ከተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተርታ ለመሰለፍ

ከተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተርታ ለመሰለፍ

በደረሰ አስፋው

በ13 ዓመቷ ነው የውድድር ተሳትፎዋን ሀ ብላ የጀመረችው፡፡ አሁን ላይ 22 ዓመቷ እንደሆናት ነው የገለጸችልኝ፡፡ በሀዋሳ ከተማ መነሻውን ያደረገው የውድድር ተሳትፎዋ እያደገ ክልሎችን ወክላ በሀገር አቀፍ ውድድሮች እስከመሳተፍ ደርሳለች፡፡ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በውድድሩ ከወርቅ እስከ ብር ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችላለች፡፡ በተሳተፈችበት የፓራኦሎምፒክ ውድድሮችም የካበተ ልምድ አግኝታበታለች፡፡ የቀድሞውን የደቡብ ክልል ወክላ በድሬዳዋና ባህርዳር በተደረጉ ውድድሮች ድልን የተጎናጸፈችባቸው ዘመኖች ነበሩ፡፡

“አካል ጉዳተኛ መሆን ተስፋ የሌለው ሰው መሆን አይደለም ስትልም ተሸናፊ የሆነ አስተሳስብ ማራመድ ተገቢ አለመሆኑን ታነሳለች፡፡ ከተሰራ መለወጥ ይቻላል፤ ስለሰራሁ ማሸነፍ ችያለሁ፡፡ ለዚህም የአመለካከት ለውጥ ከራስ ይጀምራል፡፡ እኔ የነገ ህልሜ ሩቅ ነው፡፡ ይህን እንደማደርገው ደግሞ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ያለፉት የውድድር ጊዜያት የአሸናፊነት ስነ ልቦናዬ እያደገ እንጂ እየከሰመ አይሄድም፡፡ በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ውድድርም የወርቅ ሜዳሊያ እንደማመጣ እርግጠኛ ነኝ” ስትል ነው ሀሳቧን የጀመረችው፡፡

መጠኑና አይነቱ ይለያያል እንጂ ሰዎች በህይወት አጋጣሚ በችግር ውስጥ ያልፋሉ፤ በችግርም ይፈተናሉ፤ በግልም ይሁን በተፈጥሮ ችግሮች አጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃሉ፤ ይህንንም ለማሸነፍ ደፋ ቀና ይላሉ፤ የተደላደለ ህይወት ለማግኘት ብዙ ርቀት ይጓዛሉ፤ ብዙ መሰናክሎችንም ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዛሬው የችያለሁ አምድ የመቻል አብነታችንም የዚሁ ሀሳብ መገለጫ ነች፡፡ ያጋጠማትን የአካል ጉዳት እንደ ድካም ሳይሆን እንደብርታት ነው የተጠቀመችበት። ሀገሯንም በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ ስሟን ከፍ የማድረግ ዓላማን ሰንቃ ነው እየተንቀሳቀሰች ያለችው፡፡

ረቂቅ ተገኝወርቅ ትባላለች፡፡ ሐዋሳ ከተማ ሞቢል ሰፈር ተወልዳ ያደገችበት መንደር ነው። የቤተሰቧ 3ኛ ልጅ የሆነችው ረቂቅ በአንድ እጇ ላይ በተፈጥሮ የተከሰተው አካል ጉዳት ያሰበችውን ከማሳካት አላገዳትም፡፡ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ በቤተልሄም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ፣ ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ደግሞ በምስራቅ ጮራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡

ከአስረኛ ክፍል በኋላ ግን ወደ አዲስ አበባ ነው ያቀናችው፡፡ የፓራኦሎምፒክ ተወዳዳሪ ሆና ባስመዘገበችው ውጤት ተመልምላ በአካዳሚ የሚሰጠውን ስልጠና ለመከታትል ዕድል ማግኘቷ ወደ አዲስ አበበ የመሄዷ ምክንያት ነው፡፡ ከስልጠናው ጎን ለጎን የሚኖራትን ትርፍ ጊዜም በአድማስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ በዲፕሎማ ተመርቃለች፡፡

የቀድሞውን የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልልን ወክላ ነበር የሄደችው፡፡ በዚህ ውድድርም ሁለተኛ ወጥታ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነች፡፡ ይህ ውጤት ይበልጥ አቅሟን የምታሳድግበትን እድል ፈጠረላት፡፡ የተሻለ ስራ ከተሰራ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ ተገነዘበች፡፡ ያስመዘገበችውን ውጤት የተመለከቱ የክልሉ ኃላፊዎችም ለተጨማሪ ስልጠና በር ከፈቱላት፡፡ በተፈጠረላት የስልጠና ዕድል አዲስ አበባ የስፖርት አካዳሚ ገብታ ስልጠና እንዳገኘች ነው የተናገረችው፡፡

ይህ የስልጠና ዕድል ይበልጥ አቅም ፈጠረላት። በተለምዶ ከምታደርገው ልምምድ ይልቅ ልምዱና ዕውቀቱ ባላቸው ባለሙያዎች ስልጠናውን በማግኘቷ ለቀጣይ ጉዞዋ ስንቅ ሆናት፡፡ ከድሬዳዋ ውድድር በኋላ በባህር ዳር እና ሌሎች ውድድሮች ላይ በመሳተፍ አመርቂ ውጤት አስመዘገበች። አሰላ ላይ በተደረገው የፕሮጀክት ምልመላ ውድድሮች ተመሳሳይ ውጤት በማምጣቷ የተሰጣትን ስልጠና በአግባቡ ተጠቅማበታለች፡፡

በአጭር ርቀት የ1ዐዐ እና የ200 መቶ ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ የምትሳተፈው ረቂቅ አነሳሷን ስትገልጽም፡-

“በመጀመሪያ የፓራኦሎምፒክ ስፖርት ውድድር እንዳለ አላውቅም ነበር፡፡ ቼሻየር ድርጅት ውስጥ የፓራኦሎምፒክ አሰልጣኝ ነበር፡፡ በዚህ ዘርፍ አካል ጉዳተኞች መሳተፍ እንደሚችሉ አስታወቀኝ፡፡ በስልጠና ድጋፍ አድርጐ በውድድር እንድሳተፍ ምክሩን ለገሰኝ፡፡ ድሬደዋ ላይ በነበረው የመላው ኢትዮጵያ የሴቶች ውድድር ላይ የመጀመሪያ ተሳትፎዬን አደረኩ፡፡ በዚህም ውጤታማ ሆንኩ፡፡ ይህም ለቀጣይ ውድድሮች አነሳሳኝ ትላለች፡፡

ፍላጎት፣ ጥረት እና አሁን ያለችብት ዕድሜና ውጤት ታክሎበት በፓራኦሎምፒክ የሀገር ተስፋ ነች፡፡ 7ኛ ክፍል እያለች ነው በሃዋሳ ከተማ በፓራኦሎምፒክ ውድድር ላይ መሳተፍ የጀመረችው፡፡ ይህም እያደገ መጥቶ ዛሬ ላይ ለውጤት አብቅቷታል፡፡ አዲስ አበባ በአካዳሚ ለ4 ዓመታት የሚሰጠውን ስልጠና መውሰዷ በርካታ ጥቅሞች ያገኘችበት እንደሆነም ታነሳለች። እስካሁን በፓራኦሎምፒክ ስፖርት ዘርፍ ክለብ አለመኖሩ ተጽእኖ የፈጠረባት ቢሆንም ውድድሮችን በውጤት ለማጠናቀቅ ግን የግል ጥረቷን ከማድረግ ተዘናግታ እንደማታውቅ ነው የተናገረችው፡፡

ከውድድር በኋላ ተመልሶ ወደ ቤት መግባቱ አቅሟ ይበልጥ እንዳያድግ ማድረጉ ግን አልቀረም። ውድድር አለ ወይም የውድድር ጊዜ ቀርቧል ሲባል ልምምዷን የምታደርገው በራሷ ጥረት በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ነው፡፡

አሁን ላይ ከቤተሰብ ጋር ነው የምትኖረው ረቂቅ ተምራ ባገኘችው አካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ ስራ ማግኘት አዳጋች ሆኖባታል፡፡ ይሁን እንጂ ከስፖርቱ ዘርፍ ጎን ለጎን በሀዋሳ ከተማ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት እንደምትሰጥ ነው የተናገረችው፡፡

ኤስዲዲ ድርጅት ውስጥ አካል ጉዳተኞች ላይ ለ6 ወር አገልግላለች፡፡ ስልጠና ለሚወስዱ አካል ጉዳተኞች ስልጠናውን በማመቻቸት ሰርታለች፡፡ በቤተሰብ መምሪያ በሚገኙ ክበቦች ውስጥ በልዩ ፍላጎት ክበብ ውስጥ አካል ጉዳተኞች ያላቸውን ተሰጥኦ አውጥተው እንዲጠቀሙ የምክርና የስነ ልቦና ድጋፎችን በመስጠት ትሳተፋለች፡፡ አካል ጉዳተኞች በስነ ተዋልዶ ዙሪያ ግንዛቤያቸውን የማሳደግ ስልጠና በመስጠት የበጎ ድጋፍ አገልግሎት ተሳትፎ ታደርጋለች፡፡

የቤተሰብ ድጋፍ ተለይቷት እንደማያውቅ የገለጸችው ረቂቅ ምንም እንኳ አቅማቸው ዝቅተኛ ቢሆንም በሞራል እንደሚያበረታቷት ነው የተናገረችው፡፡ ከመኖሪያ መንደሯ እስከ ሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በታክሲ እየተመላለሰች ልምምድ ስታደርግ የቤተሰቦቿ ድጋፍ ተለይቷት አያውቅም፡፡ “በርቺ፤ ይቻላል የሚለው የዘወትር ቃላቸው ጉልበት ሆኖኛል” ስትል ነው የገለጸችው።

ረቂቅ በ2016 ዓ.ም በሚደረገው ሀገር አቀፍ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገች ነው። ወደ መለማመጃ ቦታዋ ልትሄድ እየተዘጋጀች ሳለ ነው ያገኘኋት፡፡ ምንም እንኳ አሰልጣኝ ከጎኗ ባይኖርም በአካዳሚ ቆይታ ያገኘችውን ዕውቀት ተጠቅማ በራሷ አቅም ልምምዷን እንደምታደርግ ገለጸችልኝ፡፡ ካለባለሙያ መለማመዱ ተጽእኖ አልፈጠረብሽም? ብዬ ላነሳሁላት ጥያቄም፡-

“ቢገኝ አይጠላም፡፡ ካልተገኘ ደግሞ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ዋናው ሰዓት ነው፡፡ የግል ፍላጎት፣ ራዕይና ጥረትን በማስተሳሰር ነው የምለማመደው፡፡ ነገ ልደርስበት ያሰብኩትን ግብ እያሰብኩ ነው የምለማመደው። ይህ አስተሳሰብ በውስጥ ከሰረጸ ይቻላል፡፡ በአሰልጣኝም ቢሆን የሚሰጠው ድጋፍ ከዚህ የዘለለ አይደለም” በማለት ነው የተናገረችው፡፡

ወደፊትም በስፖርቱ ዘርፍ ሀገሯን ወክላ በዓለም ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዕቅድ አላት፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ሰዎች በአካል ጉዳተኞች ላይ ያላቸው ግንዛቤ እንዲለወጥ መስራት እንደምትፈልግ ታነሳለች፡፡ ብዙ ጊዜ አካል ጉዳተኞች እንደ ደካማ ፍጥረት እና እንደማይችሉ ተደርጎ የሚታየው አስተሳሰብ ተገቢ ባለመሆኑ ይህን ግንዛቤ በመቀየር ረገድ ላቅ ያለ ስራ ለመስራት ነው ውጥኗ፡፡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ ይህንን አጣምራ ለመስራት እንዳሰበች ነው የተናገረችው፡፡

“ስኬታማ ወጣት ሴት አካል ጉዳተኛ ሆኜ ከተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተርታ መሰለፍ እመኛለሁ፡፡ ለአካል ጉዳተኞችም ብርታት ሆኜ መታየትን እሻለሁ፡፡ እስካሁን በመጣሁበት ህይወት ከቤተሰብ ጀምሮ እንዲህ ነው ተብሎ የደረሰብኝ ተጽእኖ ባይኖርም በተለያዩ መልኩ ሲገለጽ ደግሞ ይስተዋላል፡፡ ስራ ለመፈለግ ስወጣ አካል ጉዳተኛ በመሆኔ እንደማልችል ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከምንጩ መድረቅ አለበት፡፡ ለዚህም ጠንክሬ መስራትን እፈልጋለሁ ነው ያለችው፡፡

ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ምን መልዕክት አለሽ ብዬ ላነሳሁላት ጥያቄም፡-

“አካል ጉዳተኝነት የደካማነት መገለጫ ሊሆን አይገባም፡፡ ምንም እንኳ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው የግንዛቤ ችግር የመገለል አዝማሚያዎች ቢስተዋሉም አካል ጉዳተኛ ሆኖ ትልቅ ስኬት ላይ የደረሱም እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ጉዳትን ተጠቅሞ ለልመና እጅን ከመዘርጋት ይልቅ ፈተናዎችን ተጋፍጦ ከችግር መውጣት አማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነ አካል ጉዳተኞች ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ በተፈጥሮ ተቸግረን ይሁን በጥረታችን ያካበትነውን ተሰጥኦ በማውጣት ወደ ውጤት ልንቀይረው ይገባል፡፡ ተሸናፊ የሆነ አስተሳስብም ማራመድ ተገቢ አይደለም፡፡ የአመለካከት ለውጥ ከራስ ይጀምራል” ስትል ነው መልዕክቷን ያስተላለፈችው፡፡

ረቂቅ አቅሙ ቢፈቅድላት ከስፖርቱ ጎን ለጎን የራሴ የምትለው የንግድ ዘርፍ ላይ የመሰማራት ሀሳብም አላት፡፡ ከታሰበ የማይሆን ነገር የለምና ይህንም ቢሆን ለማሳካትና ህይወቷን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ ውጥን እንዳላት ነው የተናገረችው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ ውድድሮች ምልመላ የሚያካሂደው የፓራኦሎምፒክ ፌደሬሽን ነው፡፡ ሀገርን በመወከል በሚደረገው ውድድርም ምልመላ ከተደረገ በኋላ ስልጠና እና ድጋፍ የሚደረግበት አጋጣሚ አለ፡፡ ከዚህ ውጪ ባለው ጊዜ ግን አብዛኛውን ልምምድም ይሁን ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን በራሳቸው ጥረት እንደሚያሟሉ ነው የምትገልጸው፡፡ በከተማና ክልሎች ላይ የተለየ ድጋፍ የለም፡፡ በልምምድ ወቅት የላብ መተኪያም ቢሆን ከራስ ውጪ ሌላ ድጋፍ የሚያደርግ አካል የለም፡፡

“በዘንድሮው ሀገር አቀፍ የፓራኦሎምፒክ ውድድር የወርቅ ተሸላሚ እንደምሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ የምትለው ረቂቅ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንደሚባለው አሁን ካለኝ ልምምድና ሰዓት አኳያ የተሻለ ውጤት አስመዘግባለሁ የሚል እምነት አለኝ” ስትል ነው ንግግሯን የቋጨችው፡፡