በደረሰ አስፋው
ከትንሹ ሶስት ሺህ እስከ 16 ሺህ ብር ዋጋ የሚጠራባቸው ፍየሎች አሉ፡፡ የፍየል ሙክቶች በእርግጥም ሰንጋን ያስንቃሉ። ቀልባቸው ያረፈበትን በዋጋ ሳያቅማሙ ከፍለው ሲወጡም ተመለከትኩ፡፡ በጥሩ የአቀራረብና የመስተንግዶ ባህሪዋ ደንበኞቿን ለማስተናገድ ትጣደፋለች፡፡
የምታደርገው የማግባባት ስራም በስራው ልምድ ያካበተች ስለመሆኗ አመላካች ነበር፡፡ በፍየሎቹ ቀንድ ላይ ዋጋ የተጻፈባቸው ቢሆንም አንዳንዱ ግን ዋጋ መከራከሩ አልቀረ፡፡ የባጃጅ እንኳ ቀንሽ ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡ ሳይከራከሩ የተባለውን ዋጋ ከፍለው የሚሄዱም አሉ፡፡
በፍየል ንግዱ ላይ አተኮርኩ እንጂ በእቱ መለኛዋ ግቢ የማይሰራ ስራ እንደሌለ በነበረኝ ቆይታ መረዳት ችያለሁ፡፡ ወደ ኩሽና ጎራ ሲባል በእንጀራ መጋገር ስራ የተጠመዱ ሴቶችን ተመለከትኩ፡፡ ይህም የንግዷ አካል እንደሆነ ገለጸችልኝ፡፡ ከዚህ ባሻገር በቤቷ ውስጥ ዳጣም ታዘጋጃለች፡፡ አዟዙራ ባሳየችኝ የንግድ ዘርፎቿ መደመሜ አልቀረም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎችም የስራ ዘርፎች እንዳሏት ከገለጸችልኝ በኋላ በስኬቷ ዙሪያ ለመነጋገር አጭር ጊዜ ሰጠችኝ፡፡ በመተዋወቅ ነው የጀመርነው፡፡
ወ/ሮ መሰለች ማሴቦ ትባላለች፡፡ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ዳቶ ቀበሌ ነዋሪ ናት። በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን ሽንሽቾ ከተማ ነው የተወለደችው፡፡ ትዳር መስርታ በሀዋሳ ከተማም ለ20 ዓመታት ቆይታለች፡፡
ሀዋሳም የቤት እመቤት በመሆን ለዓመታት ቀይታለች፡፡ በንግድ ስራ ከሚተደደሩ ባለቤቷም አራት ልጆች አፍርታለች፡፡ ይሁን እንጂ የትዳሯ አጋር በድንገተኛ የተሽከርካሪ አደጋ ህይወታቸው አለፈ፡፡ የባለቤቷ ከጎኗ መለየት ከፈጠረባት ሀዘን ባሻገር ለችግር አጋለጣት፡፡ አራት ልጆችን ይዞ ህይወትን መምራት ተሳናት። ከገጠር ወጥቶ ለማያውቅ ሰው ልጆችን ተንከባብቦ፣ አስተምሮ ለቁም ነገር ለማድረስ ጫናው ከአቅሟ በላይ ሆነ፡፡ ቀኑ ጨለመባት፡፡ የቤት እመቤት ሆኖ በቤት ውስጥ መቀመጥ ጉዳቱን የተገነዘበችውም ያኔ፤ ባለቤቷ በሞተ ማግስት ነበር፡፡
ወደ ትውልድ አካባቢዋ ለመመለስ ብታስብም ችግሩ ይብስ ይሆን እንጂ ቀላል እንደማይሆን ተገነዘበች፡፡ ሀሳቡን አውጥታና አውርዳ መፍትሄ ያደረገችው በሀዋሳ ከተማ በመረጠችው የስራ ዘርፍ መሰማራት ሆነ። የመጀመሪያ ስራዋ ያደረገችውም አንባሻ ጋግሮ መሸጥን ነበር፡፡ የአንባሻ ንግዱም እንጀራ ጋግሮ መሸጥን አስቀጠለ፡፡ በስራዋ በርካታ ደንበኞችን አፈራች፡፡ ለሻይ ቤት፣ ለሱቅና ለሆቴሎች አንባሻና ደረቅ እንጀራ እያስረከበች የገቢ አቅሟን አሳደገች፡፡ አንዱ ስራ ወደ ሌላ ስራ ይመራል ያለችው መሰለች፤ የእንጀራ ጋገራው ሌላ ስራ እንድትጀምር ዕድል ፈጠረላት፡፡
ፍየሎች ወደ ሀዋሳ በማምጣትና በመሸጥ ሌላ ስራ ጀመረች፡፡ ለተወሰኑ ሆቴል ቤቶች በማቅረብም ገበያውን አጠናች፡፡ በሂደትም በርካታ ፍላጎት እንዳለና ገበያውም አዋጭ እንደሆነ ተረዳች፡፡ ከአዶላ እና ሌሎች ቦታዎች ፍየሎችን በማምጣት ሀዋሳ፣ ሻሸመኔና አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ ለበርካታ ደንበኞች በማቅረብ የገበያዋን አድማስ አሰፋች፡፡ በፍየል ሙክት ንግድ ከተሰማራች 3 ዓመት እንደሆናት የምትገልጸው መሰለች፤ “ቤቴ ሁሌ ገበያ ነው” ብላለች፡፡
የደረቅ እንጀራ ንግዱም አልቆመም። ስራው ትናንት፤ ችግር በነበረ ጊዜ ቀን ያወጣላት እንደሆነ ነው የምትገልጸው። አሰራሩን እያዘመነች የገበያ መዳረሻዋን ለማስፋት እንጂ ስራውን ለማቆም ሀሳቡ እንደሌላት የምትገልጸው መለኛይቱ መሰለች፤ ሆቴል ቤቶች፣ ሱቆች፣ አነስተኛ ምግብ ቤቶችና ለድግስ በሯን የሚያንኳኩ በርካቶች እንደሆኑ ነው የምትናገረው፡፡ ከመናኸሪያ እስከ ዳቶና ጥቁር ውሃ የሚዘልቀው ገበያዋ በቀን በ400 እንጀራ ጀምሮ ዛሬ ግን ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ማለቱን ነው የምትናገረው፡፡
መሰለች በእንስሳት እርባታ ተሰማርታ እንደነበር ታነሳለች፡፡ 6 የውጭ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞች እነደነበሯት በመጠቆም። ወተትን ለተጠቃሚዎች በማከፋፈል፤ ከዚህም ተጠቃሚ እንደነበረች ብትገልጽም ይህ የቦታ ጥበትና የመኖ ችግር ተጽእኖ ስለፈጠረባት ማቋረጧን ነው የተናገረችው፡፡
ወደ ሀዋሳ ከመጣች በኋላ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብላ ታነሳለች፡-
“በባለቤቷ ገቢ መተዳደር ለለመደች አንዲት የገጠር ልጅ ድንገት ባለቤቷ ከጎኗ ሲለይ አራት ልጆችን ይዞ መኖር ሸክሙ ከባድ ነበር፡፡ ህመሙ ብዙ ነው፡፡ የከተማውን መውጫና መግቢያ እንኳን አላውቅም። ልጆች ከማሳደግ ውጭ የማውቀው ስራ እንኳ አልነበረም፡፡ በጥቂቱም ለሙከራ አንባሻ መሸጥ ጀመርኩ፡፡ ከቤቴ ፊት ለፊት ያለው ሻይ ቤትና ሱቅም የመጀመሪያዎቹ ተረካቢዎች ነበሩ፡፡ እየዋለ ሲያድር ፍላጎቱ ሰፊ መሆኑን አረጋገጥኩና በስፋት መስራት ጀመርኩ፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ለሙከራ ብዬ ደረቅ እንጀራ ጀመርኩ፡፡ ፍላጎቱ እየጨመረ መጣ፡፡ ይህም ይበልጥ ለስራ አነሳሳኝ። ምሽት ላይ የጀመርኩትን ስራ ሳልጨርስ ይነጋብኝም ነበር፡፡ እቁብ በመግባትና በመቆጠብ አዳዲስ ስራዎችን በመጀመር ለዛሬ ደርሻለው፡፡”
ዛሬ ላይ ልጆቿም አድገው ለቁም ነገር ደርሰዋል፡፡ ሴት ልጇ ከዩኒቨርስቲ ተመርቃ ስራ ይዛለች፡፡ ወንድ ልጇም ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በመማር ላይ ይገኛል፡፡ ሌሎች ልጆቿም በትምህርት ላይ እንዳሉ ነው የገለጸችው፡-
“ታታሪነት ምልክቴ ነው፡፡ ለሌሎች ሴቶችም መነሳሳትን ፈጥሬያለሁ፡፡ በቤት ውስጥ የምሰራቸው መደበኛ ስራዎቼ እንዳሉ ሆነው ሌሎች ስራዎችን እሰራለሁ። የማልሰራው ስራ የለም ማለት ይሻላል። በጎመን ሰአት ከጎሬና ሀገረ ሰላም ጎመን በመኪና አመጣለሁ፡፡ የእሸት በቆሎ ጊዜም እንዲሁ ምርቱ በስፋት ካለባቸው አካባቢዎች እያመጣሁ ለተረካቢዎች አከፋፍላለሁ፡፡”
መሰለች በበርካታ የስራ ዘርፎቿ ከራሷ አልፋ ለብዙዎች የስራ እድል ፈጥራለች፡፡ በመኪናዋ ላይ አንድ ሹፌርና ሁለት ረዳቶች አሉ፡፡ በእንጀራ ጋገራ ስራዋ ለአራት ሴቶች የስራ ዕድል ፈጥራለች፡፡ በየዕለቱ በቀን ስራ ከጎኗ የማይለዩ ሰራተኞችም አሉ፡፡ በችግር ውስጥ የነበሩ አራት ህጻናትንም ታሳድጋለች። እነዚህንም ልጆች እንደራሷ ልጆች አቅፋና ደግፋ ታስተምራለች፡፡
“በአካባቢዬ ላሉ በርካታ ሴቶች ምክሬንና ድጋፌን አልነፈኳቸውም፡፡ ቤት ከምትቀመጡ ስሩ እላለሁ፡፡ ጎመን እና እንጨት በዱቤ ወስደው ቸርችረው ዋናውን ዋጋ መልሰው በትርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አደርጋለሁ፡፡ ነገን ማየት እንዲችሉ አቅጣጫን አሳያቸዋለሁ፡፡ ተሰርቶ እንጂ ቁጭ ብሎ ውጤት አይገኝም እላለሁ”
መሰለች በዳጣም በርካታ ደንበኞችን ያፈራችበት የስራ ዘርፍ ነው፡፡ በሀዋሳ ያዘጋጀችውን ዳጣ ከሀዋሳና አካባቢው አልፎ ወደ ሞያሌ፣ ቦሬ፣ ነጌሌ፣ ትልካለች፡፡ በዚህም የስራ ዘርፍ ለበርካታ ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ እድል እንደፈጠረች አልሸሸገችም፡-
“ስራዎች እርስ በርስ የሚደጋገፉ ናቸው። ለኪሳራ የሚዳርጉ አይደለም፡፡ ከተሰራ ያተርፋል እንጂ አያከስርም፡፡ በታታሪነቴ ብዙ ወዳጆችን አፍርቻለሁ፡፡ አይዞሽ በርቺ እያሉ የሞራል ስንቅ የሆኑኝ በርካቶች ናቸው”
ትናንት ከምንም ነገር የተነሳው ስራዋ ዛሬ ካፒታሏም አድጓል፡፡ ከዛሬ ሶስት አመት በፊት በ3 ሚሊዮን ብር መኪና መግዛቷን ገልጻለች፡፡ በቤት ውስጥ በቋሚና በተንቀሳቃሽ ንብረት ያለ ሀብትም አለ። በትውልድ አካባቢዋም የእንስሳት ማደለቢያ ከፍታለች፡፡ ዘርፉን በማዘመን ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲያደርጋት እየሰራች መሆኑንም በመጠቆም፡፡ በፈጠረችው ሰፊ ካፒታልም የደለቡ የቁም እንስሳትን ወደ ውጭ የመላክ ውጥን አላት፡፡ ለዚህም የንግድ ፈቃድ በማውጣት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየሰራች እንደሆነ ነው የገለጸችው፡፡
“ታታሪነት ምልክቴ ነው” ትላለች፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው