ከአስራ ሁለቱ አንዱ!

አለምሸት ግርማ

ሰላምታ ማህበራዊ ትስስር ከሚጠናከርባቸው መገለጫዎች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ሰዎች አብሮነታቸውን እና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ሰላምታን ይሰጣጣሉ። በተለይም እንደ እኛ ጠንካራ ባህልና ማህበራዊ ግንኙነት ባላት ሀገር ውስጥ ሰላምታ ትልቅ ትርጉም ያለው ማህበራዊ መስተጋብር ነው።

ደስታንም ሆነ ችግርን በጋራ ማሳለፍ ባህል በሆነባት ሀገራችን ደግሞ ትልቅ ከበሬታ አለው-ሰላምታ።

አሁን አሁን ቴክኖሎጂው፣ የስራ ሁኔታና የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ በመለዋወጡ የሰዎች ማህበራዊ ግንኙነትም መጠኑ እየቀነሰ ይገኛል። በአንፃሩ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሌሎችን ሲጥሉና ሲበድሉ እየታየ ነው።

በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እየቀረ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ጎልቶ መታየት ከጀመረ ውሎ አድሯል። ምዕራባዊያኑ በሀገራት መካከል “ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅነት የለም” እንደሚሉት ማለት ነው። በጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ደግሞ ጥቅሙ ሲቀር ሌላውም አብሮ የሚቀር ነው።

በአንድ ወቅት ወዳጅ የነበሩ ሰዎች ወዳጅነታቸው ይቀርና ጠላት የሚሆኑበት አጋጣሚም እየተበራከተ ይገኛል። አብረው ሲወጡና ሲገቡ የነበሩ ሰዎች በሌላ ጊዜ አንዱ ለሌላው ስጋት ጭምር ሊሆኑ ይችላሉ።

ወዳጅነት ማለት በደስታ ጊዜ አብሮ መሆን ብቻ ሳይሆን አንዱ ለሌላው የክፉ ቀን አለኝታ መሆን ማለት ነው። አብሮ ሰርቶ፣ አብሮ ማደግ ደግሞ ትልቅ ጥቅም የሚያስገኝ ጠቃሚ ልማድ ነው። አንዱ እውቀቱን ሌላው ገንዘቡን ወይም ጊዜውን በማቀናጀት ቢሰሩበት ከራሳቸው አልፈው ሀገርን የሚደግፍ ኢኮኖሚ መፍጠር ይችላሉ።

በዚህም አብረው በመስራት ከትንሽ ወይም ከባዶ ተነስተው ትልቅ ደረጃ የደረሱ ብዙዎች ናቸው። ይህ የሚሆነው ጠንክሮ ከመስራት በተጨማሪ በሰዎች መካከል እውነተኛ መተማመን ሲኖር ብቻ ነው።

ሲደክም ሊደግፈው፤ ሲወድቅ ሊያነሳው በሚያስችል ገመድ ሲተሳሰሩ ብቻ ነው ይህ መልካም አላማ ከግብ የሚደርሰው። አሁን አሁን ግን በስራ ሰበብ የተጀመረ ግንኙነት መጨረሻው መቀናናትና መጠፋፋት ሲሆን እየተስተዋለ ነው። አንዱ ከአንዱ ሲበልጥ ማየት የማይወዱ ሰዎች በሚያድርባቸው ክፉ ሃሳብ ተነስተው ባመናቸው ሰው ላይ ክህደት ይፈፅማሉ።

በዚህ ክፉ ሃሳብ ተመርተው በቅርብ ወዳጃቸው በንብረቱ አሊያም በህይወቱ ይመጡበታል። ሰላማዊ ህይወቱን የስቃይ ያደርጉበታል። አለፍ ሲልም ውድ ህይወቱን ይነጥቁታል። በዚያም ከጊዜያዊ ደስታ በቀር የሚያገኙት ትርፍ አይኖርም። ይልቁንም ሚዛኑን በማይስተው ለህሊና ፍርድ ተላልፈው ይሰጣሉ እንጂ።

በሰው ላይ በደልን የፈፀመ አካል በሰላም ሊኖር አይችልም። ማንም ባያውቅበት እንኳን ውስጡ ሰላምን ሊሰጠው አይችልም። በተለይም በሚተማመኑ ሰዎች መካከል የሚፈፀም ክህደት ከተፈፀመበት ይልቅ የፈፀመው አካል ሰላም አይኖረውም።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ ምድር ለመጣበት ዓላማ ይረዱት ዘንድ 12 ሐዋሪያትን መርጦ ነበር። አብረው ይውላሉ፣ ያድራሉ። እርስ በእርስ የጠነከረ ወዳጅነትም ነበራቸው። ይሁዳም ጌታ ኢየሱስን ከሚከተሉት 12ቱ ሐዋሪያቶች መካከል የነበረ የቅርብ ሰው ነው። የክርስቶስ የቅርብ ወዳጅ። ለአንድ ዓላማ የቆሙ ህብረትና አንድነት ያላቸው ነበሩ።

ይሁን እንጂ ከ12ቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ ወዳጅነቱንና ታማኝነቱን በማጉደል ከዕለታት በአንዱ ቀን ጌታውን ለገንዘብ አሳልፎ ለመሸጥ አሰበ። ጌታን ፈላጊዎችም አጋጣሚውን ተጠቀሙበት። ጌታውን አሳልፎ ከሰጣቸው ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚሰጡት በመንገር አስማሙት።

በጊዜው ለጌታው ከመታመን ይልቅ የሚያገኘው ገንዘብ ደስታን የሚሰጠው መሰለው። ጌታውን ሽጦ በገንዘቡ የተሻለ ደስታን ለማግኘት ብዙ አቀደ። በልቡም ይሔን አጋጣሚ መጠቀም እንዳለበት ወሰነ። በውሳኔውም መሰረት ከገዢዎች ጋር ተስማማ። ስምምነቱንም አፀና።

ጌታውን ለመሸጥ ባሰበበት ወቅት ጌታውን ከሌላው ጊዜ በተለየ ሳመው። ሰላምታው ግን የፍቅር አልነበረም። ይልቁንም ከገዢዎቹ ጋር የሚግባቡበት መንገድ ነበር። ሰላምታ የፍቅር መግለጫ ቢሆንም እሱ ግን ጌታውንና የቅርብ ወዳጁን ለሞት አሳልፎ የሰጠበት መንገዱ ነበር።

ይሁዳ ጌታ ኢየሱስን ሲስመው ወታደሮቹ በፍጥነት መጥተው ያዙት፤ እንደ ወንጀለኛ ለፍርድ አቀረቡት። ይሁዳም የጓጓለትን ገንዘቡን ተቀበለ።

ነገር ግን ይሁዳ እንዳሰበው ደስታን አላገኘም። ጌታውን ስሞ ለሞት አሳልፎ ከሰጠው በኋላ ፀፀት ላይ ወደቀ። በሰራው ስራ ሰላሙን ከማጣቱ የተነሳ ራሱን ሊያጠፋ ችሏል። ይሔም በሌሎች ላይ በተለይም በሚያምኑን ላይ በደልንና ክህደትን መፈፀም ምን ያህል ከባድ መሆኑን የሚያስተምረን ነው።

ክፉ ስራ ሰላምን ስለማይሰጥ ይሁዳ እንዳሰበው በገንዘቡ አልተደሰተበትም። ይልቁንም መኖሩን ጠላው እንጂ። በሰላም ሲኖር የነበረው ሰው በሰራው ክፉ ስራ ሌላውንም በድሎ፤ ራሱንም ችግር ውስጥ ከቷል። ስለዚህ ሰዎች በመካከላቸው በሚኖራቸው አለመተማመን የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ህይወት ሰላም ያሳጣሉ። በመሆኑም የሰዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት መተማመን ከሌለበት ትርፉ ፀፀት ነው።   

ህሊና ማንንም ከማንም ሳይመርጥ፣ ሳያዳላ የሚፈርድ ዳኛ ነው። ሰው ክፉ ሰርቶ በሰላም ማደር አይችልም። ነገር ግን ወዳጅነትን ማስቀደም ለሁሉም የሚጠቅም ከመሆኑም በላይ ከህሊና ወቀሳም ያድናል።

የወደቀውን ልናነሳው እንጂ ለጥቅም እንደድልድይ ልንጠቀምበት አይገባም። ለሌሎች በተለይም ለወዳጆቻችን ክፋትን ማሰብ ጤናማ አስተሳሰብ አይደለም። ለጥቅማችን ስንል ሌሎችን ጠልፎ የመጣል ልማድ ልናስወግድ ይገባል።

እርስ በእርስ የሚኖረን ግንኙነት መተማመንን መሰረት ማድረግ አለበት። ወዳጅነት እምነትን ሲጨምር ውጤቱ ያማረ ይሆናል። መካካድንና መወሻሸትን ከመካከላችን በማስወገድ የግንኙነታችንን መሰረት እውነት ላይ ልናደርግ ይገባል። በዚህ ጊዜ ለሌላው እንቅፋት መሆናችን ይቀራል። በተጨማሪ ለህሊና ክስም አንጋለጥም። በመሆኑም ከሌሎች ጋር በሚኖረን ማንኛውም ግንኙነት በመካከላችን እውነት እንዲጠነክር ልናደርግ ይገባል።

ወቅቱ የአቢይ ፆም መገባደጃ በመሆኑ በማወቅም ባለማወቅም በውስጣችን የተዘራ ክፉ ሃሳብ ካለ ከቡቃያው በመንቀል በውስጣችን እውነትንና ፍቅርን እንዝራ።

ከ12ቱ አንዱ ሆኖ ክህደት እንደፈፀመው ይሁዳ ልባችን ወደ ገንዘብ እንዳያደላ የሚበልጠውን ለመያዝ ማስተዋል ያስፈልገናል። በተለይም እምነታቸውን ለጣሉብን ወዳጆቻችን መልካም እየመሰልን በስውር እንዳንጎዳቸው ልንጠነቀቅ ይገባል። ክርስቶስ የወደደን በእውነተኛ ፍቅሩ በመሆኑ እኛም ለሌሎች እውነተኛ እንሁን!