የደቡብ አፍሪካዊያን ዕጣ ፈንታ
በፈረኦን ደበበ
ለውጦች በተፈጥሯዊ ሂደት መምጣታቸው የሚጠበቅ ቢሆንም ባልተጠበቁበት ሁኔታ መከሰታቸው ግራ ያጋባል፡፡ ቀጣይ ምን እንሆናለን? የሚል ሥጋትና ፍራቻንም ያስከትላሉ፡፡
ወደ ግጭት ከገቡ ሌሎች ሀገራት በተቃራኒ ደቡብ አፍሪካዊያን ለውጡን በምርጫ ካርድ/ኮሮጆ ብቻ ማግኘታቸው አዎንታዊ ቢሆንም በምን ዓይነት ሁኔታ ተግባብተን መንግሥት እንመሠርት? የሚለው ጥያቄ ግን ከባድ ሆነባቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ወደ እርስ በርስ መወቃቀስ መዞራቸው ያሳዝናል፡፡
አዎን፤ ላለፉት 30 ዓመታት ሀገሪቱን ሲመራ የነበረውና አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ የተባለው አንጋፋ ፓርቲ አሁን አብላጫ ድምጹን አጥቷል፡፡ ዋና ዋና አመራሮቹንም ቀስ በቀስ እያጣ በአብራኩ ሌሎች በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወልዷል፡፡
እንዲህ ዓይነት አስደንጋጭ ሁኔታዎች ሲከሰቱ እንዴት መፍትሄ ይገኛል? ከሚለው አንጻርም የብዙ ሀገራት ህገ- መንግሥታት ጥምር መንግሥትን እንደ አማራጭ የሚያስቀምጡ ሲሆን በሀገሪቱ የተነደፈው ዘዴም ይሄኛው ነው፤ ምንም እንኳን ከዙፋኑ ለወረደው አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ አማራጩ ባይወጣለትም፡፡
በሀገሪቱ ካሉ 400 የፓርላማ ወንበሮች፥ ባለፈው ሰሞን በተካሄደው ምርጫ 159ን ብቻ መቆጣጠር የቻለው ኮንግረሱ፥ በውድድሩ 87 መቀመጫዎችን ካገኘው ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ፣ 58 መቀመጫዎችን ካገኘው ኤም. ኬ ፓርቲ፣ 39 መቀመጫዎችን ካሸነፈውና ከግራ ዘመሙ የምጣኔ ሀብት ነጻነት ታጋዮች ፓርቲ እንዲሁም 17 መቀመጫዎችን ካሸነፈው ኢንካታ ፓርቲ በበላይነት ተቀምጧል፡፡
በግል ጥላቻና በተለያዩ ምክንያቶች አባላት ከዋናው ፓርቲ ተገንጥለው የተመሠረቱት የእነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሌላው ገጽታ ይህ ነው የሚባል የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያለመያዛቸው ሲሆን ይህ ደግሞ ወደ ስምምነት ለመምጣት አንዱ ዕድል ነው፡፡ ምንም እንኳን የነገሰው ጥርጣሬና መነታረክ ሥጋት የሚፈጥር ቢሆንም፡፡
አሁን ያለኝን ከፍተኛ ድምጽ ይዤ ከእነሱ ጋር ህጋዊ የሆነውን ጥምር መንግሥት ልመስርት ወይስ ከዚህ ዝቅ ባለ ደረጃ ሀገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ የሚችለውን “የአንድነት መንግሥት” ብቻ ልመሠርት እያለ ለሚያቅማማው አፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስም ሁኔታዎቹ ቀላል አይደሉም፡፡
አፍሪካ ኒውስ የተባለው የዜና ምንጭ እንዳቀረበው ትንታኔ ከሆነ ብዙዎቹ ፓርቲዎች ለሀገራዊ አንድነቱ አሉታዊ አስተሳሰብ ባይኖራቸውም አብላጫ ድምጽ ወደ ያዘው አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ለመቅረብ ግን ፍላጎት የላቸውም፤ ምክንያቱም የፓርቲው መሪና እስካሁን የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ ለመቀጠል ከሚፈልጉት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር መሥራትን ስለሚጠሉ፡፡
በምርጫው ውስጥ ገብተው ጥቂት ድምጽ ያገኙት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን ጨምሮ በርካቶች ራማፎሳን አጥብቀው መቃወማቸው በሀገሪቱ ቀጣይ ተስፋ ላይ ሥጋት የሚፈጥር ሲሆን ራማፎሳ በበኩላቸው ሥልጣን መልቀቁንም ሆነ የጥምር መንግሥት ምሥረታውን አሜን ብለው የሚቀበሉት አይደለም፡፡
እያንዣበበ ያለውን አደጋ ለመቀልበስ ሲባል ነው በአመራር ላይ የቆየው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ሁለቱንም አማራጮች ለራሱ በሚጠቅም መልኩ ለመቅረጽ እየሞከረ ያለው፡፡ የጥምር መንግሥት አማራጩን ሲቀበል፥ ደግሞ አሁን በሥልጣን ላይ ባሉት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሚመራ ሆኖ አቋማቸው ግን ለሠራተኛው ህዝብ በወገነ መልክ ማድረጋቸው ሁሉንም የሚያግባባ ተብሏል፡፡
በተጨማሪ የምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ወንጀልና ሙስናን መቆጣጠር፣ በህዝባዊ አገልግሎቶች ላይ መዋዕለ-ነዋይ ማፍሰስና ሀገሪቱን አንድ የማድረግ አቅጣጫም በፓርቲው በኩል ይፋ የተደረጉ አቋሞች ናቸው፡፡
የጥምር መንግሥት አማራጩን የፓርቲው ነባር አባላት ለምን ይጠሉታል ከተባለም በፓርላማ በሚደረጉ የፖሊሲ ክርክሮች እንዲሁም በመንግሥታዊ አሠራሮች ንትርኮችን በማስነሳት ተሰሚነቱን እያጣ ያለውን ፓርቲ የበለጠ ድባቅ እንዳይመታው በመሥጋት ነው፤ ምንም እንኳን ሥልጣኑን ጠቅልለን እንያዝ የሚል ምኞታቸውም የኋላ ኋላ ሊመጣ ከሚችለው ውርደት ባያድኗቸውም፡፡
በተያዘው ሰኔ ወር ላይ ፓርላማው ተሰብስቦ ፕሬዝዳንት ይመርጣል የተባለበትን ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም በመተሳሰብና በመግባባት መንፈስ መሥራት በቻሉ ነበር፡፡
ከእነዚህ ሥጋቶች አንዱ በፓርቲዎች መካከል ያለው የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ተጠቃሽ ሲሆን የግል ጥላቻና አንዱ ሌላውን በማታለል ሥልጣን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ወደ ንትርክ የሚያስገቡ ባህሪያት ናቸው፡፡
ገዢ ፓርቲ የነበረውና በአሁኑ ምርጫ የተሻለ ውጤት በማምጣት እራሱን ከሌሎች ከፍ ባለ ደረጃ ለማስቀመጥ እየጣረ ያለው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ልማታዊ መንግሥት ሆኖ ለሁሉም አማካይ አድርጎ እራሱን ሲመለከት፥ የእሱ የቅርብ ተቀናቃኙ ዴሞክራሲያዊ አሊያንስ ደግሞ ብዙ ገንዘብ ባላቸውና በነጭ ባለ ሀብቶች ስለተመሠረተ የነጋዴውን ህብረተሰብ ክፍል ይወክላል፡፡
ቀኝ ዘመም ከሆነው ከዚህ ፓርቲ እና አማካይ ላይ ካለው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ በስተግራ በቀድሞ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የሚመራው የኤም ኬ ፓርቲ የሚገኝ ሲሆን ሀገሪቱን እየመሩ ከቆዩት ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ጋር አልሠራም ማለታቸውና ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ሁሉ መጠየቃቸው ልዩነቱን የሚያባብስ ሁኔታ ነው፡፡
በዚህ መሥመር ላይ ለምጣኔ ሀብታዊ ነጻነት እታገላለሁ ከሚለው ኢ ኤፍ. ኤፍ. ፓርቲ ጋር ሆነው ወደ ስምምነቱ እንምጣ ወይስ አንምጣ እያሉ ባሉበት ሰዓት የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ከጥምር መንግሥት ይልቅ ሀገራዊ አንድነት መንግሥት መመሥረት ያስፈልጋል ማለቱም ውዝግቡን የሚያባብስ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቀዳሚ ድርሻውን ለእራሱ በመውሰድ ሌሎች ፓርቲዎች የእሱ አጋዥ እንዲሆኑ ስለሚያደርጋቸው።
በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ተሰሚነት አግኝተው ለረጅም ዓመታት በሥልጣን ላይ እንደቆዩ ፓርቲዎች አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ከሌሎች ጋር የሚያደርገው እና እንዲሁም ሌሎች እርስ በርስ የሚያደርጉት ሽኩቻ ተጧጡፎ ቀጥሏል- ምንም እንኳን የኋላ ኋላ ተስፋ ሰጪ መረጃዎች እየወጡ ቢሆኑም፡፡
እኩልነትን የሚያሳጡ የሀብት ያለመመጣጠን፣ የዘር ልዩነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሙስናና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ባሉባት ሀገር ችግሩ በሠላማዊ መንገድ ከተፈታ የመንግሥት ምሥረታውን ለማፋጠንም የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው