አዲሱ የፌደራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ

አዲሱ የፌደራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ

 በደረሰ አስፋው

ማሻሻያ የተደረገበት የፌደራል መንግስት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ዝርዝር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ነባሩን የፌደራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ለመተካት የተዘጋጀ ነው። ነባሩን አዋጅ ማሻሻል ያስፈለገበት ዋንኛው ምክንያት የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ፣ ብቃትና ስነ ምግባር የተላበሰ ፐብሊክ ሰርቪስ እንዲፈጠር ለማስቻል የሚለው ይገኝበታል፡፡

ቀደም ሲል በ2010 ዓ.ም ተሻሽሎ ወደ ስራ የገባውና ባለ 106 አንቀጽ የፌደራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ለስድስት ዓመታት አገልግሎ ነበር፡፡ 160 አንቀጾችና 17 ክፍሎች የያዘው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ አሁን በስራ ላይ ካለው አዋጅ አንጻር ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ እና ከዚህ ቀደም በሌላ አዋጅ ይሸፈኑ የነበሩ ጉዳዮችን ሁሉ ያካተተ ነው ተብሏል። የመንግሥትን የመፈጸም ብቃት ለማጎልበትና የዜጎችን ፍላጎት የሚያረካ የመንግሥት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የሕግ ድንጋጌዎች የተካተቱበት እንደሆነም ተገለጿል፡፡

አዲስ የሠራተኞች ድልድል ሲከናውን በመስፈርትነት የተቀመጡ የምዘና እና ሕብረ ብሔራዊነት እና አካታችነት ጉዳይም በረቂቁ ተካትተዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብዝሃነት እና አካታችነትን ያገናዘበ የመንግሥት ሠራተኞች ስብጥርን ከግምት ውስጥ ያስገባ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ እንደሆነም ተመላክቶ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

የአዋጁን ማብራሪያ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንደገለጹት፤ ህብረ ብሄራዊነት፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የጾታ ተዋጽኦና የመሳሰሉትን ብዝሃነትና አካታችነትን ያገናዘበ የመንግሥት አስተዳደርና ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቁ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

አዲሱ አዋጅ ሲዘጋጅ ለማሳካት ከታቀዱ ዓላማዎች ውስጥ አንዱ “በመንግሥት መስሪያ ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማስፈፀም ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማግኘት እና በሥራ ላይ ያሉትንም ለማቆየት” የሚለው አንዱ እንደሆነ በረቂቁ መግቢያ ላይ ተጠቅሷል።

ስለዚህ የመንግስት ሠራተኞች የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ሥርዓትን መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነም የረቂቁ ክፍል ያስረዳል። በስራ ላይ ባለው የፌደራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ላይም የተደነገገው የስራ አፈጻጸም ምዘና በረቂቅ አዋጁ ላይ የጊዜ ገደብ ተቀምጦለታል። በረቂቅ አዋጁ መሰረት ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የሰራተኞቹን “የብቃት ክፍተት” ለመለየት እና ለሰራተኞቹ “የብቃት ዳሰሳ እንዲደረግ” የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎበታል።

መስሪያ ቤቶች ለሥራ ብቁ የሆነን ሠራተኛ በብቃት መመዘኛ መስፈርቶቹ አማካይነት የማረጋገጥ ስራ እንደሚያከናውኑ የሚገልጸው ረቂቁ፤ የመንግስት ተቋማቱ በስራ ላይ የሚመድቡት “በብቃት ምዘናው ዝቅተኛ ማለፊያ ውጤት ያገኘ ሠራተኛን” እንደሚሆን አስፍሯል። የሥራ ብቃት ክፍተት ያለባቸው ሰራተኞች አጭር ሥራ ተኮር ወይም ሞጅላር ስልጠና ወይም በመደበኛ ብቃት ማሟያ ረጅም ጊዜ ትምህርት እንዲያገኙ እንደሚደረግም በረቂቁ አዋጅ ላይ ተጠቅሷል።

“ክፍተት” የታየባቸው ሰራተኞች እነዚህን ስልጠናዎች ከወሰዱ በኋላ የብቃት ምዘና እንደሚወስዱ በረቂቁ ላይ የሰፈረ ሲሆን መስሪያ ቤቶችም ከሥልጠናው በኋላ በብቃት ምዘናው አነስተኛ ማለፊያ ውጤት ያገኘውን ሠራተኛ በሥራ ላይ እንደሚመድቡ አስቀምጧል።

ረቂቅ አዋጁ፤ የብቃት ክፍተት ማሟያ ሥልጠና ተሰጥቶት በስድስት ወር ለሁለት ጊዜ የብቃት ምዘና አነስተኛ የማለፊያ ውጤት ያላገኘ ሠራተኛ ይህ ረቂቅ አዋጁ ባሰፈረው መሰረት መብቱ ተጠብቆ አገልግሎትን እንደሚያቋርጥ ፈተናውን ያላለፉ ሰራተኞች እጣ ፋንታ ይገልጻል።

መስሪያ ቤቶች በሚያከናውኑት የብቃት ምዘና ውጤት መሰረትም በሥራ ላይ ለመመደብ ፍላጎት የሌለው ነባር ሰራተኛን የማሰናበት ውሳኔ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተቀምጧል። በዚህ አይነት የሚሰናበት ነባር የመንግስት ሰራተኛ ጡረታ ለመውጣት እድሜው ያልደረሰ ከሆነ የሁለት ዓመት የተጣራ ደመወዙ “በአንድ ጊዜ” እንደሚከፈለው ረቂቅ አዋጁ ያስረዳል። የሚሰናበተው ሰራተኛ ከመስሪያ ቤቱ የሚያገኘው ይህ ክፍያ ከ12 ሺህ ብር ማነስ እንደሌለበትም ተመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በስራ ላይ ባለው አዋጅ ሰራተኛን የመቅጠር፣ ማስታወቂያ የማውጣት፣ የመመልመል እና የመምረጥ ኃላፊነትም በረቂቅ አዋጁ በግልጽ ሰፍሯል። በረቂቁ መሰረት ይህ ኃላፊነት የሚሰጠው እንደ አዲስ በሚቋቋመው “የኢትዮጵያ የሥራ ብቃትና አመራር ኢንስቲትዩት” ነው።

በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ተቋቁሞ እስካሁን በስራ ላይ ያለውን “የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት” የሚተካው አዲሱ ተቋም፤ በዚህ ረቂቅ በተለይ በመንግስት ሰራተኞች ቅጥር ላይ ወሳኝ ሚና ተሰጥቶታል። በረቂቅ አዋጁ መሰረት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ክፍት የስራ መደብ ሲኖራቸው የሚያስታውቁት ለአዲሱ የኢትዮጵያ የሥራ ብቃትና አመራር ኢንስቲትዩት ነው።

ኢንስቲትዩቱም፤ ማስታወቂያ በማውጣት አዲስ አመልካች እና ነባር የመንግሥት ሠራተኛ እንዲመዘገብ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ኢንስቲትዩቱ ከተመዘገቡ ስራ ፈላጊዎች መካከል አብላጫ ውጤት ያመጡትን ከቅጥር በፊት የቴክኒካል እና የባህርያዊ ብቃት ሥልጠና እንደሚሰጥ በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

ከዚህ ስልጠና በኋላ ስራ ፈላጊው ግለሰብ “በመንግስት መስሪያ ቤት ለመቀጠር በኢንስቲትዩቱ የሚሰጠውን የቴክኒካል እና የባህርያዊ ብቃት ምዘና አነስተኛ የማለፊያ ውጤት ማግኘት አለበት” ሲል ረቂቅ አዋጁ ቀጣዩን የቅጥር ሂደት ያስረዳል። ይህንን ውጤት ያስመዘገቡ ሰልጣኞች የኢንስቲትዩቱን የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንደሚያገኙ ያሰፈረው ረቂቅ፤ ይህ የምስክር ወረቀት የሌለው ግለሰብ “በመንግስት መስሪያ ቤት ለመቀጠር አይችልም” ሲል ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ያስቀምጣል።

“የነባር ሠራተኛ ወይም የዝግጁነት ሰልጣኝ የሥራ ቅጥር አመልካች ተፈላጊ ችሎታ ማሟላታቸውን እና የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ እና በማወዳደር ኢንስቲትዩቱ ቅጥር መፈጸም አለበት” ሲል ቅጥሩን መስሪያ ቤቶቹ እንዳማይፈጽሙ ይጠቁማል። ረቂቁ እንደሚያስረዳው፤ በዚህ መልኩ የተቀጠረ የመንግስት ሰራተኛ ለስድስት ወራት በሙከራ ጊዜ ላይ የሚቆይ ሲሆን ይህ ጊዜ ሲሞላ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤቱ ከመካከለኛ በታች ሆኖ ከተገኘ የሙከራ ጊዜው ለተጨማሪ ሦስት ወር ሊራዘም ይችላል።

ረቂቁ፤ “በተራዘመው የሙከራ ጊዜ ውስጥ ሠራተኛው መካከለኛ ወይም ከዚያ በላይ የተጠቃለለ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤት ካላገኘ ከሥራ ይሰናበታል” ሲል አዲስ ሰራተኞች በቅጥር ለመቀጠል የሚያስፈልጋቸው ማለፊያ እንደ ነባር ሰራተኞች አነስተኛ ማለፊያ ውጤት አለመሆኑን ይጠቁማል።

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ከሚያስተዋውቃቸው ለውጦች ውስጥ አንዱ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ በምን ያህል ጊዜ እንደሚደረግ ማስቀመጡ ነው። በስራ ላይ ያለው አዋጅ የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ስኬል “የመንግስትን የፋይናንስ አቅም፣ የህዝቡን አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ፣ የዋጋ ደረጃዎች እና አግባብነት ያላቸውን ሌሎች ሁኔታዎች ባገናዘበ መንገድ” እየተጠና እንደሚወሰን ይደነግጋል።

ይሁንና አዋጁ በየጊዜው እየተጠና የሚወሰን ይሆናል፡፡ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የደመወዝ ስኬል ተጠንቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ከመደንገግ ውጪ ይህ ጥናት በምን ያህል ጊዜ እንደሚደረግ አያስቀምጥም። አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በአንጻሩ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሥራ ደረጃ መነሻ ዝቅተኛ ደመወዝ እና ከፍተኛ ደመወዝ ጣሪያ በየአራት አመቱ አጥንቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ እንደሚያስወስን እንዲሁም አፈጻጸሙን እንደሚቆጣጠር ያስቀምጣል።

ኮሚሽኑ የሚያደርገው የአበል ማስተካከያም በተመሳሳይ የጊዜ ገደብ ተቀምጦለታል። በረቂቅ አዋጁ፤ “የመንግስት ሠራተኛ ወጪን መሸፈን የሚያስችል ልዩ ልዩ የአበል አይነቶች እና የቀን ውሎ አበል ማስተካከያ በየሁለት አመት ኮሚሽኑ ይወስናል” ሲል በየስንት ጊዜው ማስተካከያ እንደሚደረግ ይወስናል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የደመወዝ ስኬልን ለማስተካከል በየአራት ዓመቱ የሚያደርገውን ጥናት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከማቅረቡ አስቀድሞ ማረጋገጫ የመስጠት ኃላፊነት ያለው አዲስ ቦርድም በረቂቅ አዋጁ ተዋውቋል። “የሜሪት እና የደመወዝ ቦርድ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ቦርድ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት የሚመራ ይሆናል። ቦርዱ ሰብሳቢውን ጨምሮ ስምንት አባላት ያሉት ሲሆን የፕላን እና ልማት እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትሮች አባል እንደሚሆኑ ተዘርዝሯል።

ከቦርዱ ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ፤ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ስኬል ማስተካከያ፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ የክፍያና ጥቅማ ጥቅም እንዲሁም ማትጊያ ወይም ማበረታቻ ጥናት ተጠቃሽ ሲሆኑ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበትን የኮሚሽኑን ውሳኔ ሀሳብም ያረጋግጣል።

የመንግስት ሰራተኞች ከተሰማሩበት ሙያ አንጻር መክፈል ያለባቸውን ተስማሚ፣ ተመጣጣኝ ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅምን የሚመለከተው የኮሚሽኑ የውሳኔ ሀሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በቦርዱ አማካኝነት እንደሚቀርብም ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። በአፈጻጸም ግንባር ቀደም የሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና የመንግስት ሠራተኞች የሚሸለሙበትን “የአመታዊ አገልጋይነት ቀን ሽልማት ሥርዓት” መዘርጋትም ለቦርዱ ከተሰጣቸው ኃላፊነቶች መካከል ነው።