አቶ አብዶ አህመድ የቡታጅራ ከተማ ከንቲባ ናቸው። የህይወት ስኬቶቻቸውን ፣ እንዲሁም የከተማዋን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች እያነሳን ቆይታ አድርገናል። እንግዳችን ላቀረብንላቸው ጥያቄዎች በሚሰጧቸው ምላሾች በኩል ቡታጅራ ከተማ ውስጥ እንቆያለን። መልካም ንባብ!
በጌቱ ሻንቆ
“ማንም መብቱን በሳንቲም መግዛት የለበትም”
ንጋት፦ ትውልድና ዕድገቶን እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቶን አስታውሰው ያጫውቱን እስኪ?
አቶ አብዶ አህመድ፦ ተወልጄ ያደግኩት በምስራቅ ጉራጌ ዞን ፣ መሥቃን ወረዳ፣ የተቦን የገጠር ቀበሌ ነው። የተቦን ቀበሌ ወሰጥ ልዩ ስሙ አርጉሜ በተባለ መንደር ነው የተወለድኩት። እንደ አቅሜም ቤተሠቦቼን እያገለገልኩ በስርዓት ነው ያደግኩት። ከሁሉም በላይ ግን ትኩረት አደርግ የነበረው ትምህርቴ ላይ ነበር።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በፊት አውራሪ ፍሰሀ ውልጊቾ መታሰቢያ መስከረም ትምህርት ቤት ነው።
ንጋት፦ እንደጠቀሱልኝ በታሪካዊው ሠው ስም በሚጠራ ትምህርት ቤት ነው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቶን የተከታተሉት። እዚያ ትምህርት ቤት መማር ለርሶ ምን ትርጉም አለው?
አቶ አብዶ አህመድ፦ ፊታውራሪ ፍሰሀ ውልጊቾ፣ ለቡታጅራ ከተማ፣ ለሀገራቸውም ትርጉም ያላቸው ስራዎችን ያከናወኑ ናቸው። በእኒህ ጀግና ሠው ስም በተሰየመ ትምህርት ቤት ውስጥ መማሬ በራሱ ትልቅ ትርጉም አለው። መጀመሪያ ወድጄው የተማርኩበት ትምህርት ቤቴ ነው። በዚህ ላይ በታሪካዊው ሠው ስም የተሠየመ መሆኑ ሲጨመርበት እዚያ ትምህርት ቤት ውስጥ እንኳንም ተማርኩ ያሰኘኛል። እድለኛም ነኝ በእዚያ አካባቢ በመወለዴ።
ንጋት፦ የተወለዱበትና ያደጉበት አካባቢ ብዙ የታሪክ እውነታዎች የተመላለሱበት ነው። በሀገራችን ውስጥ የታወቁ ኢንተርፕሩነሮች የፈለቁበትም አካባቢ ነው። ለምሳሌ ያህል ቀኝ አዝማች ፍሬ ሠንበት። የእንደዚህ አይነት ሰዎችን የሰኬት ታሪክ እየሰሙ ማደግ ሊኖር ይችላል። እንዲህ ያለው ነገር በህይወቶ ውስጥ ምልክት አስቀምጦ ከሆነ?
አቶ አብዶ አህመድ፦ አዎን። ምሳሌ የምታደርጋቸው ሠዎች የስፈልጉሀል። ‘ሞዴል’ የምታደርጋቸው፣ ለሀገራቸው፣ ለአካባቢያቸው ዋልታ የሆኑ ሠዎችን የውጤታማነት ታሪክ እየሠማህና እየተመለከትክ ማደግህ ትልቅ ትርጉም አለው። እነሱ የተግባር ምሳሌዎች ናቸው። የነዚህን ሠዎች የውጤታማነት ታሪክ እየተመለከትክ ማደግህ ትልቅ ወሳኝነት አለው።
እርግጥ ነው፤ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው። ቴክኖሎጂውን ተጠቅመን የነሡን ያህል ስራዎች ባንሰራም እነዚህን ሠዎች ምሳሌ አድርገን ማደጋችን በኔም ህይወት ውስጥ ትልቅ ትርጉም አለው።
ንጋት፦ መልካም። አሁንም ከዚያው አካባቢ ሳንወጣ የማነሳው ጉዳይ አለኝ። እርሶ ከተወለዱበት አካባቢ ዝቅ ብሎ ፣ ቆቶ ተብሎ በሚጠራው ከፍታማ ስፍራ የመጀመሪያው፡- 100 ዓመት ሊሞላት ጥቂት ዓመታት ከቀሯት ቡታጅራ ከተማ ቀድሞ የተቆረቆረ ከተማ እንደነበር እየተነገረ ነው።
አሁን ደግሞ ከተማዋ እየሠፋች ወደእዚህ ታሪካዊ አካባቢ ቀርባለች። ወደ ፊት ለዚህ ታሪካዊ አካባቢ ፣ የታሪኩ ማስታወሻ የሚሆን ምን አይነት የቡታጅራ ክፍለ ከተማ ሊገነባ ይችላል?
አቶ አብዶ አህመድ፦ አብዛኛዎቹና የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች የተመሠረቱት ከፍታማ ቦታዎች ላይ ነው። ያነሳኸው የታሪካዊነት መነሻ እውነት ሊሆን ይችላል። የጠቀስከው ስፍራ በመስቃን ወረዳና በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ድንበር ላይ ነው የሚገኘው። ከተሞች አይስፉ ብንል እንኳ መስፋታቸው አይቀርም።
እናም የተጠቀሰውን አካባቢ በሰነዶች ላይ የተመሠረቱ ጥናቶች አድርጎ፣ አካባቢው የከተማዋ መነሻ ነጥብ ሆኖ ፣ የታሪኩ ማስታወሻ በሚሆን መልኩ፣ ከአካባቢው ህብረተሠብ ጋር በመካከር የሚለማበት ዕድል ይፈጠራል ብዬ አስባለሁ።
ንጋት፦ አብዶ አህመድ በልጅነቱ ምን መሆንን ያስብ ነበር።
አቶ አብዶ አህመድ ፦ አቶ አብዶ በልጅነቱ ጎበዝ፣ የሚከበር መምህር መሆንን ይመኝ ነበር። ሌላ ጊዜ ደግሞ ተምሮ የመንግስት ሠራተኛ መሆንን ያስብ ነበር። የመንግስት ሠራተኛ ሆኖ ህዝብን ማገልገል። እርግጥ ነው በስተመጨረሻ የመንግስት ሠራተኛ የመሆን ህልሜን አሳክቻለሁ።
ንጋት፦ የሁለተኛ ደረጃና የዩንሸርሲቲ ትምህርቶን እናንሳ?
አቶ አብዶ አህመድ፦ የሁለተኛ ደረጃና የመሠናዶ ትምህርቴን የተከታተልኩት ቡታጅራ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። የዩንቨርስቲ ትምህርቴን የተከታተልኩት ሀዋሳ ዩንቨርሲቲ ነው። ከሀዋሳ ዩንቨርሲቲ በ”አፕላይድ ስታትስቲክስ” ተመረቅኩ። ሁለተኛ ዲግሪዬን የሠራሁት “በደቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ” ነው። በከፍተኛ ማዕረግ ነው ያጠናቀቅኩት።
ንጋት፦ ለአንድ የአርሶ አደር ልጅ ወደ እዚህ የስኬት ደረጃ ለመድረስ የሚደረግ ጉዞ ቀላል እንደማይሆን እገምታለሁ። የእናትና የአባቶ ድርሻ ምን ነበር በዚህ ጉዞዎ?
አቶ አብዶ አህመድ፦ እናትና አባትህ ብቻ አይደሉም እንድትማር የሚያደርጉህ። አካባቢህ በሙሉ ላንተ መማር ድርሻ አለው። ስታጠፋ ካየህ “እረፍ! ተስተካከል!”፣ ይልሀል። ደንገጥ ብለህ ትመለሳለህ። “ጎሽ የእንትና ልጅ! ትምህርቱን በደረጃ ይወጣል። አንተ ግን እዚህ ትንዘላዘላለህ!”፣ ብሎ ይተችሀል። አንተ ከትችቱ ለመዳን ትበረታለህ። በነዚህ ምክንያቶች ባንተ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ ቤተሰብም አካባቢም ድርሻ አላቸው። ያኔ የነበረው ዕድገታችን አሁን ለደረስንበት ደረጃ ትልቅ አበርክቶ አለው።
ከዚህ ባሻገር አባትና እናቴ ልጅ እያለሁ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። የመጨረሻ ልጅ ነኝ። በዚህ ምክንያት በታላላቅ ወንድሞቼና እህቶቼ ድጋፎችና እገዛዎች ነው ያደግኩትም የተማርኩትም። ‘ሳልቸገር ‘ ነው እየተማርኩ ያደግኩት። አሁንም እንደ ልጅ ነው የሚመክሩኝ። እንደ ልጅ ነው የሚያስቡልኝ። አንድም ቀን እናት የለኝም ፤ አባት የለኝም ብዬ አስቤ አላውቅም። በዚህ ምክንያት ላመሠግናቸው እወዳለሁ።
ንጋት፦ የመንግስት ስራ ከጀመሩበት አንስቶ አሁን እስካሉበት ድረስ ያለውን ምዕራፍ እንቃኝ ?
አቶ አብዶ አህመድ፦ ከ2002 ዓም ጀምሮ በመንግስት ስራዎች ላይ ነው የቆየሁት። በነባሩ ጉራጌ ዞን 13 ወረዳዎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች ነበሩ። በጊዜው ከዩንቨርስቲዎች ተመርቀን ለወጣን የወረዳዎቹና የከተማ አስተዳደሮቹ ልጆች የስራ ቅጥር የውድድር ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር። እኔም ተወዳድሬ በማለፍ ኮኪር ገደባኖ ወረዳ ተመደብኩ። በወረዳው ፍትህ ፅህፈት ቤት ለአንድ ዓመት አገለገልኩ።
ቀጥሎም በዚያው በነባሩ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤት ውስጥ በመስክ ስራዎች አስተባባሪነት መስራት ጀመርኩ። እዚሁ ተቋም ውስጥ የተለያዩ ስራ ሂደቶች ውስጥ ሰርቻለሁ። የቴክኖሎጂ ስራ ሂደት አስተባባሪ ሆኜ። በኻላም የስነምግባር መከታተያ ስራ ሂደት አስተባባሪ ሆኜ ከሶስት ዓመታት በላይ አገልግያለሁ። አሁንም የታክስ ትምህርት ፣ ቅሬታና አቤቱታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን ሰርቻለሁ። አስከትሎም የዞኑ ቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ሀላፊ በመሆን ሰርቻለሁ። ይህንን ተቋም አንድ ዓመት ካገለገልኩ በኻላ ነው አሁን ወዳለሁበት ሀላፊነት የመጣሁት።
ንጋት፦ እርሶ ወደ ቡታጅራ ከተማ ፣ የከተማዋ ከንቲባ ሆነው ሲመጡ ከመልካም አስተዳደር ጋር፣ ከፍትሀዊ ተጠቃሚነት ፣ እንዲሁም ተያያዥና መሠል ጉዳዮች ዙሪያ ውስብስብ ፈተናዎች ነበሩ ሲባል ሰምቻለሁ። ፈተናዎቹን ለመሻገር የርሶ ያመራርነት ተሳትፎ ምን ድርሻ ነበረው?
አቶ አብዶ አህመድ ፦ ወደ ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የመጣሁት በርካታ ጉዳዮችን ይዤ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ሆኜ ስራ የጀመርኩት የነበሩ ጉድለቶችና ጥንካሬዎችን በመለየት ነው። የመለየቱን ስራዎች ካከናወንን በኻላ ከአመራሩና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያሉትን ጥንካሬዎች እንዴት ነው የምናስቀጥለው? የሚል አጀንዳ አንስተን ወደ መነጋገሩ ገባን። ማንም ቢሄድ ማንም ቢመጣ ግን ተቋም ይቀጥላል።
ጥንካሬዎቹ የአመራሩ፣ የህብረተሰቡ ናቸው። እንዴት ነው እነዚህን ጥንካሬዎቹን እንዴት ነው የምናስቀጥለው ስንል ተነጋገርን። ጉድለቶቹንስ እንዴት ነው ማረም የምንችለው ስንል ተወያየን። ምክንያቱም ጉድለቶቹን እኛም የምንደግም ሆነን መገኘት የለብንም። በዚህም መደበኛ ዕቅዶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው ችግሮቹን መፍታት የሚያስችል የአጭር ጊዜ እቅድ አስቀምጠን ነው ወደ ስራ የገባነው። ክፍተቶቹ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ መፈታት የሚችሉ በመሆናቸው ፣ በአጭር ጊዜ መፈታት ለሚችሉት ነው እቅዱን ያዘጋጀነው።
ቡታጅራ ከተማ ማደግ በሚገባት ደረጃ አይደለም እያደገች ያለችው። ከተማዋ ካሉት ፀጋዎቿ አንፃር ፣ ካሏት የማደግ አቅሞች አኳያ ስትታይ ማደግ ባለባት መጠን አላደገችም። ራሷን ከትናንሽ ከተሞች ጋር ማነፃፀሯ ቀርቶ በሚገባት ልክ ማደግ አለባት የሚል ወኔ ይዘን ነው ወደ ስራ የገባነው።
ከተማዋ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ረገድ ሠፊ ክፍተት የነበረባት ናት። በተለይም ከመሬት ጋር ተያይዞ። ማናለብኝነት ተንሰራፍቶ ነበር።
ንጋት፦ አሁን እየነገሩን ያለው ነገር ግልፅ ሆኖ እንዲታይ አብነቶችን መጥቀስ ብንችል?
አቶ አብዶ አህመድ፦ አንደኛ አሠራርን ተከትሎ በመስራት ረገድ ክፍተት ነበር። በተለይም በማዘጋጃ ቤት አካባቢ። ለምሳሌ ከመሬት ጋር ተያይዞ። ለአንዱ አርሷደር አንድ እጣ ይበቃዋል። ለሌላኛው ደግሞ ሶስት ይገባዋል። አሁንም ለሌላኛው ምንም አይገባውም እየተባለ ነበር ስራዎች የሚሰሩት። ይህም በማዘጋጃ ቤቱ ሁለት ባለሙያዎች ብቻ የሚፈፀምበት አሠራር ነበር የተዘረጋው።
አሰራሩ ግን ይህን አይፈቅድም። መጀመሪያ ጉዳዩ በመሬት ልማት ዘርፍ ታይቶ ፣ ቀጥሎም ለማዘጋጃ ቤቱ ማኔጅመንት ቀርቦና ተወስኖ፣ ከፍ ሲልም ለከተማ ከንቲባ ኮሚቴ ቀርቦና ውይይት ተደርጎበት ከተወሠነ በኻላ ነው ተፈፃሚ የሚደረገው። ውሳኔው ተመልሶ ወደ ማዘጋጃ ቤቱ ከተላከ በኻላ። አሰራሩ የሚፈቅደው ይህንን ነው። ነገር ግን በሁለት ባለሙያዎች ብቻ የሚያልቅበት አካሄድ ነው የነበረው።
በተፈጠሩት ክፍተቶች ምክንያት ያለ አግባብ የባከኑ መሬቶች ነበሩ። ለምሳሌ በአንድ ቀን 56 የይዞታ ካርታዎች ወጪ ተደርገው ነበር። እነዚህን መሬቶች አስመልሰናል።
አርሶ አደር ሳይሆን እንደ አርሶ አደር የሚስተናገድበት ሁኔታ ነበር። አንድ መሬት ላይ ለሶስትና አራት ሠዎች የይዞታ ማረጋገጫዎች ይሰጡ ነበር።
የመሬት ይዞታ ማረጋገጫዎች በቀብድ የሚሰጡበት አሰራርም ነበር። “በቅድሚያ ይህን ያህል ገንዘብ አምጣ። ሳይቱን ስትረከብ ደግሞ ይህን ያህል ትከፍላለህ ” የሚባልበት አሠራር ነበር።
እነዚህን ነገሮች በስሜት ሳይሆን በስክነት ፣ ከማዘጋጃ ቤቱም ከሌሎች ተቋማትም የተውጣጣ ኮሚቴ አቋቁመን የማጣራት ስራዎችን ሰርተናል። ከዚህ በኻላ ነው ወደ ማረሙና ማስተካከሉ ስራ የገባነው። የግድፈቶቹን ተጨባጭነት በማረጋገጥ ፓለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች ተወስደዋል።
ንጋት፦ ከፓለቲካዊና አስተተዳደራዊ እርምጃዎች ባሻገር ምን ምን አይነት ህጋዊ እርምጃዎች ተወሰዱ?
አቶ አብዶ አህመድ፦ ከ14 በላይ ግለሰቦች በእስር ላይ ናቸው። እስሩ የፓለቲካ አመራሩንም ይጨምራል። በዚህ ጉዳይ እጃቸውን ያስገቡት የማዘጋጃ ቤቱ ምክትል ስራ አስኪያጅና የክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጆች ማረሚያ ቤት ነው ያሉት። ይህንኑ ያልተገባ ተግባር ሲፈፅሙ የተገኙ ሶስት መሀንዲሶችም ማረሚያ ናቸው። ሌሎች እጃቸው ያለበት ሁሉ በቁጥጥር ስር ውለው የህግ ተጠያቂነቱን የማረጋገጡ ተግባር በሂደት ላይ ይገኛል። ይህ ተግባር በወራት የሚቆጠር ጊዜ ወስዶብናል። ግን ደግሞ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ግዴታችን ነው።
ሁሉንም የተስተዋሉ የብልሽት አይነቶች ግን አርመናል ማለት አይደለም። ይህ አብነት ነው። የገዘፈውን ጉዳይ ወሰደን ነው ትኩረት ያደረግንበት።
ሌሎቻችንም ከዚህ ትምህርት እንውሰድ እያልን ነው ያለነው። ይህም ለስራችን በጣም አግዞናል ብዬ አስባለሁ። አመራሩም ደጋፊውም ወደ ቀልቡ የተመለሰበት ሁኔታ ነው ያለው። እኛንም ጨምሮ። ነገ ተጠያቂነት እንዳለ አውቄ ነው ስራዬን የምሰራው። ከልጆቼ ተለይቼ እስር ቤት መግባት አልፈልግም። በህዝቡ መተቸት አልፈልግም። በህሊናዬ መወቀስ አልፈልግም።
ዛሬ ላይ ምናልባት ጊዜያዊ ጥቅም ሊያታልለን ይችላል። ዛሬም ጉዳያቸውን በህጋዊ መንገድ ማስፈፀም ሲያቅታቸው “ኢንፎርማል” በሆነ መንገድ ለማስፈፀም የሚመጡ ሰዎች አሉ። አመራር ሲቀያየር የተለያዩ ፍላጎቶችን ይዘው የሚመጡ ሰዎች አሉ።
በዚህ ጉዳይ ከማህበረሰቡ ጋር በሚገባ ተወያይተናል። ማንም መብቱን በሳንቲም መግዛት የለበትም። እስከ ጥግ ድረስ ሄዶ መብቱን ማስከበር ነው ያለበት እንጂ። እላፊ ፍላጎቶችን ማንፀባረቅም የለበትም።
ከተማዋ ተጣማ ማደግ የለባትም። ልቅ አሰራርን ማበረታታት የለብንም። ህብረተሠቡ እላፊ ፍላጎቶችን ገታ በማድረግ ፣ መሰል ነገሮችም ሲከሰቱ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ የሚታገልበት ሁኔታ ነው መፈጠር ያለበት።
በክፍተቶቹ ዙሪያ ጥቆማዎች የመጡት ከህብረተሠቡ ነው። የተበላሹና በቀበሌዎች የተዘጋጁ የመሬት ካርታዎችን በ”ዋትስአፕ” ሲላላኩ የነበሩ አካላት በህብረተሰቡ መካከል ነው ያሉት። ከድርጊቱ ፈፃሚዎች ጋር የግል ችግር የለብንም። ፍላጎታችን የተጣሱ አሰራሮችን ማስተካከል ነው። ህግና አሰራሮችን ተከትለን አገልግሎት መስጠት ግዴታችን ስለሆነ ነው። በዚህ ረገድ የተሻሉ ስራዎች ማከናወን ጀምረናል።
ከተማዋን ቀስፈው የያዙት ህገ ወጥ ግንባታዎች ናቸው። በዚህ ደግሞ የደላሎች እጆች ድርሻቸው ቀላል አይደለም። አርባ ያህል የመሬት ደላሎችን ነው ያሰርነው። አላሰራ ስላሉን ማለት ነው።
በደላሎች የሚመራውን ኢኮኖሚ ለመግታት የተወሰዱ እርምጃዎችን ተከትሎ በከተማዋ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ተፈጥሯል የሚሉ ወገኖች አሉ። በአርባ ደላሎች የሚመራን ኢኮኖሚ “አርቴፍሻል” ነው ብዬ ነው የምወስደው። እነዚህ ደላሎች አርሶ አደሩን መሬትህ ሊወሰድ ነው። መንግስት የሚልህን አትስማ እያሉ ነበር መሬቱን መቶ ሺ ብር ሰጥተው የሚወስዱበት። በቅርብ ጊዜ የማይሸነሸኑ መሬቶችን ሳይቀር ደረሰብህ፣ አለቀልህ እያሉ አደናግረውታል። መንግስት የሚሰጥህን ወረቀት ይዘህ ባዶህን ልትቀር ነው እያሉ አምታተውታል። ቤተሠቡ መሀል ገብተው ጭምር እንዲበተን አድርገውታል። እነዚህ አካላትን ተዉ ብንልም ማረፍ ስላልቻሉ ነው ወደ እርምጃው የገባነው።
ወደ እርምጃው ከገባን በኻላ ህገ ወጥ የቤቶች ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተገትቷል ባንልም የቀነሰበት ሁኔታ ግን አለ። በጣም ቀንሶ ታይቷል። በደላሎች ጫና የሚመራውን ኢኮኖሚ በደንብ መቆጣጠር ተችሏል። ይህንን ስል ግን ህጋዊ ሆኖ የሚሰራውን ደላላ ማለቴ አይደለም። ከተማዋ ለምን ተጣማ አታድግም የሚል አመለካከት ይዘው የሚሠሩትን ነው እንጂ።
አሁንም ከሠዎቹ ጋር ችግር የለብንም። ከተማዋ ተጣማ እንድታድግ ከሚያደርጉት ጋር ነው ችግራችን።
ንጋት፦ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ቅጥልጥል የመብራት ገመዶች ተወሳስበው የተዘረጉበት ሁኔታ ጭምር ይታያል። አብሮም ትክክለኛ ያልሆኑ አሰፋፈሮች ። እንዲህ ያሉት ነገሮች ለአደጋ ጭምር የሚያጋልጡ ይመስላሉ። ባሉበት ሊቀጥሉ ይችላሉ?
አቶ አብዶ አህመድ፦ አይቀጥሉም። ከተማዋ ደረጃዋን ጠብቃ፣ ፕላኗን ተከትላ ነው ማደግ ያለባት። መነሳት ያለበት ቤት ይነሳል። መከፈት ያለበት መንገድ ይከፈታል። በዚህ ወቅት ግን የማህረሰቡ እገዛ ወሳኝ ነው። መንግስት አንድ ጊዜ ተበለሻሽቷልና እዛ ሠፈር ድርሽ አልልም ሊል አይችልም።
በአንፃሩ ጥያቄ የሚያቀርቡ የህብረተሠብ ክፍሎች አሉ። “አቱ” ተብሎ እንደሚጠራው አካባቢዎች ያሉ። አስከሬን ማውጫ መንገድ አጣን ብለው የሚጠይቁ አሉ። እነዚህ አካባቢዎች ላይ ትንሽዬ መሬት ካለች ህገወጥ ግንባታ ተካሂዶባት ትሸጣለች።
ህብረተሠቡ እንዲህ ያለውን ነገር መዋጋት መቻል አለበት። ምክንያቱም ዞሮ የሚጎዳው ራሱን፣ ማህበረሰቡን ነው። አስከሬን ማውጫ አጣሁ ማለትኮ ከባድ ነገር ነው። እንደዚህ ያሉ ጥያቄዎች ወደኛ እየመጡ ነው። እኛም የማስተካከሉን ስራ ጀምረናል። ህብረተሠቡ ኮሚቴ እያዋቀረ፣ በኮሚቴው በኩል ከኛ ጋር እየተገናኘ መከፈት ያለባቸው መንገዶች አቅም በፈቀደ መጠን እንዲከፈቱ፣ ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት እንዲያገኝ እየሠራን ነው።
ይሁንና መሠል ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ መንግስትም ማህበረሰቡም የመከላከል ስራዎች መስራት አለባቸው።
ንጋት፦ ስለከተማዋ መሠረተ ልማቶች እናንሳ?
አቶ አብዶ አህመድ፦ በከተማዋ ውስጥ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሆነው ከሚነሱት ጉዳዮች አንዱ የመንገዶች ተደራሽነት ነው። የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች ችግሮች አሉባቸው የሚሉ ነገሮች ይነሱ ነበር። ኮንዶሚኒየም መኖሪያ መንደር ውስጥ ከ “ሴፍቲ ታንከር” ጋር ተያይዞ የሚነሱ ነገሮች ነበሩ። በዚህ ችግር ምክንያት መኖር አልቻንም የሚሉ አካላት ነበሩ። የውሀ መስመሮች ተደራሽነት ላይ በተመሳሳይ። እነዚህ ጉዳዮች በምክር ቤታችን ጭምር ተነስተዋል።
ለነዚህ ችግሮች ማቃለያ ወደ 141 ሚሊየን ብር በመመደብ 40 ያህል ፕሮጀክቶች በማዘጋጀት ውል ተገብቶ ተፈፃሚዎች ሆነዋል። ከሶስትና አራት ፕሮጀክቶች በስተቀር ውል የገባንባቸውን ፕሮጀክቶች መቶ በመቶ አሳክተናል። በዚህም ከተማዋን ሞዴል ለማድረግ ጥረቶች አድርገናል።
እንደሚታወቀው የ UNDP ድጋፍ በዚህ ዓመት አልነበረም። ድጋፉ በሌላ ምዕራፍ በቀጣይ ዓመት የሚጀምር ነው የሚሆነው። ተቋማዊ በሆነ መንገድ ነበር ድጋፉ ለረጅም ጊዜ ስራ ላይ እየዋለ የቆየው። ሲቋረጥ ደግሞ ቀጣይነቱ ጥያቄ ውስጥ እንዳይወድቅ ብቻ ሳይሆን አጠናክረን መቀጠል አለብን የሚል አቋም በመያዝና 141 ሚሊዮን ብር በመመደብ እንዲንቀሳቀስ አድርገናል። ባለፈው ዓመት ድጋፉም ኖሮ ስራው የተመራው 90 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ነበር።
ንጋት፦ ድጋፉ በሌለበተትም ለስራ ዘርፉ የተመደበው በጀት አድጎ ታይቷል ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ አብዶ አህመድ፦ አንደኛው ምክንያት ስራው ተቋማዊ መሆኑ ነው። ሌላው ጉዳይ አቅማችንን መጠቀም አለብን ብለን በመወሠናችንና የገቢ መጠናችንን ለማሳደግ መስራታችን ነው። ሌላ የተለየ የፈጠርነው ነገር የለም። የገቢ አቅም የማሳደግ እቅዳችንን ለጥጠን ነበር ያዘጋጀነው። በ2015 ዓም የተሰበሰበው የገቢ መጠን 303 ሚሊዮን ብር ነበር። ከአምናው 78% ብልጫ ያለው ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ በመግባት 531 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጫ ፕሮጀክቶች ማከናወኛ አቅም ማግኘት ችለናል።
ከተማችን ለ24 ሠዓታት ውሃ የሚፈስባት ከተማ የሚለውን ስሟን አንድ ጥልቅ ጉድጓድ የማልማቱን ተግባር አጠንክሮ በመያዝ አድሰናል።
ሌላው ከመሠረተ ልማት ግንባታዎች ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጉዳይ የከተማዋ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ስራዎች ናቸው። በምዕራፍ ሁለት መጠናቀቅ የሚገባቸው የአስፓልት መንገዶች በጣም ተጓተው ነበር። ከኤም ,ኤስ ወዶ መስመር ያለውን የተጓተተ ግንባታ 100 ሚሊዮን ብር በመመደብ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገበት አመት ነው።
በሴራና ቅድስተ ማርያም መስጂድ ጨርቃጨርቅ ዝዋይ መንገድ የሚያገናኘውን ቀሪ የ2 ነጥብ 18 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ድርጅትና አማካሪው ጋር በ334 ሚሊዮን ብር የውል ሰነድ ተፈራርመናል። በካፍ ሆቴል መስቃን ወረዳ ፓሊስ ጣቢያ ያለው መንገድም የሚገነባ ይሆናል።
ንጋት፦ የትምህርት ስራዎችን በተመለከተ?
አቶ አብዶ አህመድ፦ የትምህርት ስራዎቻችን ስላሉበት ሁኔታ አዳራሽ ውስጥ ተቀምጠን ግምገማ ከማድረጋችን በፊት ዞረን ትምህርት ቤቶቻችን ያሉበትን ሁኔታዎች ነው የተመለክትነው። ቡታጅራ ከተማን የማይመጥኑ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን አስተውለናል። ህብረተሠቡን አስተባብረን ፣ እኛም ጨከን ብለን ማስተካከያ ስራዎች እየሠራን ነው።
ሌላው ቡታጅራ ከተማ አዳሪ ትምህርት ቤት ያስፈልጋታል ብለን ሀብት የማሰባሰብ ስራ ጀምረናል።
ንጋት፦ ከአዳሪ ትምህርት ቤቱ መገንባት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ውዥንብሮች አሉ።
አቶ አብዶ አህመድ፦ ምን ዓይነት?
ንጋት፦ ትምህርት ቤቱ የሚገነባው ቡታጅራ ከተማ ውስጥ አይደለም የሚል።
አቶ አብዶ አህመድ፦ የ”ፌስ ቡከሮች” ፓለቲካ ነው። የሚገነባበትን ቦታ ለይተን አዘጋጅተናል። ማህበረሰባችንን አሳትፈን እውን እናደርገዋለን ብለን ነው የጀመርነው።
ንጋት ፦ በጤና ዙሪያስ አቶ አብዶ?
አቶ አብዶ አህመድ፦ ቡታጅራ ከተማ ውስጥ አንድ ጤና ጣቢያ ነው ያለው። የቆየ ነው። የጤና ጣቢያው የሠው ሀይልም ክፍተት ያለበት ነው። ምን ያህል ህዝብ እያስተናገደ ነው ? ብለን ስንጠይቅ ደግሞ ከ100ሺ በላይ ህዝብ እያስተናገደ ነው። የማስተተናገድ አቅሙ ግን 25 ሺ ነው።
በኛ ደረጃ የዚህን ጤና ጣቢያ ደረጃ ማሳደግ ወይስ አዲስ መገንባት? በሚል ተወያይተናል። ማሳደጉ አንድ ተጨማሪ ጤና ጣቢያ ያስፈልጋታል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል። ቦታ ተመርጦ ሀብት የማሰባሰብ ስራ ጀምረናል። ለሚገነባው ጤና ጣቢያ ሙሉ የህክምና ቁሳቁስ እናሟላለን ብለው ቃል የገቡልን አካላት አሉን።
ነባሩም ጤና ጣቢያ መዘመን አለበት።
ሌላው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጀመሪያው የኦቲዝም ማዕከል ቡታጅራ ላይ መገንባት አለበት ብለን በሰራነው የማግባባት ተግባር ከሊያና ዲቦራ ፋውንዴሽኖች ጋር እንዲገነባ የውል ሰነድ ፈርመናል።
ንጋት፦ ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሠግናለሁ።
አቶ አብዶ አህመድ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው