“ስኬት ዓላማን መረዳት ነው”

“ስኬት ዓላማን መረዳት ነው”

በቤተልሔም አበበ

በህይወት መንገድ ላይ የሁሉም ሰው መሻት ስኬታማ ህይወትን መምራት ነው። አንዳንዱ ሰው ዕድሉ ይሆንና እምብዛም ሳይፈተን ይሳካለታል፡፡ ህይወትንም ባሻው መንገድ ይመራታል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ አንዱን የህይወት ተራራ ሲወጣ፣ሌላ ተራራ የሚከተለው፣ አንዱን ጨለማ ሲሻገር ሌላ ጨለማ ከፊት የሚያጋጥመው ይሆናል። በዚህ መንገድ የህይወት ጠመዝማዛ ጉዞ አድክሞት ተስፋ ቆርጦ የሚወድቀው አንድ ና ሁለት አይደለም፡፡ የበረታ ይሻገራል፡፡ የተራራ ግዝፈት ቢያስፈራም፣ እንደሚያልፍ በልቡ አምኖ የተነሳ፣ የጨለማው ግርማ ቢያስደነግጠውም የነገን ብርሃን አሻግሮ በመመልከት ለስኬት ይበቃል፡፡ ልክ እንደዛሬው ባለታሪካችን፡፡

ወጣት ጥጋቡ ወይሳ ይባላል፡፡ ውልደቱ በወላይታ ሶዶ ዙሪያ ኮዳ ካውሊያ ቀበሌ ነው፡፡ ለእናቱ ሶስተኛ ልጅ ነው፡፡ ትምህርቱን ከአንደኛ አሰከ አስረኛ ክፍል ተከታትሏል፡፡ ከዚያም በዲፕሎማ በቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ “በአውቶ ኢንጂን” አንድ አመት ከተከታተለ ቡኋላ በስራ አለመመቻቸት ትምህርቱን ሊያቋርጥ ችሏል፡፡

በትውልድ አካባቢው ከትምህርቱ ጎን ለጎን ብስክሌት በማከራየት ሳንቲም ያገኝ ነበር፡፡ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ብስክሌቱን ሸጠና የሸቀጣሸቀጥ ስራ ጀመረ፡፡ በዚህ ስራ ቢሰማራም ትርፋማ መሆን ባለመቻሉ ከትውልድ መንደሩ ተነስቶ ወደ ሀዋሳ ለመሄድ ተገደደ፡፡

ወጣት ጥጋቡ ወደ ማያውቅበት አካባቢ ኑሮውን ለማድረግ የተነሳው ብቻውን ሳይሆን ከጓደኛው ጋር በመሆን ነበር። ሀዋሳ ሲደርሱ ግን የእሱ እና የጓደኛው ዓላማ የተለያየ ሆኖ አገኘው፡፡

ባለታሪካችን የሚፈልገውን ስራ ለማግኘት ወደ ደላላ ቤት ሄደ፡፡ በትሪ አጣቢነት ለመስራት በወር መቶ ሃያ ብር ተከፋይ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ በወላይታ ባህል ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የመስቀል በዓል ከዘመዶቹ እና ጓደኞቹ ጋር በደስታ ለማክበር ገንዘቡን መቆጠብ ነበረበት፡፡

አንድ አመት እየሰራ ከቆየ በኃላ ጊዜው ደረሰ፡፡ ለመሄድ ሲነሳ አብረውት ይሰሩ የነበሩት የስራ ባልደረቦቹ ያስቀመጠውን ገንዘብ ሳያውቅ ወስደውበት ኖሯል። አዘነ። በዚህም የተነሳም ከሚሰራበት ቤት ወጣ፡፡ ድጋሚ ወደ ሌላ ደላላ ቤት አመራ። የመስተንግዶ ስራም አገኘ፡፡ ስራ ባገኘ በሁለተኛ ቀን፣ ተስተናጋጅ ሰላሳ ብር ይዞበት ሄደ፡፡ እንደገናም ደላላ ቤት ሄደ፡፡

በተመሳሳይ ሌላ ሆቴል በመግባት የመጸዳጃ ቤት ንፅህና ጠባቂ ሆኖ አገለገለ፡፡ በብርጭቆ አጣቢነት ከዛም ወደ ድራፍት ቀጂነት ባሬስታ እና ባርማንነት ተሻግረ፡፡ መቶ ሃያ ብር ይከፈለው የነበረው ጭማሪ ተደርጎለት መቶ አምሳ ብር ተከፋይ በመሆን ለአራት አመታት አገልግሏል፡፡

የኑሮ ውጣ ውረድ ያልታከተው ጥጋቡ ከተቀጣሪነት ወጥቶ ሳይታክተው ብስክሌት ገዝቶ በማከራየት እና ሊስትሮ በመስራት ወደ ሌላ ምዕራፍ ለመሸጋገር ሞከረና ተሳካለት፡፡ ብስክሌት ከማከራየት ጎን ለጎን የተነፈሰ ጎማ የመለጠፍ አገልግሎት በመስጠት የገቢ ምንጩን አሰፋ፡፡

እየሰራ ባጠራቀመው ገንዘብ በአምስት ሺህ አምስት መቶ ብር ሞተር ሳይክል የመግዛት ዕድል አገኘ፡፡ የገዛውን ሞተር ሳይክል የጥገና እውቀት ለመቅሰም ሲል ፈታታት፡፡ ፈታቶ ሙያ ተማረባት። በተደጋጋሚ ፈታቶ የመግጠም ሙከራውን መቻሉን አራት ሺህ ብር ከስሮ ሞተሯን አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ሸጣት። አጋጣሚ በህይወቱ ትልቅ አጋጣሚ በመሆኑ አይረሳውም ፡፡

ወጣት ጥጋቡ በራሱ አተያይ ስኬትን ሲገልፅ፡-

ስኬት ላይ የሚደርሰው ሰዎች ዓላማቸውን ቀድመው መረዳት ሲችሉ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በአንድ ስኬታማ ለመሆን ከተፈለገ ጥረትን በማስቀጠል እና የወደቅንበት ነገር አልያም የጣለንን ነገር መለስ ብለን በመመልከት እንደገና በመስራት መወጣት መቻል ነው›› ይለናል ባለታሪካችን በርካታ የማጣት እና የማግኘት ጊዜያቶችን ያሳለፈ ወጣት በመሆኑ ያሳለፋቸውን የህይወት ውጣ ውረዶች ሲያጫውተን በስሜት ሆኖ በእንባ ጭምር ነበር፡፡

የሊስትሮ ስራን፣ የብስክሌት እና የሞተር ሳይክል ጥገናን እየሰራ ትምህርቱን ጎን ለጎን ከሰባተኛ እስከ አስረኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን በሀዋሳ ከተማ አዳሬ ትምህርት ቤት ነበር የተከታተለው፡፡ በትምህርት ቆይታውም የፍቅር ጓደኛ መመስረት ችሏል፡፡ በሚያገኛት ገንዘብ የቤት ኪራይ እየከፈለ ፣ትምህርቱን እየተማረ ያለማንም እገዛ የመንጃ ፍቃድ ትምህርትም ተከታትሏል፡፡

የመንጃ ፍቃድ ትምህርንቱን ከጨረሰ ቡኋላ ህይወት ደጋፊ እና አጋር ስለምትሻ ትዳር መስርቶ በመኖር ላይ ይገኛል፡፡ የህይወት አጋሩ በብዙ ነገር እንደምትደግፈው እና አብራው እንደምትሰራም ነው ያጫወተን፡፡ ከእለት ወደ ዕለት ለውጥ በማሳየት የሞተር ጥገናው ላይ በማተኮር በሙያው ስድስት አመት ካገለገለ ቡኋላ ብቁ ባለሙያ በመሆኑ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ቻለ። በሂደትም ሰዎች ከሚሰጡት አስተያየት ተነስቶ ሞተር ጥገና ዋንኛ ሙያው እንደሆነ እያረጋገጠ መጣ፡፡

ነገሮች ላይ ተስፋ ባለመቁረጥ ህይወቱን ያስቀጠለው ጥጋቡ፣ ከብዙ ፈተና፣ ውጣ ውረድ እና ትግል በኋላ የሚፈልገውን አይነት ስኬታማ ህይወት የሚመራበት መንገድ የራሱን የሞተር ጥገና ቤት በመክፈት ከራሱ አልፎ ስድስት ሰዎችን በስሩ በመቅጠር በቀን በሁለት መቶ አምሳ ብር ክፍያ በማድረግ ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር የቻለ ወጣት ሆኗል።

የህይወት ተሞክሮውን መነሻ አድርገን፣ ሰዎች ኑሯቸውን ለመቀየር ምን ማድረግ ይገባቸዋል ብለን ላቀረብንለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ፡-

“ትላንትና ዝቅ ብዬ ስራን ሳልንቅ በመስራቴና ዛሬ ላይ ከራሴ አልፌ ለሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር የቻልኩት ስራን ባለመናቅ ነው፡፡ የግል ጥረት ለሰዎች መለወጥ ከፍተኛ አስተዋዕጾ አለው፡፡ በተጨማሪም አስር ብር ቢጠፋ ነገ ሰላሳ ብር አገኛለሁ ብሎ ማሰብ እና መስራት ተገቢ ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ ወደ ኋላ እንጂ ወደፊት አያራምድም”፡፡

በቀጣይ ያቋረጠውን፣ የአውቶ ኢንጂን ትምህርቱን በማስቀጠል የመኪና ጥገና ለመክፈት ዕቅድ እንዳለውም አጫውቶን የስራውን አድማስ በማስፋት ረገድ በማህበር በመደራጀት ፒያሳ 06 ቀበሌ ከጓደኞቹ ጋር አቅንቷል፡፡ ቀበሌው ያለበት ክፍለ ከተማ በማህበር የመስሪያ ቦታ እንዲሰጠው የጠየቀ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም፡፡ በዚህ ረገድ የሚመለከተው አካል በማበረታታት ከጎናቸው እንዲቆሙም ስንል እንጠይቃለን።