“በሕይወቴ አስገራሚ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ” – አቶ ታምሩ ናሳ

“በሕይወቴ አስገራሚ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ” – አቶ ታምሩ ናሳ

በአስፋው አማረ

ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የምናልፍባቸው በርካታ ውጣ ውረዶች ይኖራሉ፡፡ እነዚያን ውጣ ውረዶች ፈታኝ በመሆናቸው ትዕግስትና ጽናትን ይጠይቃሉ፡፡ አለዚያ ያሰቡበት ዓላማ መድረስ አይቻልም፡፡

የዛሬው ባለታሪካችንም የገጠሙትን ፈተናዎች በትዕግስትና በጽናት በማለፍ የተሻለ ደረጃ መድረስ የቻለ ነው፡፡ አቶ ታምሩ ናሳ ይባላል፡፡ የተወለደው በጋሞ ዞን ቦረዳ ከተማ ነው፡፡

እንደማንኛውም የአካባቢው ልጅ ለቤተሰቡ ከብቶችን በማገድና ድጋፍ በማድረግ አድጓል፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ ዳና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በመቀላቀል ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡

በመቀጠል ከቦረዳ ወደ ወላይታ ሶዶ በማቅናት ትምህርቱን ለመከታተል ወሰነ፡፡ በዚህ ጊዜ ከቤተሰቦቹ የሚሰጠው ድጋፍ ዝቅተኛ በመሆኑ ሥራ እየሰራ ትምህርቱን ለመከታተልም አሰበ፡፡ ትምህርቱን እየተማረ መስራት የሚችለው የሊስትሮ ሥራ በመስራት እንደሆነ ተገነዘበ፡፡

ጫማ በማሳመር የሚያገኘውን ገንዘብ ለደንብ ልብስ፣ ለቀለብ፣ ለግል ንህጽና መጠበቂያና ለሌሎች አስፈላጊ ነገሮች እያዋለ በግማሽ ሰዓት እየሰራ ግማሽ ሰዓት ደግሞ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ፡፡ 7ኛ እና 8ኛ ክፍልን ደግሞ በጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ የኋላ ኋላ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ትምህርቱንም ተምሮ ጨርሷል፡፡

12ኛ ክፍል ከጨረስክ በኋላ ቀጣይ ህይወት እንዴት ነበር? ብለን ላነሳንለት ጥያቄ ሲመልስ፦ “12ኛ ክፍል ከጨረስኩ በኋላ ሐዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅን ተቀላቀልኩ፡፡ በዚህ ደግሞ ለሶስት ዓመታት ትምህርቴን በመከታተል በስፖርት ሳይንስ በዲፕሎማ ፕሮግራም ተመርቄያለሁ፡፡

“ከተመረቅኩ በኋላ እጣ ሳወጣ በሐዋሳ ታቦር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመደብኩ፡፡ በማስተማር ላይ እያለሁ በዲላ ዩኒቨርስቲ ዲግሪዬን በመከታተል በስፖርት ሳይንስ ተመረቅኩኝ፡፡ በውስጤ አዳዲስ ነገሮችን መፈለግና ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ነበረኝ፡፡ ይህን ተከትሎ ወደ ሀዋሳ ፋርማ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመግባት በህብረተሰብ ጤና ሳይንስ (ጤና መኮንነት) ትምህርት ክፍል በመከታተል በሁለተኛ ድግሪ ተመርቄያለሁ፡፡

“በጤና መኮንንነት እንደ ተመረቅኩኝ ከመምህርነት የሙያ መስመር በመቀየር ወደ ሐዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ ተዛወርኩኝ፡፡ በዚህም ደግሞ በአላሙራ እና ጥልቴ ጤና ጣቢያዎች በጤና መኮንነት አገልግያለሁ፡፡

“ሁልጊዜ እራሴን ማብቃትና አዳዲስ ነገሮችን ማወቅ በጣም ያስደስተኛል። ከዚህም የተነሳ ሌላ ሁለተኛ ድግሬዬን (2ኛ ማስተርስ) በዲላ ዩኒቨርስቲ በስፖርት ጤናና አካል ብቃት ስፔሻላይዝ በማድረግ ተመርቅያለሁ” ሲል ትምህርቱን ያሻሻለበትን ሂደት ተናግሯል፡፡

ቀጥሎ ከሀዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ በመልቀቅ በቀድሞ ደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መስራት ጀመረ፡፡ የስፖርት ህክምናና የፀረ አበረታች ቅመሞች ክፍል ኃላፊ በመሆን መስራት ችሏል፡፡ በዚያም በመስራት ላይ እያለ ለበርካታ ጊዜያቶች የተለያዩ አጫጭር የስፖርት ህክምና ስልጠናዎችን በመውሰድ በዘርፉ በስፋት ማገልገል ችሏል፡፡

እነዚህ የህክምና ስልጠናዎቹን በስፔን፣ ቻይና፣ ሞሮኮ እና በተለያዩ ሀገራት በመውስድ የስፖርት ህክምና እውቀትን አዳብሯል፡፡ እንደዚሁም ኢንተርናሽናል ኦሎምፒክ ኮሚቴ ያዘጋጀውን ስልጠና እና ፊፋ ባዘጋጀው የገጽ ለገጽ (online) እግር ኳስ ስልጠናዎችን በመውስድም ሙያውን በስፋት ያዳበረበት ሁኔታ መፈጠሩን ይናገራል፡፡

አቶ ታምሩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከ15 ዓመት በታች ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድን ለስምንት ዓመታት አገልግሏል፡፡ ከብሔራዊ ብድኑ ጋር በአፍሪካ ወደሚገኙ ከ20 ሀገራት በላይ በመጓዝ የህክምና ቡድን ኃላፊና የህክምና ባለሙያ በመሆን አገልግሏል፡፡

እንደዚሁም የኦሎምፒክ ቡድንን በመቀላቀል በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች (All African games) ላይ የጤና ክፍል ኃላፊ በመሆን ሰርቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ የስፖርት ህክምናና የፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሙያ፣ እንዲሁም የአሰልጣኞች አሰልጣኝ በመሆን ወደየክልሎች በመዞር ስልጠናዎችን መስጠት ችሏል፡፡

በቀድሞ ደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ይሰራበት ስለነበረው አጋጣሚ ሲያወሳ፡-

“በደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እየሰራሁ ነበር፡፡ ይህን ሥራ በመተው ወደ ስፖርት ህክምና በማዘንበል ወልቂጤ እግር ኳስ ክለብን ተቀላቀልኩ፡፡ በክለቡ ውስጥ የህክምና ኃላፊና ባለሙያ በመሆን ለሁለት ዓመታት አገልግያለሁ” በማለት የመንግስት ሥራውን በመተው ወደ ህክምናው ዘርፍ በስፋት መግባቱን ይናገራል፡፡

በዚህ መካከል የአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ስፖርት ክለብ የዋና ሥራ አስኪያጅ ማስታወቂያ ማውጣቱን ተከትሎ ይወዳደርና ያልፋል፡፡ በ2015 ዓ.ም በክለቡ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሥራ ሲጀምር ክለቡ በውድድር ዘመኑ ስድስተኛ ጨዋታውን አከናውኖ ነበር፡፡ በዚሁ ዓመት ክለቡም ውጤት ሳይቀናው፣ እሱም ብዙም ሳይቆይ ከክለቡ ጋር የነበረው ቆይታ ተቋጨ፡፡

“የአርባ ምንጭ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅነትን ካቆምኩ በኋላ በ2016 ዓ.ም ወደ ግል ሥራ ገባሁ፡፡ በሐዋሳ ከተማ ‘ፕራይም ፊዚዮቴራፒ ስፔሻሊቲ ክሊኒክ’ በመክፈት መስራት ጀመርኩና አሁን ይህንኑ ስራ እየሰራሁ እገኛለሁ፡ ፡ ክሊኒኩ አንድ ሜዲካል ዶክተር፣ አራት ፊዚካል ፊዚዮቴራፒስቶችና ሌሎች ባለሙያዎችን ጨምሮ በጠቅላላ ሰባት ባለሙያዎች በመያዝ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው” ሲልም ተናግሯል፡፡

ክሊኒኩ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያና ክልል ጤና ቢሮ ባስቀመጠው ደረጃ መሰረት አስፈላጊውን ሁሉ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን በማሟላት ፈቃድ እንደተሰጠው ይናገራል፡፡

ክሊኒኩ በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ አገልግሎቶች በመስጠት ላይ እንደሆነ የሚናገረው አቶ ታምሩ ለስፖርተኞች ጉዳት፣ ለአካላ ጉዳት፣ ስትሮክና ሌሎች ከወገብ ጋር ለተያያዙ በሽታዎች እንዲሁም የስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡

እንደዚሁም ለእግር ኳስ ተጫዋቾች፣ አትሌቶች፣ ከተለያዩ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች በሪፈር ለሚመጡ ተገልጋዮች በዘመናዊ የህክምና ማሽኖች በመታገዝ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ስፖርት ህክምና እና ፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ እየተጋበዘ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይም ይገኛል፡፡

በሥራ ዓለም ላይ በርካታ ውጣ ውረዶች በማሳለፍ የዛሬው ደረጃ ላይ መድረሱን የሚናገረው አቶ ታምሩ በእነዚህ ሁሉ የሚያስደስቱና አሳዛኝ ጉዳዮች ገጥመውታል፡፡ በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ ከብሔራዊ ቡድን ጋር ሀገሩን ወክሎ ማሊ ባማኮ ያደረገው ጉዞ፣ እንዲሁም የሥራ ዓለም አሀዱ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀጠር ሐዋሳ ከተማ ላይ ሲመደብ የተሰማው ደስታ የማይረሳ እንደሆነ አስታውሶናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በስፖርት ህክምና ዘርፍ አንቱታን ካተረፉ ባለሙያዎች መካከል እንደ ዶ/ር አያሌው እና ሌሎች ትላልቅ ባለሙያዎች ጋር ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አባል በመሆን የመስራት ዕድሉን አግኝቷል፡፡

“በሌላ በኩል ደግሞ በብዙ ውጣ ውረድ አጠገቤ የነበረችው እናቴ ስታርፍ የተሰማኝ ሀዘን ከፍተኛ እና የማይረሳ ጊዜ ነበር፡፡ የአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ በነበርኩበት ጊዜ ክለቡ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደበት አጋጣሚ በሥራ ዓለም ከገጠሙኝ አሳዛኝ ክስተቶች አንዱ ነበር” ሲል ደስታና ሀዘኑን አጋርቶናል፡፡

“በወቅቱ ክለቡን ስረከብ ያደራጀሁት እኔ አልነበርኩም፡፡ ስድስት ጨዋታዎችን ካከናወነ በኋላ ነበር በሥራ አስኪያጅነት የተረከብኩት፡ ፡ ከዚህ በኋላ የነበረው ውጤት ዝቅተኛ ነበር፡ ፡ እስከ መጨረሻው ያለንን አቅም በመጠቀም ክለቡ እንዳይወድቅ ጥረን ነበር፡፡ በመጨረሻው 30ኛው ሳምንት ጨዋታ ላይ አንድ ጎል አስቆጥረን ቢሆን ኖሮ አንወርድም ነበር፡፡ ነገር ግን ማስቆጠር ሳንችል ቀርተን ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመውረድ ተገደናል” ሲል ጊዜውን አስታውሶናል፡፡

በወቅቱ የጀርባ ህመም (የዲስክ መንሸራተት) ቢገጥመውም ህመሙ ሳይበግረው ተቋቁሞ በክራንች በመጨረሻው ጨዋታ ላይ መገኘት ችሎ ነበር፡፡ ወቅቱም በጣም አሳዛኝ ጊዜ ማሳለፉን አጫውቶናል፡፡ በ2016 ዓ.ም ደግሞ ክለቡ ሻምፒዮን በመሆኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ በማለፉ ትልቅ ደስታ ተሰምቶት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ለአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ደጋፊዎችና ቤተሰብ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡