“ሙሉ አፍሪካ ነጻ እስካልወጣ ድረስ የእኛ ነጻነት ትርጉም የለውም” – ዶ/ር ክዋሜ ንኩሩማ

በኢያሱ ታዴዎስ

…ክፍል ሁለት

ከአውሮፓዊያኑ 1780 እስከ 1849 የኢንደስትሪ አብዮት በአውሮፓ እንደ ሰደድ እሳት የተቀጣጠለበት ጊዜ ነበር፡፡ በታላቋ ብሪታኒያ የፈነዳው አብዮት በምዕራብ አውሮፓ በተለይም በቤልጂየም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ተከተለ፡፡ ሀገራት ከተሞቻቸውን በዚህ አብዮት ውስጥ ማሳደግ ጀመሩ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የሀገራት ምጣኔ ሃብት እና የሕዝብ ብዛት ከተጠበቀው በላይ አሻቀበ፡፡

ይህ የኢንደስትሪ አብዮት ለአውሮፓዊያን ሌላ የሽግግር ምዕራፍ አመጣ፡፡ (ኋላ ላይ አፍሪካን ለመሰለች አህጉር ግን ዳፋ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡) የኢንዱስትሪው አብዮት ያቅለበለባቸው አውሮፓዊያኑ የጥሬ ዕቃ እጥረት ገጠማቸው፡፡ ከኢንደስትሪው ጋር አብሮ የማደጉ ፍላጎቱ፣ ከወዲያ የምጣኔ ሃብቱ መወጣጠሩ አማራጭ እንዲፈልጉ አስገደዳቸው፡፡

በተለይም ከ1841 ጀምሮ የአውሮፓ ነጋዴዎች በንግድ ሰበብ አብዝተው የአፍሪካን ምድር ይረግጡ ነበር፡፡ ይህም የንግድ ትስስር ቀስ በቀስ አውሮፓዊያኑን እየሳበ መጣ፡፡ በወቅቱ አፍሪካ የርካሽና መጠነሰፊ ጥሬ ዕቃዎች ባለቤት ነበረች፡፡ በዚያ ላይ እምብዛም የንግድ ውድድር አልነበረባትም፡፡

በሌላ መልኩ የዝሆን ጥርስ፣ ጎማና የፕላስቲክ ውጤቶች፣ የፓልም ዘይት፣ ካካዎ፣ ቡና፣ ሻይ አልማዝ፣ ወርቅ፣ ቆርቆሮ፣ ዩራኒየም እና ሌሎች ሃብቶች እንደ ልብ የሚገኙባት መሆኗ አውሮፓዊያኑ ሳይተኙ እንዲያድሩ አደረጋቸው፡፡

ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ አውሮፓዊያኑ የራሳቸውን ምድር ትተው ገና ያልተነካና የካበተ ሃብት ያላትን አፍሪካ ሲያዩ ምራቃቸውን በአምሮት የዋጡት፡፡

አውሮፓዊያኑ ምኞታቸውን በተሰመረው የንግድ መስመር ማሳካት ይችሉ ነበር፡፡ ከአፍሪካ ጋር ጥሩና ጤናማ የንግድ ትስስር ስለነበራቸው፡፡ ይሁን እንጂ የሌሎች ላብና ደም የሚጥማቸው አውሮፓዊያኑ ዓይናቸውን ከአፍሪካ ሊነቅሉ አልቻሉም፡፡ ይህም ስውር አጀንዳ በታላቅ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተገለጠ። አፍሪካን መቀራመት በሚል ስልት ተኮር ብዝበዛ፡፡

የዚህ ሃሳብ ጥንስስ ከ1884 እስከ 1885 በጀርመኗ በርሊን ከተማ በተካሄደው ጉባኤ በአሜሪካ እና በሌሎች 13 የአውሮፓ ሀገራት ተዶለተ፡፡ በጉባኤውም በአዲሱ የኢምፔሪያሊዝም አቀንቃኝነት ወይም ደግሞ ቅኝ ግዛት አፍሪካን እንደ ዶሮ ብልት በታትኖ ለመግዛት ከስምምነት ተደረሰ፡፡

ከዚያም ታላቋ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ስፔን እና ፖርቱጋል ያላቸውን የጦር ኃይል ሸክፈው አፍሪካዊያኑን ተከፋፍለው ሊገዙ ወደ አህጉሪቱ ወረዱ፡፡ የራሷን አንጡራ ሃብት ተጠቅማ ማደግ የምትችለው አፍሪካም በቅኝ ገዢዎቿ እግር ስር ወደቀች፡፡

የአፍሪካዊያኑን ላብ እና ደም ግብር ያስከፈለው አስከፊው ጭቆና ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ እንዲሁም ከምስራቅ እስከ ምዕራብ አህጉሪቱን አጥለቀለቃት፡፡ በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ 10 በመቶ የነበረው የአውሮፓዊያኑ ቁጥጥር (ቅኝ ግዛት)፣ በ1914 90 በመቶ አፍሪካን ሸፍኖ ነበር፡፡

በእርግጥ አፍሪካን በቅኝ ግዛት የመደቆስ ሃሳብ ገቢራዊ መሆን የጀመረው ከበርሊኑ ጉባኤ አስቀድሞ በ1870ዎቹ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚሁ ወቅት 10 በመቶ የሚሆነው የአህጉሪቱ ክፍል በምዕራባዊያን ቁጥጥር ስር ነበር፡፡

ከበርሊኑ ጉባኤ በኋላ ግን የሚቆጣጠሯቸውን ሀገራት ቁጥር እያበዙ ሙሉ አፍሪካን እስከመሸፈን ደረሱ፡፡ ከ1885 እስከ 1914 ባሉት ጊዜያት ውስጥ ታላቋ ብሪታኒያ 30 በመቶ፣ ፈረንሳይ 15 በመቶ፣ ፖርቱጋል 11 በመቶ፣ ጀርመን 9 በመቶ፣ ቤልጂየም 7 በመቶ፣ እንዲሁም ጣሊያን 1 በመቶ የሚሆነውን የአፍሪካ ሕዝብ በቁጥጥራቸው ስር አድርገው ነበር፡፡

በዚህ ጊዜ ከቅኝ ግዛቱ ያመለጡት ኢትዮጵያ፣ ላይቤሪያ እና ከፊል ሊቢያ ብቻ ነበሩ፡፡ ላይቤሪያ አስቀድማ ከ1821 ጀምሮ በአሜሪካ ቅኝ ግዛት ስር የነበረች ሲሆን በ1847 ነጻነቷን አውጃ የአውሮፓዊያኑ የቅኝ ግዛት መዳፍ ሳይዳስሳት ቀረ፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ ከአንድም ሁለት ጊዜ በጣሊያን የተደረገባትን ወረራ መክታ አፍሪካዊያን በነጮች ላይ የበላይነትን መቀዳጀት እንደሚችሉ ምሳሌ በመሆን በነጻነት መንቀሳቀስ ቻለች፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በጭቆና የተቀፈደዱ አፍሪካዊያን ሀገራት ራሳቸው ታግለው ነጻነታቸውን መቀዳጀት እንዲችሉ በር ከፈተ፡፡

በተለይም ከኢትዮጵያ አልገዛም ባይነት የተማሩት ሀገራት የፓን አፍሪካኒዝም ዋነኛ አቀንቃኝ በመሆን ዘመናዊውን የምዕራባዊያን ጦር ለመመከት አንድ በአንድ ተሰናዱ፡፡ የነጻነት ጉዞ ያኔ ተጀመረ፡፡

የገዛ ከርሰ ምድራቸው ያጎናጸፋቸውን የማዕድን ገጸበረከት እንዳይጠቀሙ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ራሳቸው አውጥተው የሚበዘብዟቸውን ቅኝ ገዢዎች በጽኑ በመቃወም ለነጻነታቸው ታግለው ውጤታማ ከሆኑ ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚዋ ናት፡፡ ደቡብ አፍሪካ “ጭቆናችሁ በአፍንጫዬ ይውጣ” በማለት ብሪታኒያ ላይ ያደረገችው መራር ትግል ፍሬ አፍርቶ ነጻነቷን አወጀች። ከዚያ በኋላ ሀገሪቱ እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ድረስ በነጮች የበላይነትና በአፓርታይድ ስርዓት በብዙ ተፈትናለችም፡፡

ከዚያም ሰሜን አፍሪካዊቷ ግብጽም በተመሳሳይ ብሪታኒያ ላይ አምጻ ቅኝ ግዛት አሻፈረኝ በማለት 1952 ከጭቆና የጸዳ አየር መተንፈስ ጀመረች፡፡ ነጻነቱ እየተፋፋመ ሀገራትን ማዳረስ ጀመረ፡፡

በ1956 ብቻ ሱዳን፣ ሞሮኮ እና ቱኒዚያ እንደየቅደም ተከተላቸው ቅኝ ገዢዎቻቸውን አሳፍረው ነጻነታቸውን አወጁ፡፡ ይሄኔ ነበር ጋና በድንቅ ልጇ ዶ/ር ክዋሜ ንኩርማ የነጻነት አቀንቃኝነት ታግዛ፣ ለሌሎችም ሀገሮች አርዓያ ሊሆን በሚችል መልኩ ሊቀለበስ የማይችል ትግል አድርጋ ታላቋን ብሪታኒያ ከምድሯ በማስወገድ በ1957 ነጻነቷን የተቀዳጀችው፡፡

ጋናን ወደ ነጻነት የመሩት ንኩሩማ በነጻነት ቀናቸው፣ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የጸረ ቅኝ ግዛት ትግላቸውን እንዲያፋፍሙ በሚገፋፋው ንግግራቸው፡-

“መላው አፍሪካ ነጻ እስካልወጣ ድረስ የእኛ ነጻነት ለብቻው ትርጉም የለውም” ሲሉ ቆፍጠን ያለ መልዕክት ሲያስተላልፉ ተደመጡ፡፡

ይህ መልዕክታቸው ተራ አባባል አልነበረም፡፡ ይልቅስ በየሀገራቸው ቅኝ ግዛት ላይ ቂም የቋጠሩ እንደ ፓትሪስ ሉሙምባ፣ ጁሊየስ ኔሬሬ እና አህመድ ሴኮቱሬ ያሉ ጉምቱ ታጋዮችን ወደ ትግሉ ሜዳ አመጣ። እንዲያውም ጋና የወቅቱ ጸረ ቅኝ ግዛት ተምሳሌት ተደርጋ በማመሳከሪያነት መወሳት ጀመረች፡፡

የተከፈተውን በር በመጠቀም፣ ጊኒያዊው አህመድ ሴኮቱሬ ጊዜ ሳይፈጅ ሀገሩን ነጻ ለማውጣት ፍልሚያ ማድረጉን ተያያዘ። ትግሉም ሳያሳፍረው ምድራቸውን የበዘበዘችውን ፈረንሳይ በኃይል በመፈንገል ጥቅምት 2 /1958 ነጻይቱን የጊኒ ምድር ተረከበ፡፡

በመላው አፍሪካ በቀጠለው የጸረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ፣ በ1960 ብቻ 17 የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን አወጁ፡፡

ከዚያም በ1961 3፣ በ1962 4 ሀገራት እያለ የቀጠለው የነጻነት ጉዞ በ1980 ዚምባቡዌ ከብሪታኒያ በተጎናጸፈችው ነጻነት የቅኝ ግዛት መንበር ከአፍሪካ አህጉር ላይ ዳግመኛ ላይከሰት ተገረሰሰ፡፡

… ይቀጥላል