የወረዳው ነዋሪዎች የበሽታውን አስከፊነት በመረዳት የወባ ቁጥጥር ሥራ በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጋሞ ዞን የወባ በሽታ ከሚከሰትባቸው ቆላማ አከባቢዎች አንዱ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የላንቴ ቀበሌ ነው።
በባለፉት ጊዜያት ወቅቱን ጠብቆ የሚከሰተው የወባ ስርጭት ከሁለት ዓመታት ወዲህ መቀነስ መቻሉን የወረዳው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ወ/ሮ ምንትዋብ ምትኩ እና ውድነሽ ዓለሙ የቀበሌው ነዋሪዎች ሲሆኑ፥ በጤና ልማት ቡድን ታግዘው ያቆሩ ውሃዎችን በማፋሰስ፣ የአልጋ አጎበር በአግባቡ በመጠቀማቸው እና የጤና ባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ በማድረጋቸው የተነሳ የወባ በሽታን መቆጣጠር መቻላቸውን ገልጸዋል።
ቀበሌያቸው ከአባያ ሐይቅ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ ለወባ መቀስቀስ ምቹ በመሆኑ ሳይዘነጋ ወባ ትንኝ የሚራባባቸው አከባቢዎችን የማጽዳት ሥራ መስራታቸውን አክለው ገልጸዋል።
የላንቴ ቀበሌ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ወ/ሮ ጥበቧ ሰይፉ በሁሉ መንደሮች የጤና ልማት ቡድን በማደራጀት ስለ ወባ በሽታ መከላከል በቂ የግንዛቤ ትምህርት በመሠጠቱ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል ብለዋል።
የላንቴ ቀበሌ ጤና ጣቢያ ሀላፊ አቶ አድማሱ ኦንኬ በበኩላቸው የጤና ጣቢያው ሠራተኞች በዘመቻ መልክ ወደ ህብረተሰቡ ውስጥ በመግባት የግንዛቤ ትምህርት በመስጠታቸው የወባ ቁጥጥር ሥራ መሰራቱንና በዚህም ወባ ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ኢያሱ እሸቱ በወረዳው በወባማ ቀበሌያት ላይ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የወባ በሽታን የመከላከሉ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ ሥርጭቱን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።
በወረዳው በቆላማ ቀበሌያት እርጥበትንና የዝናብ ወቅትን ተከትሎ ሚቀጥሉት ወራት ወባ የሚከሰትበት ወቅት በመሆኑ የቁጥጥሩ ሥራ እንዲጠናከርም ሀላፊው አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ክርስቲያኑ የ2019 ዓ.ም የእንቁጣጣሽ በዓልን በሚያከብርበት ወቅት አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሀይማኖት አባቶች ተናገሩ
የ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ታላላቅ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት እና የዲጂታል ሽግግር የሉዓላዊነቷ ምሰሶ መሆን የቻለችበት አመት መሆኑን አቶ አልማው ዘውዴ ገለፁ
ጳጕሜን 5 “የነገው ቀን” በኮሬ ዞን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው