊት ከቤተሰብ ተለይቼ ዩኒቨርሲቲ ሳለሁኝ መጀመሪያ ላይ ከትምህርቱ ይልቅ አካባቢውን መልመዱ ትንሽ ይከብድ ነበር፡፡ በትምህርት ክፍሉ ያለምንም ችግር ለሶስት ዓመታት ትምህርቴን በመከታተል ተመርቄያለሁ፡፡

“ከተመረቅን በኋላ የእኛ ዙር ተመራቂዎች ፔዳጎጂ ኮርሶችን(ስለተማሪ ባህሪ እና ውጤት አሞላል) አልወሰድንም ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የትምህርት ስልጠናዎችን ለመውሰድ በእጣ ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተደለደልን፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆነና ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ደረሰኝ፡፡ “ስልጠናውን ከጨረስን በኋላ አጋጣሚ ሐዋሳ ከተማ ትምህርት መምሪያ መምህራን ለመቅጠር የሥራ ማስታወቂያ አወጣ፡፡ የትምህርት ማስረጃዎቼን አስገብቼ ነበር፡፡ የምድባ ቦታ ዕጣ እንዳነሳ በማስታወቂያ ተጠራሁ፡፡ ዕጣ ሳነሳ ቱላ ክፍለ ከተማ ጨፌ ኮቲጀ ቤሳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተመድቤ በ2011 ዓ.ም የስራ ዓለምን አሀዱ ብዬ ጀመርኩ” ስትል ወደ ስራ የገባችበትን አጋጣሚ አጫውታናለች፡፡

ወደ ፈጠራ ሥራ የገባችበትን አጋጣሚ ደግሞ በሐዋሳ ከተማ ትምህርት መምሪያ በየዓመቱ የሚካሄድ በሐዋሳ ከተማ ትምህርት ቤቶች ሥር የሚገኙ መምህራንና ተማሪዎች የሚሳተፉበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ውድደር ይካሄድ ነበር፡፡ ውድድሩም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ መምህርት ጽጌሬዳና ጓደኞቿ የመሰላቸው የተማሪዎች ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽንና ውድድር መምህራንንም የሚያሳትፍ መሆኑን መገንዘብ ችለዋል፡፡ ይህን ተከትሎ በሁለተኛው እና በሶስተኛ ዙር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ውድድር ላይ የመሳተፍ ፍላጎቱ ያድርባቸዋል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽና ውድድር ከዚህ ቀደም በውስጧ ታሰላስለው የነበረ የተለያዩ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት ምክንያት ሆናት፡፡

በልጅነቷ የተለያዩ የዕደ ጥበብ ሥራዎችን ትሞካክር እንደነበር አስታውሳን። እንደዚሁም በዩኒቨርስቲ በነበረችበት ወቅት በመኝታ ክፍሏ ውስጥ ያሉ ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ ሴት ተማሪዎች ሌሎች አካባቢ የሚሰሩ የዕደ ጥበብ ሙያዎችን መቅሰም መቻሏን ትናገራለች፡፡ ይህ ደግሞ እሷ ከምታውቀው በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች የሚሰሩ የዕደ ጥበብ ሥራዎችን እንድታውቅ እድሉን ፈጥሮላታል። “ከትግራይ፣ ከጎጃምና ከወሎ የመጡ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እኔ የማውቀውን ለእነሱ እያጋራሁ ከእነሱ ደግሞ እኔ ማላውቀውን የእደ ጥበብ አሰራር እቀስም ነበር፡፡ የቀሰምኳቸው ሙያዎች በቀላል ወጪ ቤትን ማስዋብ የሚያስችሉ ናቸው” ስትል ትናገራለች፡፡ የመጀመሪያ ዙር ኤግዚቢሽን ከተከናወነ በኋላ እነሱም በስፋት የመሳተፍ ፍላጎት አደረባቸው፡፡

“በመጀመሪያ ተማሪዎች የተለያዩ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና ሀሳቦችን ማገዝ ሥራ በስፋት ሰርተናል” ስትል ቅድሚያ ተማሪዎች ላይ ትኩረት ስለማድረጓ ትናገራለች፡፡ በተለይም ተማሪዎችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማገዝና ማብቃት ተቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው እንደሚሰሩ ትገልፃለች፡፡ በዚህም ደግሞ አጥጋቢ ውጤት ማየት እንደቻሉና ተማሪዎችም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች መስራት መቻላቸውን ትናገራለች፡፡ “በሐዋሳ ከተማ ለሶስተኛ ጊዜ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ውድድር ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ከተሰሩት ሥራዎች መካከል በአካባቢያችን ከምናገኛቸው የጉሎ፣ የአቩካዶ እና የሰሊጥ ዘይት በማምረት ማቅረብ ችለን ነበር” ብላናለች፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቀላሉ የቤትና የንግድ ቦታዎችን ማስዋብ የሚችሉ ሥራዎችን ይዘው ቀርበው ነበር፡፡ ለአብነት የተማሪ ቦርሳዎችን ለመስራት የተጠቀሙት በቀላሉ ከሚገኝ ጥሾ (ከቆጮ ሲፋቅ የሚወጣው ተረፈ ምርት) እና ትላልቅ ሆቴሎችን ማስዋቢያ ጌጣ ጌጦችንም ሰርታ በኤግዚቢሽኑ ላይ ማቅረብ መቻሏን አጫውታናለች፡፡ “የፈጠራ ሥራቸውም ማንኛችን ሰው በቀላሉ በአካባቢው ከሚያገኛቸው ቁሳቁሶች ሊሰራቸው ስለሚችል በበርካቶች ዘንድ አድናቆትን አግኝተናል፡፡ በተለይም ዘይቱ አሁን ላይ በህብረተሰባችን ዘንድ ከመወደዱ ጋር ተያይዞ የበርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ መሳብ ችሏል” ስትል ስለውድድሩ አውግታናለች፡፡

በውድድሩም ላይ ከሐዋሳ ከተማ የተውጣጡ ትምህርት ቤቶች መምህራን ባቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች ውድድር ተካሂዶ መምህርት ጸጌሬዳ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች፡፡ በዚህ ደግሞ የእውቅና ሰርተፍኬት እና የብር ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡ በተመሳሳይ በሲዳማ ክልል አቀፍ በተደረገው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ላይ ባደረገችው ተሳትፎ ሁለተኛ ደረጃ መውጣት ችላለች፡፡ በዚህም ውድድር ደግሞ የብርና የእውቅና ምስክር ወረቀት ተብርክቶላታል፡፡

“ሌላው ደግሞ ከሰል ያመረትንበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይህ ማለት ከሰሉን ለማምረት የተጠቀምነው የከብቶች አዛባ(እዳሪ) ለማጣበቅያነት፣ አመድና የተጣለ ደቃቅ ከሰል በመጠቀም ሶስቱን በመቀላቀል የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችን በመጠቀም ከሰል አምርተናል። አሁን ላይ የከሰል ዋጋ ኩንታሉ ከአንድ ሺህ ብር በላይ ነው፡፡ እኛ ያመረትነው ከሰል ግን በቀላሉ እያመረቱ ማግኘትና መጠቀም ይቻላል” ስትል በኤግዚቢሽኑ ላይ ስላቀረቧቸው ምርቶች አውግታናለች፡፡

ተማሪዎቹ በመምህራኖቻቸው በመታገዝ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን መስራት መቻላቸውን መምህርት ጽጌሬዳ ትናገራለች። ለአብነት ጁስ መስሪያ ማሽን፣ አጉሊ መነፅር እና ሌሎች ሥራዎችን ከሌሎች መምህራን ጋር በመሆን ሰርታለች፡፡ በውድድሩም የተለያዩ የዕውቅና ሰርተፍኬቶችን ማግኘታቸውን መምህርት ጽጌሬዳ ትናገራለች፡፡

በቀጣይ የተለያዩ ችግር ፈቺ ናቸው ብላ የምታስባቸውን የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን የመስራት ዕቅድ አላት፡፡ ጨፊ ኮቲጀ ቤሳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕስ መምህርና አስተማሪዎች ያደረጉላት እገዛ ከፍተኛ መሆኑንም ገልፃለች፡፡