በአጋር ድርጅቶች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የመንግስት የልማት ክፍተት በመሙላት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በመንግስት ከሚተገበሩፕሮጀክቶች በተጨማሪ በአጋር ድርጅቶች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የመንግስት የልማት ክፍተት በመሙላት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም የ2017 በጀት ዓመት የፋይናንሻል አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 ዕቅድ አቅጣጫ ላይ የምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ አካሂዷል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሚሊዮን ዓለሙ እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት ከፌደራል ገንዘብ ሚኒስተር እና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እና በመቀናጀት ድህንነትን ለመቀነስ ከሚተገበሩ ፕሮግራሞች አንዱ የዋን ዋሽ ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡

የብሄራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም በክልሉ ባሉ ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ወረዳዎች በመድረስ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሆነ ፕሮግራም መሆኑን በመግለፅ የውሃ ሽፋን ማስፋፋት እና ተደራሽ ማድረግ፣የጤና ተቋማት መገንባት እና ትመህርት ባልተዳረሰባቸው አከባቢዎች ትምህርት ቤት በመገንባት ተደራሽ ማድረግ ዋነኛው ዓለማው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የ2017 የፋይናንሻል አፈፃፀም ሪፖርት እና የዋን ዋሽ ፕሮግራም በአቶ ጌታሁን ታደሰ እና በአቶ ሳሙኤል ታምሩ የቀረበ ሲሆን በሪፖርቱ ዙርያ ከዞን ከከተማ አስተዳደር እና ከወረዳ የመጡ ባለሙያዎች ሃሳብ አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡

ሃሳብ አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል አቶ ምትኩ መጫሎ ከከፋ ዞን፣ አቶ አድማሱ ጎሹ ከኮንታ ዞን እና አቶ አርጀፎ አያና ከሸካ ዞን እንደተናገሩት የብሄራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም ከመንግስት ጎን በመሆን የዜጎች የመልማት ጥያቄን እየመለሰ ያለ መሆኑን ተናግረው በትምህርት፣ በጤና እና በውሃ ግንባታዎች ላይ ጥራት እና ቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀው የጨረታ አወጣጥ ላይ የሚታዩ ጉድለቶች በመለየት እንዲሁም የሚለቀቀው በጀት ለታለመለት ዓለማ እንዲውል ተለይቶ ቢቀርብ ብለዋል፡፡

በቀረበው ሃሳብ አስተያየት ዙርያ ቀጣይ አቅጣጫ እና ማጠቃልያ በፋይናንስ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሚሊዮን ዓለሙ እና በውሃ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ታምሩ ምላሽ እና ማብራርያም ተሰጥቷል፡፡

ጊዜው እና እድሉ ካለን በገኘን አጋጣሚ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሚሊዮን ዓለሙ ሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ወረዳዎች ያሉበቸውን ችግሮች በአጭሩ እንዲቀርፉ አፅንኦት ሰጥተውበታል፡፡

መርሃ ግብሩም ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆ ሲሆን ከፌደራል፣ ከዞን፣ ከከተማ አስተዳደር እንዲሁም ከወረዳ የተወጣጡ በለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሁነዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ተመስገን ዳጉሳ – ከሚዛን ጣቢያችን